Saturday, 23 August 2014 11:14

የአርበኞች ህንፃ በ1ሚ. ብር ወጪ ሊታደስ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

          የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ህንፃ እድሳት ሊደረግለት መሆኑን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለፁ፡፡ ከ55 ዓመት በፊት ለአርበኞች አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባው ህንፃው፤ ለአራት ወለል እስካሁን በወር የሚያስገባው ገቢ 79ሺህ ብር ብቻ እንደሆነና ፕሬዚዳንቱ ባስጠኑት ጥናት ከእድሳቱ በኋላ ከ1ሚ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያስገኝ መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
15 የሚደርሱ ድርጅቶች በህንፃው ላይ ተከራይተው በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ለእድሳቱ እንዲለቁ የአራት ወራት ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን እድሳቱ ሲጠናቀቅ አሁን ላሉት ደንበኞች ቅድሚያ ተሰጥቶ በከተማው ዋጋ እንደሚከራዩ ተነግሮአቸዋል፡፡ አንዳንድ ተከራዮች ከእድሳቱ በኋላ በሚጨመረው የኪራይ ዋጋ ደስተኞች እንዳልሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለረጅም ዓመት በህንፃው ላይ የቆዩ ተከራዮች በጣም አነስተኛ የኪራይ ዋጋ እንደሚሰሩበትና ህንፃው ፈራርሶ፣ በረንዳው ላይ ውሃ ተኝቶ፣ ግድግዳውን የሽንት ቤት ፍሳሽ አበላሽቶት በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ታድሶ በከተማው ጥሩ ዋጋ መከራየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
“አባት አርበኞች ቀሪ ጊዜያቸው አስደሳች እንዲሆን ገቢ ማግኘት አለባቸው” ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በአሁኑ ሰዓት በቀን ስድስት ብር ብቻ እያገኙ ኑሮዋቸውን በችግር የሚገፉ አባት አርበኞች በቀን 25 እና 30 ብር እያገኙ፣ ጥሩ ህክምና እየተደረገላቸው ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ጥሩ እንዲመገቡ ለማድረግ ህንፃው የግድ መታደስና ጥሩ ገቢ ማስገኘት አለበት ብለዋል፡፡
“ህንፃው ታድሶ በጥናት የተረጋገጠውን ገቢ በወር ማግኘት ከቻለ መንግስት በየአመቱ የሚመድብልንን በጀት እግዜር ይስጥልን ብለን በራሳችን እንቆማለን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህን ለማድረግ እና እድሳቱን ለመጀመር በወጣው ጨረታ ኢንጂነሮች እና አርክቴክቶች ከቴክኒካል ፕሮፖዛል ጀምሮ የተለያዩ የሙያ ፕሮፖዛሎችን በማቅረብ እየተወዳደሩ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ለህንፃው እድሳት ከ800 ሺ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡ በህንፃው ላይ የምግብና የሆቴል ማሰልጠኛ፣ ባርና ሬስቶራንት፣ የልብስ ንፅህና መስጫ፣ የልብስ መሸጫ መደብር፣ የውበት ሳሎን፣ የኮምፒዩተር ማሰልጠኛ ት/ቤትና መኖሪያ ቤት የሚገኝ ሲሆን የኪራዩ ሁኔታ በቀድሞው ስራ አስፈፃሚ የተከናወነና የተወሳሰበ በመሆኑ አዲሱ የማህበሩ አመራር ይህን ለማጥራት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ህንፃው ታድሶ ሲያልቅ ህንፃው ስር ያለው ሲኒማ ቤት ታድሶ ለአገልግሎት እንደሚውል የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህ የሲኒማ አዳራሽ ውስጥ በየቦታው ተበታትኖ የተቀመጠ የአርበኞች ፎቶግራፍና የጦር ሜዳ ውሏችው ማስታወሻ በሙዚየም መልክ ይደራጃል ተብሏል፡፡

Read 1790 times