Print this page
Saturday, 31 December 2011 09:52

የአብዱራፊን ተስፋና ስጋት

Written by  -አበባየሁ ገበያው-
Rate this item
(1 Vote)

ከአዲስ አበባ ጐንደር የገባነው በአየር ነው - በአውሮፕላን፡፡ ከዚያ በኋላ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በመኪና የአምስት ሰዓት መንገድ ይጠብቀናል - 230 ኪ.ሜ ገደማ፡፡ እንደ ትንግርት የሚታዩትን የሰሜን ሰንሰለታማ ተራሮች እየቃኘን ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ በነገራችን ላይ በእነዚህ ታሪካዊ ተራሮች ላይ አልፎ አልፎ አበጥ አበጥ ብለው የሚታዩ ጉብታዎች የልጃገረድ አጐጠጐጤ ስለሚመስሉ የብዙዎችን ዓይን ይስባሉ ወይም ያስታሉ፡፡ አስፓልቱን ጨርሰን ወደ ጥርጊያው መንገድ ከመግባታችን በፊት ያገኘነው የመጨረሻ ከተማ “አብርሃ ጅራ” ይባላል፡፡ ተገረምን፡፡ እንደ ሰው ስም ከነአባቱ ያለው ከተማ በማግኘታችን፡፡

ከተማው ለምን “አብርሃ ጅራ” ተባለ ብለን መጠየቃችን አልቀረም፡፡ አንድ ኦሮሞ ነው አሉ፡፡ ወንድሙ ይጠፋና እሱን ፍለጋ ይወጣል፡፡ እግሩ  ደግሞ ወደ ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል መራው፡፡ ተጉዞ ተጉዞ ደቡብ ሱዳን ጠረፍ ሊደርስ ሆነ፡፡ ግን ሳይደክመው አልቀረም፡፡ እናም በአካባቢው ላገኛቸው ሰዎች “አብርሃ ጅራ?” ሲል ጠየቀ - በትውልድ ቋንቋው በኦሮምኛ፡፡ “አብርሃ አለ?” ወይም “አብርሃን አይታችሁታል?” ነው ነገሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዚያ ከተማ ስም አብርሃ ጅራ ተባለ ሲሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ አጫወቱን፡፡ ያ የኦሮሞ ተወላጅ ወንድሙን ያግኝ አያግኝ እኛም አልጠየቅን ነዋሪውም አልነገሩን፡፡ እንዳገኘ ተስፋ አድርገን እንቀጥል፡፡

የሰሜን ተራሮች እንደ ብዥታ ነው ከዓይናችን ብን ብለው የጠፉት፡፡ አካባቢው በአንድ ጊዜ ጭር አለብን፡፡ ጐጆዎች፣ መንገደኞች፣ ከብቶች አላየንም፡፡ አየሩ ተቀይሯል፡፡   ከወይና ደጋ ወደ ቆላ፡፡ የተንጣለሉ የእርሻ ማሳዎች በርቀት ይታዩናል፡፡ ከማሳዎቹ በብዙ ርቀት ደግሞ የሱዳን ድንበር ተራሮች፡፡  በእርሻ ማሳዎቹ ላይ የሰሊጥ፣ የጥጥና የማሽላ ተክሎች በብዛትና በስፋት በቅለው ሰብስቡን  ደርሰናል ይላሉ፡፡ በእርግጥም ወቅቱ የአዝመራ ነው - ምርቱ የሚታጨድበትና ተሰብስቦ የሚከመርበት፡፡ አብዱራፊን የምትባለው ከተማ በዚህ ጊዜ ትደምቃለች - ትሞቃለች፡፡ ጉልበት ለስራ በሚመጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ተከበባለች፡፡ በየዓመቱ ከሰኔ እስከ ህዳር ባሉት ጊዜያት አብዱራፊ እንዲሁ ናት - የውቂው ደብልቂው አገር ትሆናለች፡፡ አብዱራፊን ተስፋና ስጋትን በአንድ ላይ ያቋተች ከተማ ናት - ህይወትና ሞት፡፡   ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በትራክተርና በእግር ጭምር አብዱራፊ የሚገቡት ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ታዳጊዎች በማሽላ፣ በሰሊጥና ጥጥ አጨዳ ስራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ ከምዕራብ ጐጃም ዞን፣ መራሂ ከተባለ አካባቢ እንደመጣ ያጫወተኝ የ16 ዓመቱ ወጣት አበራ፤ በአብዱራፊ የሰሊጥና የጥጥ  ለቀማ ሥራ መኖሩን ሌሎች የቀዬው ልጆች ጠቁመውት እንደመጡ ገልፆልኛል፡፡ በአካባቢው የምግብ አቅርቦት አለመኖሩ ቆይታቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ያወሳል አበራ፡፡ ምግብ ብቻ ሳይሆን መጠለያም የለም -አብዱራፊ፡፡ ብዙ ወጣቶች በእባብ እንደሚነደፉና ለወባ በሽታም እንደሚጋለጡ ይናገራል፡፡ ወደ አብዱራፊ መጥተው ከነበሩ የትውልድ ቀዬው ልጆች አብዛኞቹ ችግሩን መቋቋም አቅቷቸው መመለሳቸውን የሚናገረው አበራ፤ አንዳንዶቹም የበረሃ እራት ሆነው እንደቀሩ ሀዘን ባጠላበት ስሜት ገልፆልኛል፡፡ ከሰሜን ጐንደር እስቴ አካባቢ መምጣቱን የነገረኝ ሌላው የ23 ዓመት ወጣት ደግሞ በየዓመቱ ለዚሁ ስራ አብዱራፊንን እንደሚጐበኝ -አጫውቶኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ግን በጠና ታመመ፡፡ ሲመረመርም ወባ እንደያዘው አወቀ፡፡ ይሁንና ዘንድሮም አልቀረም፡፡ በለመደው ስራ ላይ ተሰማርቶ መጠነኛ ጥሪት ለመቋጠር አብዱራፊን ተገኝቷል፡፡  በአካባቢው ጐጆ ወይም መጠለያ የሚባል ነገር አይታይም፡፡ ወጣቶቹ ጥላ ያለበት አካባቢ ጠጋ ብለው ከቀዬአቸው ቋጥረው ያመጡትን ድርቆሽ ፈርፈር አድርገው ይመገባሉ፡፡ እዚያው ጋደም ይላሉ፡፡ አበራና ጓደኞቹ አዝመራውን ካጨዱና ከሰበሰቡ በኋላም ሌላ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ መሬቱን ለቀጣዩ የዘር ወቅት አርሶና አለስልሶ ማዘጋጀት ሁለተኛ ሥራቸው ነው፡፡ ጠቅላላ የሥራ ጊዜው አራት ወር ገደማ የሚፈጅ ሲሆን በየመሃሉ ታዲያ በጉልበት ስራ የደከመ አካልና አዕምሮን ዘና ለማድረግ ወደ ከተማ ብቅ ይላሉ፡፡ የሚዝናኑት ደግሞ በሌላ ሳይሆን በመጠጥና በዝሙት እንደሆነ አበራ ይናገራል፡፡ ከሽሬ ድረስ ገላዋን ቸርችራ ገንዘብ ለማግኘት አብዱራፊን የመጣችውን የ15 ዓመት ታዳጊ ጨምሮ በርካታ ወጣት ሴቶች በዝሙት አዳሪነት ይተዳደራሉ፡፡ ፈፅሞ ሥልጣኔ ያልጉበኛትና ያልዘመነችው ይህች ከተማ፤ የኤሌክትሪክ መብራት የሌላት ሲሆን የጄነሬተር መብራት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ብቻ ነው የሚቆየው፡፡ ከዚያ በኋላ ጨለማ ይወርሳታል፡፡ ሁሉ ነገር ውድምድም ይላል፡፡ ሆኖም አበራና ጓደኞቹም ሆኑ በዝሙት የሚተዳደሩት ጨቅላ እንስቶች የሚፈልጉትን ከማድረግ አያግታቸውም፡፡ መጠጡም ዝሙቱም ይቀጥላል - በድቅድቁ ጨለማ፡፡

ክፋቱ ደግሞ አበራና ጓደኞቹ ስለ ኤች አይ ቪም ሆነ ወሲብ - ወለድ በሽታዎች እምብዛም ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ከኮንዶም ጋር አይተዋወቁም፡፡  ስሜታቸውን የሚወጡት ህይወታቸውን ለአደጋ የሚዳርግ ልቅ የወሲብ ግንኙነት በመፈፀም ነው፡፡ በዝሙት ሥራ የሚተዳደሩት ለጋ ወጣት ሴቶችም ለትንሽ ገንዘብ ሲሉ ያለ ኮንዶም ወሲብ ለመፈፀም ፈቃደኛ ይሆናሉ - አንድም በግንዛቤ እጦት አሊያም በከፋ ድህነት የተነሳ፡፡አካባቢው የሱዳን ጠረፍ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ አያሌ ሱዳናውያን ወደ አብዱራፊን እየዘለቁ ያሻቸውን ሸምተው ይወጣሉ - ወሲብንም ጨምሮ፡፡ በዚህም የተነሳ አካባቢው የኤች አይቪ/ኤድስ ከፍተኛ ስጋት ያለበት ስርጭት መሆኑ ቀጥሏል፡፡ ለአካባቢው ስጋት የሆነው ኤችአይቪ/ኤድስ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በቆላ ዝንብ ንክሻ የሚመጣው በሽታ ሌላኛው የአካባቢው ስጋት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቬሴራል ሌሽማኒያሲስ በመባ\ለ የሚታወቀው በሽታ በጥገኛ ህዋስ ሳቢያ ከሚተላለፉ በሽታዎች አንዱ ሲሆን በመላው ዓለም በገዳይነቱ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል - ከወባ ቀጥሎ፡፡ የካላዘር በሽታ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ለሞት ይዳርጋል፡፡ ለዚህ ነው ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ዓለም አቀፍ የህክምናና የሰብዓዊ አገልግሎት ድርጅት (M.S.F) በአካባቢው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርፆ የሚንቀሳቀሰው፡፡ በፈረንሳይ ዶክተሮችና ጋዜጠኞች የተቋቋመው የሀኪሞች ቡድን፤ በኤች አይቪ ኤድስና በካላዘር በሽታዎች ዙሪያ ግንዛቤ በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን የህክምና መስጪያና ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያም አለው - እዚያው አብዱራፊን፡፡ በ2010 እ.ኤ.አ በአብዱራፊ ፕሮጀክት 394 የካላዘር በሽተኞች ህክምና እንደተደረገላቸው የሚጠቁመው የድርጅቱ መረጃ፤ በአሁኑ ወቅትም በካላዘርና በኤች አይቪ የተያዙ ህመምተኞች በመቆያ ጣቢያው እንዳሉ ያመለክታል፡፡  የካላዘር በሽታ ምልክቶች በአብዛኛው ከወባ ጋር እንደሚመሳሰል የተናገሩት የጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ረዳት አስተባባሪ አቶ አዳሙ ዘሪሁን፤ በዚህም ሳቢያ ብዙ ህመምተኞች በበሽታው መያዛቸው ሳይታወቅ እንኳ ሊሞቱ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ የካላዘር ህክምና ከአብዱራፊን ጊዜያዊ መጠለያ ውጪ በጐንደር ሆስፒታል ብቻ እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን ጥረቱ አብዱራፊንን የስጋት ከተማ ከመሆን መታደግ ይመስላል፡፡ ሠርተው ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ለማሻሻል በተስፋ ተሞልተው የሚመጡ ወጣቶች በግንዛቤ ማጣትና በዕውቀት ማነስ ህይወታቸውን እንዳያጡ የተለያየ ነፍስን የመታደግ ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ቡድኑ ይናገራል፡፡ አብዱራፊንን የስጋት ሳይሆን የተስፋ ከተማ እንደሚያደርጋት ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 

 

Read 3324 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 10:21