Saturday, 23 August 2014 11:19

“ጐጆ እቁብ” የአባልነት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ መቆሙን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

         ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው የ“ጎጆ እቁብ” የአባልነት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆሙንና ገንዘብ የመሰብሰብ ስራው እንዳልተጀመረ መስራቹ አቶ ናደው ጌታሁን የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከእቁቡ ጋር ይሰራሉ የተባሉ አምስት ባንኮች ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡
“ጐጆ እቁብ” ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ አምስት ባንኮች የጐጆ እቁብ ሰብሳቢ ተደርገው የተገለፁት በስህተት መሆኑን ጠቁሞ ጐጆ እቁብ ግን ስራውን ለመስራት የሚያስችል ዝግ ሂሳብና የቁጠባ ሂሳብ በተለያዩ ባንኮች መክፈቱን አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በንብ ባንክና በአቢሲኒያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዕቁቡን ለመጀመር ሂሳብ መከፈቱን የገለፁት የእቁቡ መስራችና ዳኛ አቶ ናደው፤ ገንዘብ የመሰብሰብ ስራው እንዳልተጀመረና የአባላት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ መስራች ነኝ የሚሉት ግለሰብ ስራውን ከባንኩ ጋር ለማከናወን ስምምነት እንደፈፀሙ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫ መስጠታቸውንና በተለያዩ በራሪ ወረቀቶች ላይ የባንኩን ሎጎ አሳትመው ማሰራጨታቸውን ጠቅሶ ባንኩ ከጎጆ እቁቡ ጋር ምንም አይነት የስራ ግንኙነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡  ከእቁቡ ጋር አብሮ ይሠራል የተባለው የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ አበባው ዘውዴ በበኩላቸው፤ ባንካቸው ከጐጆ እቁብ ጋር ምንም አይነት የስራ ስምምነት እንደሌለው ነገር ግን በሶስት ግለሰቦች ስም በቅንፍ ጐጆ እቁብ ተብሎ በአንደኛው የባንኩ ቅርንጫፍ የዝግ ሂሳብ መከፈቱን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ ከእቁቡ ጋር አብረው ይሰራሉ የተባሉት አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኃላፊዎች የእቁቡ መስራች እንዳነጋገሯቸው ጠቁመው አብረው ለመስራት ግን ስምምነት አለመፈፀማቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።

Read 2915 times