Saturday, 23 August 2014 11:32

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር የአለም 1ኛ የሆነችበት ሚስጥር!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

             መንግስት እንደሚለው፤ ጋዜጠኞችን የሚያዋክበውና የሚያስረው በርካታ ጋዜጠኞች ስርዓት አልበኛና ነውጠኛ ስለሆኑ ይሆን? ወይስ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ መንግስት በጭራሽ የነፃነትን ጭላንጭል የማይፈቅድ የለየለት አምባገነን ስለሆነ?
እንደምታውቁት፤ በዚህ አሳዛኝና አሳሳቢ የአገሪቱ እውነታ ውስጥ፤ “ሕዝቡ” የለበትም። በዚህ ላይ መንግስትና ገዢው ፓርቲ፣ እንዲሁም አብዛኞቹ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች ይስማሙበታል። በቃ! “ሕዝቡ”... ለእውነት የቆመ፣ ነፃነት ወዳድ፣ በቅንነነትና በፍትህ የሚያምን፣ ኩሩና የሰላማዊ ነው። ችግሩ ያለው ሌላ ጋ ነው። ማን ጋ? እዚህኛው ጥያቄ ላይ፣ ልዩነት ይመጣል። መንግስት፣ “አመኛ” የሚላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና “የተቃዋሚዎች ልሳን” የሚላቸውን ጋዜጠኞች ይወነጅላል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ ይኮንናሉ። እስቲ ሁለቱንም በየተራ እንመልከታቸው።
በቅርቡ በነፃ መፅሔቶች ላይ በቀረበው ክስ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ነገር አለ - መፅሔቶቹ አመፅን ይቀሰቅሳሉ የሚል። ገና በፍርድ ቤት ባይረጋገጥም፣ እንዲያው ነገሩ እውነት ቢሆን እንኳ፤ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ያስከስሳል ወይ? አመፅን የሚቀሰቅስ ሁሉ አይከሰስም -  ጉዳት ካደረሰ ወይም ደግሞ ካሁን አሁን ጉዳት ያደርሳል የሚል አጣዳፊ ስጋት ካልተከሰተ በቀር። የአመፅ ቅስቀሳ በተጨባጭ አመፅን ካልፈጠረ በቀር ሊያስከስስ አይገባም ማለቴ አይደለም። የአመፅ ቅስቀሳው ለጊዜው ጉዳት ባያደርስም፣ ቢያንስ ቢያንስ አስጊ ከሆነ ... ያኔ ክስ ሊመጣ ይችላል - በግልፅ የሚታይ ደራሽ አደጋ የሚጥር ከሆነ ማለት ነው - (clear and present danger) እንደሚባለው።
ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስላችሁ። የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም ሃሳቦችን ማሰራጨት፣ ያለ ጥርጥር አመፅን ከመቀስቀስ የተለየ ትርጉም የለውም። የግል ንብረትን ለመውረስና የአንድ “አብዮታዊ ፓርቲ” አምባገነንነትን ለማስፈን፣ ከአመፅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም በማለት የሚሰብኩ ናቸውና። ነገር ግን፤ አያስከስሱም። ለምን? ዛሬ ቅስቀሳው አመፅን አልፈጠረም፤ አጣዳፊ አደጋ ይፈጥራሉ ለማለት የሚስችል ምልክት የለም።
ሌላ መረጃ ልጨምርላችሁ። የአገሪቱ መንግስት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ነባሮቹ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግድ ስርዓቱ ሁሉ የሰይጣን ተወካዮች ናቸው ብለው የሚያምኑ ሰዎች፤ በይፋ እምነታቸውን ይሰብካሉ፤ መንግስትን ጨምሮ የሰይጣን ተወካዮች የተባሉት ተቋማት በሙሉ እንደሚፈራርሱና አመድ እንደሚሆኑ ዘወትር ይሰብካሉ፤ ያንንም ጊዜ ይናፍቃሉ። ግን፣ አመፅ አልፈጠሩም፤ አልያም የአመፅ ጥፋት ለመፍጠር አፋፍ ደርሰዋል የሚያስብል የአደጋ ፍንጭ የለም። ስለዚህ ምንም የሚያስከስስ ወንጀል አልሰሩም። እንዲያውም፤ መንግስታዊው ስርዓት የሰይጣን ተወካይ ነው ብለው መስበክ መብታቸው ስለሆነ ነው፤ በይፋ መፅሔት የሚያሰራጩት፤ በየመንገዱ የሚሰብኩት፤ በየሳምንቱ ከደርዘን በላይ በሆኑ አዳራሾች ጉባኤ የሚያካሂዱት።
 በአመፅ “አብዮታዊ አምባገነንነትን” ለማስፈን የሚቀሰቅሱ ቅሪት የኮሙኒዝም አፍቃሪዎችም ሆኑ፣ “መንግስት የሰይጣን እንደራሴ ነው” ብለው የሚያምኑ ሰባኪዎች፡ “ያንን ፃፋችሁ፤ ይሄንን ተናገራችሁ፤ መፅሔት አሳተማችሁ፣ በራሪ ወረቀት በተናችሁ” ተብለው አይከሰሱም። ለምን? አሁን የፈጠሩት አመፅ የለም፤ አሁን የጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰ አጣዳፊ አደጋም የለም። ስለዚህ ወንጀል አልፈፀሙም። ወንጀል ካልፈፀሙ ደግሞ፣ መታሰርና መዋከብ የለባቸውም።
“ወንጀል አልሰሩም፣ ሃሳባቸውን ቢገልፅና ቢሰብኩ መብታቸው ነው” ሲባል ግን፤ “ሃሳባቸው ትክክልና ጠቃሚ ነው” ማለት አይደለም። ሃሳባቸው፣ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው፤ ጎጂ ነው። ነገር ግን፤ “ሃሳባቸው የተሳሳተ ነው፤ ወደፊት ጉዳት ያደርሳል” የምንል ከሆነ፣ ከእነሱ ተሽለን ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ እስከያዝን ድረስ መፍትሄው ቀላል ነው። ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና “ሆ” ብሎ የሚጎርፍ ተከታይ እንዳያገኙ፣ በሃሳብ ተከራክረን ልናሸንፋቸው እንችላለን - ስህተታቸውንና ጉድለታቸውን በግልፅ በማሳየትና ትክክለኛውንና ጠቃሚውን ሃሳብ በማቅረብ። “መተማመኛህ ምንድነው?” በሉ።
ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ “ህዝቡ” ቅዱስ ከሆነ፣ ... አብዛኛው ሰው ለእውነት በመቆምና ነፃነት በመውደድ የእኔነት ክብር የተጎናፀፈ ከሆነ፤ ... ማለትም አገሪቱ የስልጡን አስተሳሰብ ባለቤት ከሆነች... ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል።
የአመፅ ቅስቀሳ ከየትም ቢመጣ ሰሚ አያገኝም፤ እያሰለሰ የሚያስርና የሚያዋክብ አምባገነንም አይኖርም። “በስልጡኑና በአስተዋዩ ሕዝባችን” ፊት እየቀረቡ በመከራከር ብቻ ማሸነፍ ይቻላል። መቼም “ሕዝቡ” ስልጡን እስከሆነ ድረስ፣ በሃሳብ ክርክር ላይ፤ ከተሳሳተና ከጎጂ ሃሳብ ይልቅ፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ብልጫ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር፤ ትክክለኛ አስተሳሰብ ካልያዝን ነው፤ ወደ እስርና ወደ ወከባ የምንቸኩለው።
አሁን፣ “አመፅን ቀስቅሰዋል” ተብለው ወደ ተከሰሱት መፅሄቶች እንመለስ። የመጀመሪያው ጥያቄ፣ “አመፅ ቀስቅሰዋል የተባሉት መፅሔቶች፣ በእርግጥ አመፅ ፈጥረዋል ወይ?” የሚል ነው። እስካሁን፣ መፅሄቶቹ አመፅ ስለመቀስቀሳቸው እንጂ አመፅ ስለመፍጠራቸው በመንግስት የተነገረ መረጃ የለም። ይሄ አያከራክረንም። ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንሻገር - “አፋፍ ላይ የደረሰ ግልፅ የአደጋ ስጋትስ ተከስቷል ወይ?”
ስጋትማ መች ይጠፋል ብትሉ አይገርመኝም። ደግነቱ፣ ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፣ ዛሬ በአመዛኙ የተረጋጋ ሁኔታ ይታያል። “ሁሉም ነገር አማን ነው” ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያ እንደ ብዙዎቹ ኋላቀር አገራት በቀላሉ ለአደጋ የምትጋለጥና ብዙም ከስጋት ያልራቀች አገር ናት። እንዲያም ሆኖ መንግስት፣ “በመፅሔቶቹ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቄያለሁ” ብሎ በጭራሽ የሚናገር አይመስለኝም።
ደግሞስ፣ በሳምንት አንዴ የሚሰራጩ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች እንዴት ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ትልቅ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ? በየእለቱ ከጥዋት እስከ ማታ የሚሰራጩ በደርዘን የሚቆጠሩ የቲቪና የሬድዮ ጣቢያዎችን ይዞ፤ በመቶ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችንና በሺ የሚቆጠሩ የ”ኮሙኒኬሽን” ባለሙያዎችን ያሰማራ መንግስት፤ ከመሃል አገር እስከ ጠረፍ ድረስ እልፍ ካድሬዎችን አሰማርቶ፣ ከደርዘን በላይ ግዙፍ ማህበራትንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትን ያደራጀ ገዢ ፓርቲ፣ እንዴት በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶችን በክርክር ማሸነፍ ይሳነዋል? በ“ሕዝቡ” ዘንድ ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና ለአመፅ “ሆ” ብሎ የሚነሳ ተከታይ እንዳይኖራቸው ማድረግ አቅቶት ስጋት ላይ ይወድቃል?
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም። ለዚህም ነው፤ መንግስት “በመፅሔቶቹ ምክንያት አገሪቱ ስጋት ላይ ወድቃለች” ብሎ ሊናገር የማይችለው። አሃ! በአራት መፅሔቶች ሳቢያ የአገሪቱ የመንግስት ስጋት ላይ ከወደቀ፤ ... ወይ መንግስት ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ አልያዘም፤ አልያም “ሕዝቡ” ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የለውም ማለት ነው።    
ያው፣ እንደተለመደው መንግስትና ገዢው ፓርቲ፤ “ፈፅሞ እንከን የለብንም፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ይዘናል” ባይ ናቸው። ስለዚህ ችግሩ ያለው፣ “ሕዝቡ” ላይ ሳይሆን አይቀርም። አመፅ ይቀሰቅሳሉ በሚል የተከሰሱት መፅሔቶች ለመንግስት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉት፣ ነውጥ የሚያፈቅርና በትንሽ ቅስቀሳ “ሆ” ብሎ ለመትመም የተዘጋጀ አስተዋይነት የጎደለው ኋላቀርና ግልብ “ህዝብ” ካለ ብቻ ነው።
“ሕዝቡ”፤ ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የሌለው፣ በቀላሉ የሚታለል፣ እንደ ከብት እየተነዳና እየተንጋጋ ነውጥን የሚደግፍ ወራዳ ካልሆነ፣ ችግር አይፈጠርም። ለእውነትና ለነፃነት በመቆም የእኔነትን ክብር የተጎናፀፈ “ሕዝብ” ውስጥ፤ የነውጥ ቅስቀሳ ጉዳት አያደርስማ። “የምፅአት ቀን ደርሷልና ወደ ፅዮን ተራራ ውጡ” ብሎ በእንግሊዝና በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ከሚቀሰቅስ ሰባኪ የተለየ አይሆንም - በዛሬ ዘመን ብዙ ሰሚ አያገኝም፤ ቢሰሙትም ተከታይ ሆነው አይጎርፉለትም።
ልክ እንደዚያው፣ መንግስት እንከን አልባ ከሆነና “ሕዝቡ” ስልጡን ከሆነ፤ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች በሳምንታዊ ሕትመት ብቻ ሳይሆን ነጋ ጠባ አመፅ ቢቀሰቅሱ እንኳ ቅንጣት ታህል ስጋት መፍጠር አይችሉም። በእንከን አልባው መንግስት ላይ ስጋት መፍጠር ከቻሉ ግን፤ ያለ ጥርጥር “ሕዝቡ” ላይ ችግር አለ። “ሕዝቡ” ክፉ የአመፅ ጥም አለበት፤ አልያም በጥቂት ቅስቀሳ የሚንጋጋ ተላላ ሞኝ ነው። የዚህን ያህል እጅግ የባሰበት ኋላቀርነት ውስጥ ባይዘፈቅ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ የኋላቀርነት ዝንባሌ የተጠናወተው መሆን አለበት። እንዴት? ያው፣ ቅስቀሳ እስካልሰማ ድረስ፣ ጨዋ ይሆናል። ቅስቀሳ የሰማ ጊዜ ግን፤ ናላው ይዞራል፤ ለነውጥ ይነሳል - በሌላ አነጋገር ለነውጥና ለተላላነት የተጋለጠ ነው። “አይ፤ ሕዝቡን አትንካ” ከተባለ፤ ሌላኛ አማራጫችን ጣታችንን መንግስት ላይ መቀሰር ይሆናል። ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ይስማማሉ።
እና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የአለም መሪ ለመሆን የምትፎካከረው፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ስለሆነ ይሆን? በእርግጥ፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ ዛሬ ጋዜጠኞችን አሰረ ወይም አዋከበ ብለን እንደ አዲስ የምንገረምበት ምክንያት አናገኝም። እንዲያውም፤ ሳይታሰሩ የቆዩ ጋዜጠኞችና ሳይዘጉ የቆሙ መፅሔቶች መኖራቸው ነው የሚገርመን።
በሌላ አነጋገር፤ ገዢው ፓርቲ የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ የግል ነፃ ጋዜጣና መፅሔት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፤ እንደ ኤርትራ ወይም እንደ ሰሜን ኮሪያ። ጥሩ! ገዢው ፓርቲ “የለየት አምባገነን” ባይሆንም እንኳ... ተራ አምባገነን ቢሆንኮ በቂ ነው። ማሰርና ማዋከብ የዘወትር ስራው ያልሆነ፣ ሰበብ ካገኘ ግን የማያልፍ. ወይም እያሰለሰ የሚነሳበት ለተራ አምባገነን ጋዜጠኞችን የሚያስረውና መፅሔቶችን የሚዘጋው ስጋት ስለፈጠሩበት ላይሆን ይችላል።
እናም፤ መፅሔቶቹ በየሕትመታቸው የሚፅፉት፣ መረጃ ለማሰራጨት፣ “ሕዝቡ”ን ለማሳወቅ፣ ለመልካም ለውጥ ለማነሳሳትና ለመቀስቀስ ቢሆንም፤ “ተችተውኛል፣ ፓርቲው የማልፈልገውን መረጃ ያሰራጫሉ፣ ለመንግስት የማይጥም ሃሳብ ይፅፋሉ፣ ደፍረውኛል” በሚል ከማሰር አይመለስም እንበል። እሺ ይሁን። ግን፤ ይሄን ሁሉ በግላጭ የሚያየው የአገሪቱ “ሕዝብ”፣ ለእውነትና ለነፃነት የቆመው፣ ለፍትህና ለሰው ክብር ፍቅር ያለው “ስልጡኑ ሕዝብ”፣ መንግስትን በመገሰፅ “ተው” ይለዋል? ለመሆኑ፤ ከመነሻው “ሕዝቡን” ማነሳሳትና መቀስቀስስ ለምን አስፈለገ? መንግስት አምባገነን ቢሆንም፣ ሕዝቡ ይህንን ስለማያውቅና ስለማይገባው ይሆን? ወይስ ሕዝቡ የመንግስትን አምባገነንነት ቢያውቅም፣ ለእውነትና ለነፃነት ደንታ ስለሌለው፣ የእኔነት ክብር ስለራቀው ወይም በጣም ፈሪ ስለሆነ ቀስቃሽ ያስፈልገዋል? ያው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚሉት መንገድ ስንሄድም፤ “ሕዝቡ” ላይ (እኛው ላይ) ጣታችንን መቀሰራችን አልቀረም።
ለማለት የፈለግኩት ምንድነው? በአንድ በኩል፤ ኢህአዴግና መንግስት ራሳቸውን እንደ እንከን የለሽ በመቁጠር፤ የዚህ አገር ችግር በአራት በአምስት መፅሔቶች ላይ ለማሳበብ የሚያደረጉት ሙከራ ዋጋ የለውም። በሌላ በኩል፤ የብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃራኒ ሙከራም አያስኬድም። ኢህአዴግ በአንዳች ምክንያት፣ በምርጫም ሆነ በአመፅ፣ ወይም በሌላ መንገድ ከስልጣን ቢወርድ፣ ኧረ እስከነጭራሹ ጥፍት ቢል እንኳ፣ ተአምረኛ ለውጥ አይመጣም። የአገር ኋላቀርነት በአንዳች ተዓምር ብን ብሎ አይጠፋም።

Read 4228 times