Saturday, 23 August 2014 11:28

ተጨማሪ 7 ጋዜጠኞች አገር ለቀው ወጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

በአንድ ወር ውስጥ 12 ጋዜጠኞች ተሰደዋል

                   በፍትህ ሚኒስቴር ክስ የቀረበባቸው የ“ሎሚ” መፅሄት ባለቤትን ጨምሮ በመፅሄቱ ላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች ይሰሩ የነበሩ 5 ጋዜጠኞች አገር ለቀው የወጡ ሲሆን የ“አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ እና የ “ጃኖ መፅሄት” ባለቤትም እንደተሰደዱ ታውቋል፡፡
ሰሞኑን ከሃገር ወጥተዋል የተባሉት ባለፈው ሳምንት በ “ሎሚ” መፅሄት ባለቤትነታቸው ለቀረበባቸው ክስ ፍ/ቤት ቀርበው በ50ሺህ ብር ዋስትና የተለቀቁት አቶ ግዛው ታዬ፣ የመፅሄቱ ሚዲያ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ድርሻ፣ ዋና አዘጋጁ ሰናይ አባተ እንዲሁም ሁለት አምደኞች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የ“አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ቶማስ አያሌው እና የ“ጃኖ” መፅሄት አሳታሚ አስናቀ ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ባለቤት አቶ አስናቀ ልባዊም ከሃገር ወጥተዋል ተብሏል፡፡
የ“አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ እና የ “ሎሚ” መፅሄት አምደኛ ዮናስ ወ/ሰንበት፤ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ጠዋት ወደ “አፍሮ ታይምስ” ቢሮ ከሌሎች ሁለት የስራ ባልደረቦቹ ጋር መሄዱን፣ ቢሮ ሲደርሱም በህንፃው ላይ ያሉ ተከራዮች “የእናንተ ባልደረቦች እኮ ከሃገር ወጥተዋል ተብሏል” ብለው ሲነግሯቸው ባልደረቦቻቸው ሃገር ለቀው መውጣታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ “እኛ እንደተለመደው የጋዜጣዋን ስራ ለመስራት ነበር ወደ ቢሮ ያቀናነው” ያለው ጋዜጠኛ ዮናስ፤ ወዲያውኑ ቢሮውን ቆልፈው ቁልፉን ለህንፃው አከራዮች በመስጠት ወደየመጡበት መመለሳቸውን ተናግሯል፡፡ “በዚህ መልኩ የስራ ባልደረቦቻችን ከሃገር መውጣታቸው ያሳዝናል” ያለው ጋዜጠኛው፤ “የስራ ባልደረቦቻችንንም አጥተናል፣ የምንሰራበት ሚዲያም ተዘግቷል፤ በግራ መጋባት ውስጥ ነው ያለነው” ብሏል፡፡  አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቀደም ብሎ ከሃገር የወጣውን የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጨምሮ መንግስት በ6 የሚዲያ ተቋማት ላይ ክስ መመስረቱን ተከትሎ 12  ጋዜጠኞች ከሃገር የወጡ ሲሆን ክስ የቀረበባቸው አብዛኞቹ የህትመት ውጤቶችም አሳታሚ በማጣት ከገበያ ውጪ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የሚዲያ ተቋሟቱ የፍ/ቤት ውሎ
ባለፈው ረቡዕ  በዋለው ችሎት የ“ሎሚ” መፅሄት ባለቤት በቀጠሮአቸው ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ፍ/ቤት በቀጣይ ቀጠሮ በፖሊስ ተይዘው ታስረው እንዲቀርቡ  ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን የ “ፋክት” መፅሄት ባለቤት በጋዜጣ ጥሪ ይደረግላቸው ተብሏል፡
ባለፈው ሳምንት አርብ ነሐሴ 9 ፍ/ቤት ቀርበው “በቀረበብኝ ክስ ላይ ከህግ ባለሙያ ጋር ተማክሬ ልቅረብ” ያሉት የዳዲሞአ ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ባለቤት አቶ ግዛው ታዬ፤ ረቡዕ ዕለት ፍ/ቤቱ ሊገኙ ባለመቻላቸው ፍ/ቤቱ በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡ አዝዞ ጉዳዩን ለመመልከት ለነሐሴ 19 ቀጥሯል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ችሎቱ የ “ፋክት” መፅሄት ባለቤት የወ/ሮ ፋጡማ ኦርዮን ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን ፖሊስ ተጠርጣሪዋን በአድራሻቸው ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም የሚል ማመልከቻ ለፍ/ቤቱ በፅሁፍ ካቀረበ በኋላ አቃቤ ህግ በማመልከቻው መሰረት ፖሊስ ተጠርጣሪውን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥለት ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍ/ቤቱም ተጠርጣሪዋ በአድራሻቸው ሊገኙ አልቻሉም የሚል ተደጋጋሚ ማመልከቻ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሶ፤ ተጠርጣሪዋ የቀረበባቸውን ክስ ቀርበው እንዲከላከሉ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ይደረግላቸው፤ ካልሆነም ጉዳያቸው በሌሉበት ይታያል ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መዝገቡንም ለነሐሴ 26 ቀጥሯል፡፡ የ“አዲስ ጉዳይ” መፅሄት አሳታሚ ሮዝ ህትመት ስራዎች እና ባለቤቱ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ጉዳይ ከነገ በስቲያ ሰኞ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል። ጽ/ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ በዚህ መዝገብ ላይ ለተጠርጣሪዎቹ የጋዜጣ ጥሪ ይደረግላቸው፣ ካልሆነም ጉዳያቸው በሌሉበት ይታያል የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
የ “ሎሚ” እና የ “ፋክት” መፅሄት አሳታሚዎችን ጨምሮ የ “አዲስ ጉዳይ”፣ “ጃኖ” እና “እንቁ” መፅሄቶች እንዲሁም የ “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚዎችና ባለቤቶች ላይ ፍትህ ሚኒስቴር ክስ የመሰረተ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሚዲያ ተቋማት ባወጧቸው ፅሁፎች ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ በአመፅ ለማፍረስ በማሰብና ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት በሚሉ የወንጀል ፍሬዎች ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገ የነፃ ፕሬስ ተሟጋች ድርጅት፣ በ2014 ባወጣው የፕሬስ ነፃነት የደረጃ ዝርዝር ኢትዮጵያን ከ180 የዓለም አገራት በ143ኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Read 7437 times