Saturday, 16 August 2014 10:36

ዕዳ የሌለበትን ድህነት እና በሽታ የሌለበትን ክሳት የሚያህል ነገር የለም! (የወላይትኛ ተረት)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ትናንሽ ልጆች ወደ ት/ቤት እየሄዱ ይጨዋወታሉ። የአንደኛው ልጅ አባት ወፍራም ናቸው፡፡ በዛ ላይ ሀብታም ናቸው፡፡ ትልቅ ህንፃም ይገነባሉ፡፡ የሁለተኛው ልጅ አባት ምስኪን ናቸው፡፡ ከሲታ ናቸው፡፡ በአንዲት የጭቃ ቤት ነው የሚኖሩት፡፡
የሀብታሙ ልጅ - የእኛን ፎቅ አየኸው? ሰማይ ሊነካ ነው!
የደሀው ልጅ - አዎ፣ ታድላችኋል እናንተ!
የሀብታሙ ልጅ - እናንተ ለምን እንደኛ ፎቅ  አትሰሩም?
የደሀው ልጅ - እኔንጃ!
የሀብታሙ ልጅ - ገንዘብ የላችሁም?
የደሀው ልጅ - እኔ እንጃ፡፡ ቆይ አባቴን እጠይቃለሁ፡፡
የሀብታሙ ልጅ - የእኔ አባት ወፍራም ነው
የደሀው ልጅ - የእኔ አባት ግን በጣም ቀጭን ነው
የሀብታሙ ልጅ - ለምንድነው አባትህ የከሱት? ምግብ አትበሉም እንዴ?
የደሀው ልጅ - ኧረ እንበላለን፡፡ ግን እንጃ አባቴ ቀጭን ነው፡፡
የሀብታሙ ልጅ - ታዲያ ለምን ከሱ?
የደሀው ልጅ - እኔንጃ ቆይ እቤት ስደርስ እጠይቀዋለሁ፡፡
እኒህ ልጆች ሁሌ እንዲህ እንዲህ እያወሩ ት/ቤት ይሄዳሉ፡፡ በኋላም ተመልሰው ወደቤት ሲሄዱ እንደዚሁ እያወሩ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡
ደሀው ልጅ ቤት ሲደርስ ለአባቱ፡-
“አባዬ?”
“ወይ ልጄ?”
“ጓደኛዬ ሁል ቀን እኛ ትልቅ የግንብ ፎቅ ቤት ነው ያለን፡፡ እናንተ ግን ጭቃ ቤት ነው ያላችሁ፡፡ ደሞ ያንተ አባት ቀጭን ናቸው፡፡ የእኔ አባት ግን ወፍራም ናቸው ይለኛል፡፡ በጣም ያበሽቀኛል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ አባባ?”
አባትየውም፣
“አይዞህ ልጄ፡፡ አየህ እነሱ ያን የሚያክል ፎቅ የገነቡት ገንዘብ ከባንክ ተበድረው ነው። እኛ በራሳችን ነው የሰራነው፡፡ ስለውፍረትም ያልከው፤ ማን ያውቃል? የወፈረ ሁሉ ጤነኛ፣ የከሳ ሁሉ በሽተኛ አይምሰልህ፡፡ “ዕዳ የሌለበትን ድህነት እና በሽታ የሌለበትን ክሳት የሚያህል ነገር የለም!” አለው፡፡
                                         *           *              *
“La v’ertit‘e est de la buche des enfants” ይላሉ ፈረንሳዮች፡፡ ዕውነት ያለው ህፃናት አፍ ውስጥ ነው፤ ማለታቸው ነው፡፡ ህፃናቱ የሚያዩትን የተጨበጠ ዕውነት አወሩ፡፡ ውስጡ ያለውን ሚስጥር አባቶቹ ያውቃሉ፡፡ ላይ ላዩን ትላልቅ የሚመስል፣ ላይ ላዩን ያሸበረቀ የሚመስል፣ ውስጡ ሲታይ ግን በሙስና የተሞላ አያሌ ሀብት በሀገራችን ይታያል፡፡ እስኪታወቅ እንጂ አንድ ቀን ህዝብ ያወቀ የጠየቀ ዕለት ለውርደት መዳረግ አይቀሬ ነው፡፡
ሙያው ሌላ፣ ሀብቱ ሌላ የሆነ አያሌ ሰው አለ፡፡ ከስውር ምዝበራ ወደግልፅ ሌብነት የተሸጋገረ ዐይን-አውጣ ሙስና አሳሳቢ የሀገር ድቀትን ማምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከግለሰብ ሙስና ወደ ቡድን ሙስና፣ ከቡድን ሙስና ወደ ድርጅታዊ/ተቋማዊ ሙስና፣  እየተሸጋገረ ያለ ሙስና በዚያው በትራንስፎርሜሽን ንፍቀ-ክበብ ውስጥ የታቀፈ በመሆኑ በቀላሉ የማይመነጠር የአረም እሾክ ነው፡፡ ዱሮ “በቀይ ካባ ስውር ዳባ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ይሰውረን! ከሁሉም በላይ ደግሞ A Law - maker is a law – breaker (አጥር - አጣሪ አጥር - ሰባሪ እንዲሉ) ሲሆን አሳሳቢ ነው፡፡ Who guard the guards ጠባቂዎቹንስ ማን ይጠብቃቸዋል? እንዲሉ ፈረንጆች፤ ይሄም አሳሳቢ ጉዳይ ነው! ከዚህም ይሰውረን፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት የ2014 ዓ.ም ሪፖርት “ለአፍሪካ የትራንስፎርሜሽን ዕድገት ኢንቨስትመንትን ማጫጫር” በሚለው ፅሁፍ፡-
“ኢንቨስትመንት የረዥም ጊዜን ዕድገትና ልማትን የሚሾፍር ዋና አቅም ነው፡፡ ምርታዊ አቅምን ይገነባል፡፡ ኢኮኖሚ መዋቅርን በሥር-ነቀል መልክ ይለውጣል፡፡ ሥራ የማስያዝ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ድህነትን ይቀንሳል” ይልና፤ ሆኖም የአህጉሩ አማካይ የኢንቨስትመንት መጠን አሁንም እንደዚያው ዝቅ እንዳለ በመሆኑ የሀገራዊ ልማት ግቡን ለመምታት የሚያስችለውን ያህል ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ከቀጠለ የአፍሪካ ቅርብ ጊዜ ልማት ተሰባሪ ነው፣ ሸውሸዌ (fragile) ነው” ይላል፡፡ የጉዳዩ አንኳርም ሀገራዊና ዓለምአቀፍ ፖሊሲን ማጣጣም ነው፤ ብሎ ይደመድመዋል፡፡ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕውቀት ባለቤቶች በአግባቡ የመጠቀምን እስትራቴጂ ስራዬ ብሎ፣ ይሆነኝ ብሎ መያዝ ብልህነት ነው፡፡ አለበለዚያ ኢኮኖሚያችን እንኳን ዘላቂ ሊሆን ለእለቱም ተሰባሪ ነው የሚሆነው፡፡
ጥቂት ከበርቴዎች በባንክ ብድር የሚገነቡዋቸው ህንፃዎች ብድራቸውን ለመመለስ የማይችሉበት አረንቋ ውስጥ ገብተው ውስጡን ለቄስ መሆናቸውን ባንክ ከሚያወጣቸው ጨረታዎች ለመገንዘብ ዐይንን ማሸት አያስፈልግም፡፡ የሚያማምሩ መኖሪያ ቤቶች፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ ሰፊ ቦታ ላይ ተንጣለው የተንሰራፉ ግን ያላለቁ የግንባታ ግቢዎች የአስደንጋጭ ዕዳ ባለቤቶች መሆናቸው፤ አልፎ ተርፎም ሙስና ውስጥ የተዘፈቁት ሲጋለጡ ሲታይ እጅግ አሳዛኝ አገር ውስጥ እንደምንኖር እንገነዘባለን፡፡ አንዱ በላቡ ለመኖር ይፍጨረጨራል፤ ሌላው “በጥበቡ” ገንዘብ እየመዘበረ ፎቅ ይሰራል፡፡ ሁለቱም ዜጋ ይባላሉ! ዞሮ ዞሮ ሙስና መጋለጡ ስለማይቀር ጤና ይነሳል! ከዚህ ይሰውረን፡፡ “ዕዳ የሌለበትን ድህነት እና በሽታ የሌለበትን ክሳት የሚያህል ነገር የለም!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡


Read 7670 times