Saturday, 16 August 2014 10:29

በምስራቅ አፍሪካ ከ14 ሚ. በላይ ህዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  በምስራቅ አፍሪካ አገራት በተከሰተው የዝናብ እጥረትና የእርስበርስ ግጭቶች ሳቢያ የምግብ እጥረት መፈጠሩን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤  በቀጠናው ከ14 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር የምስራቅ አፍሪካ ቃል አቀባይ ማቲው ኮንዌይን ጠቅሶ የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ በቀጠናው የሚታየው የምግብ እጥረት ችግር እየከፋ የመጣ ሲሆን በዘጠኝ አገራት የሚገኙ 14 ነጥብ 4 ሚሊዮን አፍሪካውያን የምግብ እርዳታ ካላገኙ የከፋ ችግር ይደርሳል ብሏል፡፡
የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ህዝቦች አብዛኞቹ የሚኖሩት በጦርነት በመታመስ ላይ ባለችው ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ውስጥ እንደሆነ የጠቆመው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚመታው የኬንያ ሰሜናዊ ክፍልም የችግሩ ተጠቂ እንደሆነ አመልክቷል፡፡በሱዳን 5 ሚሊዮን፣ በደቡብ ሱዳን 3.5 ሚሊዮን በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ በጅቡቲ 120ሺ ያህል ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡
ከሶስት አመት በፊት በአካባቢው ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት የኦክስፋም ሪጅናል ዳይሬክተር ፍራን ኢኩኢዛ በበኩላቸው፤ በወቅቱ ከደረሰው ጥፋት በመማር በአፋጣኝ ለችግሩ ምላሽ መስጠት ከተቻለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት መታደግና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትንም ከረሃብ ስቃይ  ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

Read 2012 times