Saturday, 16 August 2014 10:21

ኢሬቴድ በመጪው አመት 4 የቴሌቪዥንና 2 የሬዲዮ አዳዲስ ድራማዎች አቀርባለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተካተቱበት ገምጋሚ ካውንስል ተቋቁሟል

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአዲሱ ዓመት ዓ.ም 4 አዳዲስ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችና 2 የሬዲዮ ድራማዎች እንደሚያቀርብ የገለፀ ሲሆን አዳዲስ ድራማዎችን በዘርፉ ባለሙያዎች በተዋቀረ ካውንስል እያስገመገመ እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡
የታላላቅ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትን ልምድ በመቅሰም ከእንግዲህ በኋላ በቴሌቪዥንም ሆነ በሬዲዮ የሚቀርቡ ድራማዎች ለዚሁ ተግባር በተቋቋመው የፊልምና ድራማ ገምጋሚ ካውንስል ይገመገማሉ ያሉት በድርጅቱ የመዝናኛና ስፖርት የስራ ሂደት መሪ አቶ ታከለ ኮይራ፤ ካውንስሉን እንዲመሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ጽሑፍ ት/ቤት ዲን አቶ ነብዩ ባዩ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት አለሙ እና አቶ አቦነህ አሻግሬ መመረጣቸውን ገልፀዋል፡፡
የገምጋሚ ካውንስሉ ዋነኛ ተግባር አድማጭና ተመልካቹን የሚመጥኑ ድራማዎችን መገምገም፣ መምረጥ እና መከታተል ሲሆን ይሄም በሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚቀርቡ የጥበብ ስራዎች ይበልጥ አስተማሪና አዝናኝ እንዲሁም ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሏል፡፡
አዲሱ ገምጋሚ ካውንስል በዛሬው እለት ወደ 70 ለሚደርሱ የድራማና ፊልም ሰሪዎች በሚዲያ ተቋሙ በሚቀርቡ የጥበብ ስራዎች ዙሪያ ውይይትና ገለፃ እንደሚያደርግና ስልጠና እንደሚሰጥ የታወቀ ሲሆን ስልጠናው ለተወዳዳሪዎች ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አቶ ነብዩ ባዩ ገልፀዋል፡፡
የጥበብ ስራዎች መመዘኛን በተመለከተ ጠንከር ያለ አዲስ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች፤ ከእንግዲህ ድራማ ለማቅረብ ግለሰቦች ሳይሆኑ ኩባንያዎች ብቻ እንዲወዳደሩ ይደረጋል የመረጣው ሂደትም ሙያዊ ይሆናል ብለዋል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ተካሂዶ የነበረው ጨረታ መሠረዙን የጠቆሙት ሃላፊዎቹ፤ ወደፊት የሚወጣውን ጨረታ ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ እንሠራለን፤ የመምረጫ መስፈርቱንም ከመጀመሪያው አንስቶ ግልጽ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ይበልጥ ግልጽነትን በማስፈንም አሸናፊው ያሸነፈበት ምክንያት ተሸናፊውም የተሸነፈበት ምክንያት በግልፅ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ከነሐሴ 15 እስከ መስከረም 15 ድረስ ለማሳያ በሚሆን ፕሮዳክሽን የታገዘ ፕሮፖዛል ከተወዳዳሪዎች እንደሚቀበል የገለፁት የድርጅቱ የኮሙኒኬሽንና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረ አምላክ ተካ፤ ከመስከረም 16-30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ካውንስሉ ግምገማውን ጨርሶ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ አሸናፊዎች ይፋ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ ህዳር 1 የተመረጡት አዳዲስ ስራዎች ለህዝብ መቅረብ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ገብረአምላክ ገልፀዋል፡፡

Read 2925 times