Saturday, 23 August 2014 11:23

ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ የጠየቁት ዋስትና ውድቅ ሆነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ሴት ተከሳሾች የመብት ጥሰት እየተፈፀመብን ነው ብለዋል

            አገሪቱን በሽብር ለማናወጥና በአመፅ ለመበጥበጥ አሲረዋል፣ የሽብር ስልጠናዎችን ወስደዋል፣ ይህን ለማስፈጸም ኦነግና ግንቦት ሰባት ከተባሉ አሸባሪ ቡድኖች ጋር በመገናኘት፣ ገንዘብ በመቀበልና በህቡዕ በመደራጀት የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት የተከሰሱት ሰባቱ ጦማሪያንና ሶስቱ ጋዜጠኞች የጠየቁትን የዋስትና መብት ከፍተኛው ፍ/ቤት ውድቅ አደረገው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በሽብርተኝነት ከተከሰሱ በኋላ የተከሳሾቹ ጠበቆች ደንበኞቻችን በሽብርተኝነት የሚያስከስስ ወንጀል ባለመፈጸማቸው ዋስትና አያስከለክላቸውም፣ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ ሶስት ከተዘረዘሩት የወንጀል ድርጊቶች አንዱንም ባለመፈፀማቸው የዋስትና መብት ሊከበርላቸው ይገባል ሲሉ መከራከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የ9ኛ ተከሳሽ የጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ዶ/ር ያሬድ ለገሰ ደንበኛዬ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ ሶስት ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱንም ባለመፈፀሟ ዋስትና መከልከሏ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ጉዳዩ ለፌደራል ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ይላክልኝ ሲሉ ፍ/ቤቱን ጠይቀው የነበረ ሲሆን ይህም ጉዳይ በፍ/ቤቱ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ተከሳሾቹ በጸረ ሽብር አዋጁ የተከሰሱ በመሆናቸው ፣ ማሴር፣ በህቡዕ መደራጀት፣ ለአመፅ መንቀሳቀስ በሽብርተኝነት ያስከስሳል ሲል የተከራከረው በፍ/ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ተከሳሾቹ በእስር ቆይተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል፡፡
ከጦማሪዎቹ አንዷ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ በ6/12/2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ቢደረግላትም ባለመቅረቧ ክርክሩ በሌለችበት እንዲካሄድ ፍ/ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
ረቡዕ እለት ረፋድ ላይ ፍ/ቤት የቀረቡት ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው በኩል የሽብር ድርጊት ስላልፈጸሙ ጉዳያቸው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ እንዲታይ ቢጠይቁም ተቀባይነትን አላገኙም፡፡ አንድ ተጠርታሪ በሽብርተኝነት ክስ ከቀረበበት በፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀፅ 25/5 ላይ ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ እና የዋስትናን ጉዳይ በተመለከተ ፍ/ቤቶች በህጉ መሰረት ዋስትናን የሚነፍጉበት አግባብ ስላለ ተከሳሾቹም ተከሰሱት በሽብር ወንጀል በመሆኑ ዋስትና ያስከለክላቸዋል ብሏል ፍ/ቤቱ። የ9ኛ ተከሳሽ ጠበቃ ደንበኛቸው ጉዳይ በፌደራል ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ እንዲታይላቸው ያቀረቡት ጥያቄም በፀረ ሽብር አዋጁ የተከሳሾች በመሆኑ ጉዳዩ በአጣሪ ጉባኤ የሚታይበት የህግ አግባብ ስለሉለ መከራከሪያው ውድቅ እንዲሆን የጠየቁት አቃቤ ህግ ጥያቄያቸው ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
በዕለቱ ከ2ኛ እስከ 8ኛ ተከሳሾች ጠበቆች ሶስት የክስ መቃወሚያዎችን ለፍ/ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው መቃውሚያ አቃቤ ህግ በአንደናው ክስ ላይ “ሌሎች ያልተያዙ አባሎችን በማደራጀት” በሚል የተመለከተው አባባል የተከሳሾችን የመከላከል መብት የሚያጣበንብ ብቻ ሳይሆን ተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት የሚያቀርቧቸውን ምስክሮች ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ክሱን እንደሚቃወሙና ከሳሽ አቃቤ ህግ ሌሎች ያልተያዙ አባሎች የሚላቸወን በስም ዘርዝሮ ባልገለጸበት ሁኔታ ያቀረበው ክስ ውድቅ እንዲሆን ወይም በስም ማንነታቸውን ገልፆ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው የክስ መቃወሚያ ከሳሽ ለየትኛው ክስ እና በየትኛው ተከሳሽ ላይ እንዳቀረበው ባለመገለፁ በኤግዚቢት ዝርዝር ያመለከታቸው ንብረቶች ክስ ከቀረበበት ድርጊት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና አንዴትና ምን የወንጀል ድርጊት እንደተፈፀመባቸው የማይገልፅ በመሆኑ ከኤግዚቢት ዝርዝሩ ውስጥ ወጥቶ ለባለንብረቶቹ እንዲመለስላቸው ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
ጠበቆች በሶስተኛው የክስ መቃወሚቸው ከሳሽ አቃቤ ህግ ባቀረበው 2ነ ክስ ላይ ተከሳሾ “ለአመፅ የሚቀሰቅሱ ፅሁፎች በመበተን” በሚል ያቀረበውን በተመለከተ መቼ፣ የትና ምን የሚል ፅሁፍ እንደበተኑ ያልገለፀ ሲሆን ይህም የተከሳሾችን የመከላከል መብት የሚያጣብብ እና የቀረበባቸውን ክስ ተረድተው እንዲከላከሉ የማስስችል በመሆኑ ከክሱ ውስጥ እንዲሰረዝ ወይም መቼ፣ ትና ምን የሚል ፅሁፍ እንደበተኑ አመልክቶ ክሱን እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠበቆቹ አመሃ መኮንን እና ሽብሩ በለጠ በፅሁፍ ለፍ/ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ተከሳሾቹ በእለቱ ለፍቤቱ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን የተከሰስንበት ወንጀል ሽብርተኛ ስለሚል ከሌሎች ተጠርታሪዎች ተለይተን ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ስር ወድቀናል ያሉ ሲሆን በተለይም 4ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች ማህሌት ፋንታሁንና ኤዶም ካሳዬ ከቤተሰብ ለመገናኘትና ስንቅ ለመቀባበል የተፈቀደልን ከ6፡00-6፡10 ሰዓት 10 ደቂቃ ብቻ ነው፤ ቀድሞ ያልተመዘገበ እንዳያገኘን ተደርገናል፤ የምንፈልጋቸው ቤተሰቦችና ጓደኞቻችንን ለጥየቃ እንዳናስመዘግብ ተከልክለናል ያሉ ሲሆን በሃኪም፣ በጠበቃ በቤተሰብና በጓደኛ እንዳንጠየቅ የተደረገብን ገደብ እንዲነሳልንና እንዲሁም በተለያዩ የእስረኛ ኮሚቴዎች እንዳንሳተፍ መደረጋችን አግባብ ባለመሆኑ ይህ ሁሉ እገዳ እንዲነሳልን ፍ/ቡቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ይስጥልን ብለዋል፡፡
ፍ/ቤቱም አቤቱታውን የክስ መቃወሚውን ካዬ በኋላ ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ የማረሚያ ቤት ተወካይ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርቦ ምላሽ እንዲሰጥ ካዘዘ በኋላ ተከሳሾችም ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።  

Read 2118 times