Saturday, 16 August 2014 10:31

ኢቦላ ኢትዮጵያ ከገባ ለማከም ሆስፒታል ተዘጋጅቷል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች ሊስፋፋ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን የኢቦላ በሽታ በበቂ ደረጃ ለመከላከል  ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለፀው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ እስካሁን በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ባይገባም አዲስ እየተገነባ ባለው የኮተቤ ሆስፒታል 10 አልጋዎች ያሉት የህክምና ክፍል ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ሰሞኑን ከናይጄሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሁለት ቻይናውያን ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በተደረገላቸው የጤና ፍተሻ በበሽታው ተጠርጥረው አዲስ አበባ በሚገኘው ኮርያ ሆስፒታል ሲታከሙ የሰነበቱ ሲሆን ህመማቸው ወባ ሆኖ በመገኘቱ አስፈላጊው ህክምና ተደርጐላቸው ከትናንት በስቲያ ከሆስፒታል መውጣታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተ ብርሃን ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ አራት ሃገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በንቃት እየተከታተለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚሁ ሲባል ሁለት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሌት ተቀን እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በዶ/ር ከሰተ ብርሃን የሚመራውና የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርንና የመከላከያ ሚኒስቴርን ያካተተው ኮሚቴ፤ በሽታው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የመከላከል ስራ የሚያከናውን ሲሆን በበሽታው ዙሪያ ለባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡ እስካሁን 275 የጤና ባለሙያዎች ስለ በሽታው ስልጠና እንደተሰጣቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ የክልል የጤና ቢሮ ሃላፊዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉንና ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የምርመራ ስራዎችን የሚያከናውን ኮማንድ ፖስት መቋቋሙንና በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚሠሩ 20 ያህል በጐ ፈቃደኛ ዶክተሮች የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አክለው ገልፀዋል፡፡
ከ500 በላይ መንገደኞች በየቀኑ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በአውሮፕላን ማረፊያው ከሚደረገው ክትትል ባሻገር በድንበር አካባቢም ቅኝቱ መጠናከሩን አስታውቀዋል፡፡ በሽታው ድንገት ቢያጋጥም በሚልም 95 በመቶ ግንባታው በተጠናቀቀው የኮተቤ ሆስፒታል 10 አልጋዎች ያሉት ልዩ የህክምና ክፍል ከባለሙያዎች ጋር መዘጋጀቱን በቅርቡም የአልጋ ቁጥሩ ወደ 50 ከፍ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ በሽታው ከተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ ሃገሮች አንዷ በሆነችው በናይጄሪያ ሌጎስ አራተኛው ሰው በቫይረሱ መያዙን ተከትሎ በነዳጅ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ አለማቀፍ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን እስከመበተንና ኩባንያዎች እስከ መዘጋት መድረሳቸው ታውቋል፡፡ በሴራሊዮን 32 ነርሶች መሞታቸውን የጠቆመው የዓለም የጤና ድርጅት፤ በምዕራብ አፍሪካ የበሽታውን መስፋፋት ለመከላከል በመንግስታት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ጠቁሞ በሽታው እየተስፋፋ ስለሆነ፤ ተጨማሪ ክትትልና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ናይጄሪያ በበሽታው የተጠቁ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ሲሆኑ የኬንያ አየር መንገድ ወደነዚህ ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው በረራ በየቀኑ የሚያደርግ መሆኑን ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ኬንያን ለበሽታው በአደገኛ ሁኔታ የተጋለጠች ሲል ፈርጇታል፡፡ የኮርያ አየር መንገድ ወደ ኬንያ የሚያደርገውን ማንኛውንም በረራ እንደሰረዘ ታውቋል፡፡

Read 2910 times