Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 December 2011 11:31

የሸራተኑ ምሽት - በአቶ በረከት መጽሐፍ ምርቃት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

- አቶ በረከትና ሼኽ መሐመድ አሊ አልአሙዲ የተደናነቁበት ምሽት

- አቶ መለስ፣ ኢሕአዴግና አልአሙዲ ተወድሰዋል

- ኢሕአዴግ “የሕዝብ ፍቅር ያለው ፓርቲ” ተብሏል

- በመጽሐፉ ተቃዋሚዎች ክፉኛ ተተችተዋል - በተለይ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

የኢሕአዴግ ነባር ታጋይ፣ የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስቴር፤ አሁን ደግሞ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም በምርጫ 97 ጉልህ ስፍራ የነበራቸው አቶ በረከት ስምኦን ጻፉት የተባለውን መጽሐፍ ለማንበብ በጉጉት ስጠባበቅ ነበር፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ለመታደም ወደ ሸራተን አዲስ ሆቴል ያመራሁትም ከዚህ ጉጉት በመነጨ ስሜት ነው፡፡  የአቶ በረከት መጽሐፍ የምረቃ ሥነ ሥርዐት የሚካሄደው ሸራተን ሆቴል ካሉት አዳራሾች በጣም ሰፊው እንደሆነ በሚነገርለት “ላሊበላ” አዳራሽ እንደሆነ የጥሪ ካርዱ ላይ ስለተጠቆመ ወደዚያው አመራሁ፡፡ አዳራሹ በሰዎች ተጨናንቋል፡፡ ደራሲዎች፣ ድምፃውያን፣ ቲያትረኞች፣ የፊልም አክተሮች፣ ሰዓሊያን፣ የማስታወቂያ ባለሞያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ባለሃብቶች፣ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እና ሌሎች ተጋባዦች አዳራሹን ሞልተውታል፡፡  አዳራሹ በርካታ ሰዎችን እንዲይዝ ታስቦ ይመስላል መቀመጫዎቹ በሙሉ ተነስተው እድምተኛው ቆሞ የዝግጅቱን መጀመር ይጠባበቃል፡፡ የሸራተን አስተናጋጆችም በፈገግታ  ተሞልተው መጠጥ ለታዳሚው ለማስተናገድ ይዘዋወራሉ፡፡“በሸራተን ምን ጠፍቶ” በሚያስብል ሁኔታ ተበልቶ አይደለም ተደፍቶ የማያልቅ ምግብም ተዘጋጅቷል፡፡  በአጠቃላይ ድግሱ እጅግ የተዋጣለት የሚባል ነው - የአቶ በረከት መጽሐፍ ምርቃት፡፡ የአቶ በረከት የመጽሐፍ ምርቃት ዝግጅት የአንዲት ነባር ታጋይ የመጽሐፍ ምርቃት ዝግጅትን አስታውሶኛል፡፡ ነባር ታጋይና የአቶ ገብሩ አስራት ባለቤት የሆኑት የወ/ሮ የውብማር አስፋው የመጽሐፍ ምርቃት፡፡ ወ/ሮ የውብማር የሕወሓት ሴት ታጋዮችን የትጥቅ ትግል ታሪክ የሚተርክ “ፊንክስዋ ሞታም ትነሳለች” የተባለ መጽሐፋቸውን ያስመረቁት በኢምፔሪያል  ሆቴል ነበር፡፡ ያኔ ግን እንዲህ ሞልቶ የተረፈ ሰው አላየሁም፡፡ እንዲህ ሞልቶ የተረፈ ምግብ እና መጠጥም አልነበረም፡፡ በእርግጥ ነባር ታጋይዋ ስልጣን ላይ እንዳልነበሩ አውቃለሁ፡፡ መጽሃፉን ያሳተሙላቸው ሼክ መሐመድ አላሙዲም አልነበሩም፡፡ ከምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ የተጀመረው የምርቃት ሥነ ሥርዐቱ ፣አቶ በረከት ለቤተሰባቸው በተለይም ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ባደነቁት በመድረኩ መሪ አቶ ሴኮ  ቱሬ ነበሩ፡፡ በርካቶች በትወና ችሎታዋ የሚያደንቋት አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ በዘመናዊ ልብስ ተውባና ፊቷ እንደ ፀዳል አብርቶ ወደ መድረኩ ብቅ አለችና፤ በጣም ወደድኩት ያለችውን የአቶ በረከትን “መቼስ ምን እንላለን” የሚለውን ግጥም አነበበች፡፡  በኋላ ላይ በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ ግጥሙ ከመጽሐፉ የተቀነጨበ እንደሆነ ሲነገር ሰማሁ፡፡ አርቲስቷ ራሷ በምታቀርበው ሌላ የሬዲዮ ፕሮግራምም፤ “አቶ በረከትን ግጥሙን ለማቅረብ አስፈቀድኳቸው” ስትልም አደመጥኩ፡፡ “መቼስ ምን እንላለን” የሚለው የአቶ በረከት ግጥም ግን ጋብቻ ተከልክሎ በነበረበት የትጥቅ ትግል ወቅት አቶ በረከት በ33 ዓመታቸው በ1977 ዓ.ም በለስ ላይ ቁጭ ብለው ለአሁኗ ባለቤታቸው የጻፉት ነበር፡፡ ይኸው ግጥምም በወቅቱ የነበረው የታጋዮች ግጥም እና የፍቅር ደብዳቤዎች በኅዳር ወር በ1998 ዓ.ም ታትሞ በወጣበት “ሶረኔ” በተባለው መጽሐፍ ላይ ተካትቷል፡፡ አርቲስት ሐረገወይን አቶ በረከትን ማስፈቀድ አያስፈልጋትም ነበር፡፡ ሸገር እንዳለውም በአዲሱ የአቶ በረከት መጽሐፍ ውስጥ የተካተተ ግጥም አልነበረም፡፡

ሐረገወይን ግጥሙን ካቀረበች በኋላ የአቶ በረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘው መጽሐፍ ገጽ ተከፈተ፡፡ መድረክ መሪው አቶ ሴኮም የአርቲስቶቹን ስም ተራ በተራ እየጠራ “የወደድኩት፣ የሳበኝ፣ የመረጥኩት” ያሉት ነው በማለት እያስተዋወቀ ወደ መድረክ ጋበዛቸው፡፡ እነሱም የመጽሐፉን ገፆች እየገለጡ የሳባቸውን አነበቡ፡፡ አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ፣ አርቲስት እመቤት ወ/ገብርኤል፣ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም፣ አርቲስት ደበሽ ተመስገን፣ አርቲስት ባዩሽ አለማየሁ እና አርቲስት መሆኑን ባላውቅም የቀድሞው የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ እና የ”50 ሎሚ” ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ደግአረገ ነቃጥበብ በየተራ አነበቡ፡፡

ፕሮግራሙ ቀጠለ፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፤ ተመራማሪዎችና የተለያዩ ተቋማት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊና የልማት ተቋማት ላይ ለመመራመር እና የዳበረ ሐሳብ ለማምጣት የአቶ በረከት መጽሐፍ መነሻ ሊሆናቸው እንደሚችል እምነታቸው እንደሆነ ገለፁ፡፡

የመጽሐፉ፤ መታሰቢያነት ለትግሉ ባለቤቶች፣ ታጋዮች፣ የልጅነት ዕድሜያቸውን ለሰላምና ለዴሞክራሲ በተለይ በትግሉ ወቅት ላሳለፉት ታላቅ ከበሬታ የሰጠ እና ለማስታወስ ያለመ ነው አሉ - አቶ ደመቀ፡፡ እኔም ንግግሩን ተከትዬ መታሰቢያ የተጻፈበትን ገጽ ገለጥኩ “መታሰቢያነቱ ለወንድሜ ካሳሁን ገብረህይወት” ይሁንልኝ ብቻ ይላል፡፡ አቶ ደመቀ የገለጿቸው ታጋዮች በአቶ በረከት መጽሐፍ የቱ ጋር እንደተጠቀሱ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፡፡

ቀጠሉና አቶ በረከት ወደ መድረክ ወጡ፡፡ በምርጫ 97 ወቅት ዋና ተዋናይ ስለነበሩ ስለሁለቱ ምርጫዎች ለመጻፍ እንደማይበዛባቸው ገለፁ፡፡ ኢሕአዴግ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ባካሄደባቸው 10 ዓመታት የቀድሞዋ ኢትዮጵያ እየተናደች፣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተገነባች መሆኑንም አወሱ፡፡ “ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ባለችበት የልማት ጐዳና ቀጥላ ውጤታማ ለመሆን 30 እና 40 ዓመታት ያስፈልጋታልም” አሉ፡፡

ምርጫ 97ን በሚመለከት ተቃዋሚዎች ጊዜ ስለነበራቸው በወቅቱ ብዙ መጽሐፍትን   እንደጻፉ የጠቀሱት አቶ በረከት፤ በኢሕአዴግ ወገን ያለውን ለማያውቁ እውነታውን ለማካፈል ይጠቅማል በሚል እርሳቸው በተራቸው ይሄን መጽሐፍ መጻፋቸውን አብራሩ፡፡

ማንም ሰው በቀላሉ ዕድሉን የማያገኘውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዳይናሚክ እርሳቸው እንዲያውቁት እና ልምድ እንዲያገኙበት ዕድሉን የሰጣቸውን ኢሕአዴግን አመሰገኑ፡፡  “ኢሕአዴግ አስተዋይ እና አገሪቷን ከእንቅልፏ የቀሰቀሰ ድርጅት ነው” በማለትም ፓርቲያቸውን አሞካሹ፡፡

“መለስ ለእራሱ ከባድ ሥራ ወስዶ ለሰውም ከባድ ሥራ እየሰጠ የሚያሠራ መሪ ነው”  በማለት ሙገሳቸውን እና ምስጋናቸውን ለአቶ መለስም የቸሩት አቶ በረከት፤ ከምስጋናው ሁሉ ረጅሙን ሰዓት በወሰደባቸው በሼከ መሐመድ አልአሙዲን ምስጋና ውዳሴያቸዉን አጠናቀቁ፡፡

“የእኔ ሥራ መጽሐፉን መጻፍ ብቻ ነበር፡፡ የእኔን እና በቅርቡ የአቶ መዝሙር ፈንቴ (የባለቤታቸው ወንድም) የተረጐሙትን መጽሐፍ አልአሙዲ እንዲያሳትመው መመሪያ ብቻ ነው የሰጠሁት፡፡ ደወልኩ እና እነዚህን መጽሐፎች ታሳትማቸዋለህ አልኩት” በማለት መጽሐፉን ከኢትዮጵያ ውጪ ከማሳተም ጀምሮ እንዲያ ባለ በደመቀ ሥነ ሥርዐት እንዲመረቅ የማድረግ ወጪውን ሼኹ እንደሸፈኑ ገለፁ፡፡

እኔ ግን አቶ በረከትን አንድ ጥያቄ መጠየቅ ፈልጌ ነበር፡፡ “አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን አንድን ባለሃብት ደውሎ እንዲህ ያለውን ትእዛዝ መስጠት እና ተፈፃሚ ማድረግ ሙስና ነው አይደለም?” የሚል፡፡ ልብ አድርጉ ይሄ ጥያቄ ነው፡፡ የማላውቀውን ብጠይቅ ችግር ያለው ስላልመሰለኝ ነው፡፡ ግን ደግሞ አንድ ነገር አውቃለሁ፡፡ አቶ ስዬ በሙስና ተጠርጥረው በታሰሩበት ወቅት ከቀረቡባቸው ማስረጃዎች አንዱ፤ አንዱን የባንክ ሐላፊ ደረጃ ላይ አግኝተው ጀርባውን ቸብቸብ በማድረግ “ጐረምሳው ተባበረው” በማለት ለወንድማቸው ትብብር ጠይቀዋል የሚል ነበር፡፡ ምናልባት ሁለቱ አይገናኙም ልባል እችላለሁ፡፡ እውነትም ላይገናኝ ደሞ ይችላል፡፡

ቀጣዩ ንግግራቸው የሁለቱን ቅርበት የሚጠቁም ነበር - የአቶ በረከትንና የአልአሙዲን፡፡   “በምርጫ 97 ማግስት ከምርጫው ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ ህመም ገጥሞኝ ደቡብ አፍሪካ ለሕክምና በሄድኩ ጊዜ እዛ ድረስ መጥቶ ጠይቆኝ ነበር፡፡ የልብ ወዳጆች ነን፡፡ አሊ አልአሙዲ ወሬኛ ነው፡፡ ጨዋታ ይወዳል ውጭ አገርም ሄዶ ቢሆን ሦስት ቀን አያድርም፤ ይደውላል፤ ደውሎም ቀልድ አዋቂ ነው ተሳስቀን ነው የምንለያየው፡፡ አሊ አልአሙዲ ሣቅ እና ዕድሜህን ያብዛልህ” በማለት ምርቃቱን አዥጐደጐዱት፡፡

ጐንደር ልማት ማኅበር (ጐልማ) ሆስፒታል ማስገንባት በፈለገ ጊዜ አቶ በረከት የከተማዋ ተወላጅ በመሆናቸው እርዳታ እንዲሰጡ ሲጠየቁ አል አሙዲን ጋር ቀርበው 5 ሚሊዮን ብር መጠየቃቸውንና 50 ሚሊዮን ተደርጐ እንደተሰጣቸው፣ የደራሲያን ማኅበር የአፍሪካ ደራሲያንን በጋበዙ ጊዜ ሼኹ እርዳታ ማድረጋቸውን በመግለፅ “አላሙዲን ጠይቄው አሳፍሮኝ አያውቅም” በማለት የባለሃብቱና የእርሳቸውን ቅርበት የት ድረስ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የመጨረሻው ተራ የባለሃብቱ የሼክ ሙሐመድ ነበር -እሳቸውም ጨዋታውን ቀጠሉ፡፡ “አንዳንድ ሰዎች ኢሕአዴግን ትወዳለህ ይሉኛል፡፡ አዎ እወዳቸዋለሁ አራት ነጥብ፡፡ በምርጫ 97 ወቅት ከተሰደቡት ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፤ ሳይቸግረኝ የአረብ ሳተላይት አስገብቼ በየቀኑ ሰዎቹን እሰማቸው ነበር፤ በረከትም በሩን ብርግድ አድርጐ ሰጣቸው” አሉ ሼክ ሙሐመድ “በሩን ብርግድ …” ማለታቸው ቴሌቪዥኑን እና በምርጫ 97 የተደረገውን ክርክር ነበር፡፡ ለምርጫ ክርክር በሩን ከፍቶ መስጠት የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህርይ እንጂ የአቶ በረከት መልካም ፈቃድ እንዳልሆነ አላብራሩም፡፡

“ለምን እንደተሰደብኩ አላውቅም እኔን እንኳን አፌን አልከፈትኩም ነበር፡፡ ግን የንብ ቲሸርት ለብሼ ከአውሮፕላን ወረድኩ፡፡ አቶ መለስና አቶ በረከት እንኳን ለምን ሳታማክረን ለበስክ ብለው ተቆጥተውኝ ነበር፡፡ አላማክራችሁም አልኳቸው ምክኒያቱም ባማክራቸው እንዲህ አድርግ … እንዲህ አታድርግ ስለሚሉኝ ነበር ያላማከርኳቸው” በማለት የምርጫውን ወቅት ትዝታቸውን ለታዳሚው አወጉ፡፡

ስለ አቶ በረከት ቀጠሉ፤ “አቶ በረከት እንዳለው ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጠይቄዋለሁ፤  የጠየኩት ግን አመፀኛ እና ልውጣ ብሎ ስለሚያስቸግር ነው፡፡ ታከም፣ እረፍ ሲባል እሺ አይልም፡፡ እኔ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ መጀመሪያ ያደረኩት ክፍሉን በሴኪዩሪቲ ማስከበብ ነበር፡፡ እሱ ግን በኋላ የብአዴን 25ኛ ዓመት በዓል ላይ ካልተገኘሁ ብሎ አስቸገረ ቃል አስገብቼ ይዤው መጣሁ፡፡ በ48 ሰዓት ውስጥ አንጠልጥዬ መለስኩት፤ እኔን  የሚያሳስበኝ የጤናቸው ጉዳይ ነው፡፡” በማለት ሚስጥራቸውን አጫወቱን፡፡ ከዚህ ጨዋታቸው አልአሙዲ ለኢህአዴግ  ባለስልጣናት የጤና ጉዳይ እንደሚጨነቁ ተገነዘብኩ፡፡ በአቅም ማነስ ህክምና ሳያገኝ ጤናው የሚታወክ ባለስልጣን አይኖርም ብዬ ደስ አለኝ፡፡ የባለሥልጣናትን የጤና ጉዳይም ለባለሃብቱ ተውኩላቸው፡፡

ሼክ መሐመድ ቀጠሉ፤ “ከዋናው ሰውዬ ጀምሮ ወዳጆች ነን፤ ተግባብተን እና ተቻችለን ነው የምንኖረው፤ እኔ ግን አንድ ቀን እንዲህ ሆንኩ ብዬ ቅሬታ አቅርቤላቸው አላውቅም እንደውም እነሱ እንደኔ ሁሉንም የሚጭኑበት ሰው የለም” አሉ፡፡ እውነት ከሆነ ኢህአዴግ ምን ነካው ያስብላል፡፡ ወይስ ከባለሃብት ጋር መሞዳሞድ እንዳይመስልበት ፈርቶ ይሆን?

በመጨረሻም ሼኽ መሐመድ “እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ አብረን ነን” ሲሉ ማሉ፡፡ አቶ በረከትም በጭብጨባ መሐላውን አፀኑላቸው፡፡ ታዳሚውም አጨበጨበ፡፡ አጨብጭቦም ወደ ቤቱ አልሄደም፡፡ “ምን ጠፍቶ” የተባለለትን የሸራተንን ድግስ እስኪበቃው ተቋደሰ፡፡ የ”ሁለት ምርጫዎች ወግ” በወፍ በረር ቅኝት

የ”ሁለት ምርጫዎች ወግ” የሕትመት ደረጃውን የጠበቀ፣ 314 ገፆች ያሉት መጽሐፍ ነው፡፡ ጽሑፉ ያልተጨናነቀ፣ ዘርዘር ብሎ የተቀመጠና ለማንበብ ምቹ ነው፡፡ “የብራ መብረቁ የኤራትራ ወረራ” በሚል ርእስ የቀረበው የመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ፤ የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት አጀማመር እና አጨራረስን በ48 ገፆች ይተርካል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተጀመረው በኤርትራ መንግሥት በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ትንኮሳ መሆኑን በመጥቀስ፤ “የኢሳያስ መንግሥት ከጦርነት በስተቀር ለሰላም ፈፅሞ ዋጋ የማይሰጥ መሆኑ እየተረጋገጠ በሄደ ቁጥር ነገሮች ወደ ነበሩበት ለመመለስና ጦርነቱን በአጭር ለመቋጨት የሚያስችሉ ጠንከር ያሉ ወታደራዊ ርምጃዎችን ወደመውሰድ ተሸጋገርን” ይላሉ፡፡ ቀጠል አድርገው የመከላከያ ሠራዊቱ ባድመን ማስመለሱን ገልፀው በዚህም የኤርትራ መንግሥት ወደ ድርድር የመምጣት አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር አውስተው ወረድ ይሉና፤ “ይሁንና ዛላምበሳንም ነፃ ለማውጣት  የነበረንን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በፆሮና ግንባር የከፈትነው ሌላ ማጥቃት እንዳሰብነው ሳይሄድ በመቅረቱ የኢሳያስ የጦረኝነት ልክፍት እንደገና ማገርሸት ጀመረ” በማለት ጦርነቱ በኢሳያስ የጦረኝነት ልክፍት ግፊት ምክንያት መቀጠሉን እንዲሁም ጦርነቱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለ ውዝግብ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚያም ሲቀጥሉ፤ “ወደ ጦርነቱ መገባደጃ የአቋም ልዩነቶች እየተሸጋሸጉ ከሄዱ በኋላ ግን በአንድ በኩል ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ብለው ጦርነቱን ለማራዘም የሚፈልጉት የእነ አቶ ተወልደ ወልደማርያም እና አቶ ስየ አብርሃ ወገን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱ በአጭሩ ተቋጭቶ ፊታችንን ወደ አገራችን ልማትና የኢሕአዴግ ውስጣዊ ችግሮች ወደ መፍታት ማዞር አለብን የሚለውን የአቶ መለስ ዜናዊን ሐሳብ የሚጋሩ ወገኖች በለየለት የአቋም ልዩነት የሐሳብ ትግል ውስጥ ገቡ፡፡ አቶ ስየ በርከት ባሉ አጋጣሚዎች መሳሪያና ተተኳሽ ለመሸመት ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አካባቢ ይመላለስ የነበረ ይሁን እንጂ በኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው ልዩነት “ጦርነቱ የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ ኤርትራን ለማንበርከክና ከተቻለም አሰብን ቆርሰን ለማምጣት ልንቆጥበው የሚገባ ህይወትና ሃብት ሊኖር አይገባም” የሚለውን አቋሙን ለማራመድ እና በዚህ አቋሙ የተቧደነ አንጃ ለመፍጠር የሚሆን ከበቂ በላይ ጊዜ ግን ነበረው፡፡” በማለት እርሳቸዉ አስቀድመው “ጦረኛ” ያሏቸውን የኢሳያስ መንግሥትን እስከመጨረሻው እንዋጋ የሚል ሐሳብ እንደነበራቸው በተዘዋዋሪ ያረጋገጡልንን እነ አቶ ስየን የጦረኝነት አስተሳሰብ ያላቸው በማለት ይተቿቸዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን መሬት መውረሩን፣ ፀረ ሰላም መሆኑን፣ ጦረኛ አስተሳሰብ ያለው መሆኑን ያልካዱት አቶ በረከት፤ ይህን ኃይል እስከ መጨረሻው ሄደን እንዉጋው ያለውን ቡድን ግን “የጦረኝነት አስተሳሰብ ያለው፤ ጀብደኝነት የተጠናወተው” ማለታቸው እርስ በርሱ የሚጣረስ ሆኖብኛል፡፡   “የኢሳያስ መንግሥት መሸነፉን ሲያውቅ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለነበሩት ኮፊ አናን በእኩለ ሌሊት ደውለው የሰላም አማራጭ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን በማሳወቃቸው ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ መቆሙን ያወሱት አቶ በረከት፤    ከጦርነቱ በኋላ ያለውን ጊዜ ኢሕአዴግ ከጥገኛ ዝቅጠት ወጥቶ ወደ ተሃድሶ የገባበት የሽግግር ወቅት እንደነበር በመጠቆም የምርጫ 97 ወጋቸውን ቀጥለዋል፡፡  የአቶ በረከት የምርጫ 97 ወግ በሚጀምርባቸው የመጀመሪያ ገፆች “የቀለም አብዮት” ያሉትን የምርጫ 97 ተቃውሞ “ለብዙ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያው የቀለም አብዮት ጠንሳሽ ቅንጅት የሚመስላቸው ቢሆንም፣ የየፓርቲዎቹን ፈለግ ለተከተለ ሁሉ የመጀመሪያው የአመፅ ስትራተጂ ቀያሽ ሕብረት እንደነበር ለመገንዘብ አያዳግትም” በማለት ሕብረትን በመተቸት ይጀምራሉ፡፡

“ቅንጅት” እና “ሕብረት”ን እንደ ፓርቲ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ፣  ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ኢንጅነር ግዛቸው እንዲሁም አንዴ ወጋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወዳጅ በሚመስል ሁኔታ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል እና አቶ ልደቱ አያሌውን እና ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን የአውሮፓ ሕብረት አመራርን እና የአውሮፓ ሕብረት አመራርን እና የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ አና ጎሜዝን በጠንካራ ትችት የሚያነሳው መጽሐፍ፤ በምርጫ 97 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕግ ጥሰው ሕዝቡን ለዐመፅ የቀሰቀሱ፣ የማይረቡ፣ ሥልጣን የተጠሙ፣ አገሪቷን የማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት ያለሙ፣ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ እንደሆኑ በመግለፅ ክፉኛ ይተቻቸዋል፡፡ አቶ በረከት በወቅቱ የነበረ ሂደት ነው ያሉትን ሲተርኩ፤ ኢሕአዴግ ሰላማዊ ፓርቲ እንደሆነ እና ምርጫው ሁለት ዓመት እስኪቀረው ጊዜ ድረስ የተሃድሶ ወቅት ላይ በመሆኑ የምርጫ ስራ ካለመሥራቱ ውጪ ፓርቲውን “የመላእክት” ያህል ንፁህ፣ ሕዝቡን ወዳድ የምርጫውን ውጤት በሰላም የተቀበለ ፓርቲ አድርገው ስለውታል፡፡ ከምርጫ 97 በፊት ያለውን ሁለት ዓመት እና ከምርጫ 97 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስም በሚገባ በመሥራቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተወደደደ እና የተፈቀረ ፓርቲ በመሆኑ ሕዝብ መርጦት ሥልጣን ላይ መውጣቱን ተርከዋል፡፡

በመጽሐፉ ምዕራፍ ሦስት ላይ፤ በምርጫ 97 ግንቦት ሰባት ምርጫው ሳይጠናቀቅ ኢንጀነር ኃይሉ  ሻውል ድርጅታቸው በአዲስ አበባ ምርጫ እንዳሸነፈ ነገር ግን ኢሕአዴግ ምርጫውን እንዳጭበረበረ መግለፃቸውን ከባድ ድፍረት በማለት ይተቹና፤ “ድምፅ የመስጠቱ ሂደት እንደተጠናቀቀ አቶ መለስ እሁድ ምሽት በቴሌቭዥን ቀርቦ ምርጫው በጥሩ አኳኋን እንደተካሔደ ከገለፀ በኋላ የተጋጋለው ስሜት እንዲበርድ እና ሕዝቡ የምርጫውን ውጤት በሰከነ አእምሮ አመዛዝኖ እንዲቀበለው ለማድረግ በማሰብ መንግሥት ለአንድ ወር ሰላማዊ ሰልፍ እንዲታገድ መወሰኑን አስታወቀ” ከማለት ውጪ አቶ መለስ በቴሌቪዥን ቀርበው ኢሕአዴግ ምርጫውን ማሸነፉን ስለመናገራቸው አንድም ቦታ አይጠቅስም፤ እሳቸዉንም አይወቅስም፡፡

አቶ በረከት ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋርም ሆነ ከአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ጋር የነበራቸውን ውይይት ሲጠቅሱ፤ “አስጠነቀቅናቸው፣ በወንጀል እንደሚጠየቁ ነገርናቸው፣ ጠንከር ያለ ስምምነት እንዲፈርሙ አደረግናቸው” የሚሉ የድርድር ሳይሆን የኢሕአዴግን የበላይነት የሚያሳይ የማስፈራራት ሂደት እንደነበር የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ የሚጨክነው የአቶ በረከት መጽሐፍ፤ “ከንቲባነትን በቆረጣ” በሚል በተቸበት ርእስ ስር ከምርጫ 97 በኋላ ያለውን ሂደት፤ “ለዶ/ር ብርሃኑ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛው የከንቲባነት መንበሩን መቆናጠጥ ስለነበር፣ ለእርሱ ቅንጅትም ሆነ ቀስተ ደመና፣ መኢአድም ሆነ ኢዴፓ የቼዝ ጠጠሮች ናቸው፡፡ በእንያንዳንዱ እርምጃው እንደ አመቺነቱ በተናጠል ወይም በቡድን የላቀ ችሎታ ባለው ኃይል ፊት ያጋፍጣቸዋል፡፡ ሲፈልግ ሰድቦ ለሰዳቢ ይሰጣቸዋል፡፡ ኢንጂነር ኃይሉን የሚፈልጋቸው ተሸክመው ወደ መንበረ ከንቲባነቱ እንዲያመጡት ስለነበር በአንድ በኩል እየተለማመነ፣ በሌላ በኩል ግን ገንዘብና መረጃ እየሰጠ በሚያሰማራቸው “ቤዛ”ን በመሳሰሉ የግል ጋዜጦች ይሰድባቸዋል፡፡ የቅንጅት ሚስጥሮች፤ በተለይም ኢንጂነር ኃይሉን የሚመለከቱና በየጋዜጠው ይወጡ የነበሩ ውስጣዊ መረጃዎች ከዶክተር ብርሃኑ የሚፈልቁ እንደነበሩ በአንድ አጋጣሚ ያገኘሁትና ዶ/ር ብርሃኑ እንዲህ ብለህ ጻፍ እያለ መረጃ፣ ምክርም ገንዘብ ይሰጠው እንደነበር ያጫወተኝ በግል ጋዜጣ ውስጥ ይሠራ የነበረ ጋዜጠኛ ነው” ይላል፡፡

እዚህ ጋር ግን መረጃ ተጣርሷል፡፡ አቶ በረከት ዶ/ር ብርሃኑ “ቤዛ”ን በመሳሰሉ ጋዜጦች ላይ ያጽፍ ነበር ያሉት ከምርጫው በኋላ ባለው ወቅት ሲሆን የጠቀሱት “ቤዛ” ጋዜጣ የተዘጋው ግን በሚያዝያ ወር 1992 ዓ.ም ነበር፡፡ በተጨማሪም አቶ በረከት አንድ ጋዜጠኛ ነገረኝ በሚል የ2002 ምርጫ ሁኔታን በጻፉበት ምዕራፍም፤ “አዲስ ነገር”  ጋዜጣ በቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ እርዳታ በአሜሪካ ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ መቋቋሙን ገልፀው ይህንንም “በግሉ ፕሬስ ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ናቸው የነገሩኝ” በማለት ጽፈዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለመጻፍ በማስረጃ ላይ የተደገፈ እርግጠኝነት የሚያስፈልግ ሲሆን ጋዜጠኞች ነገሩኝ በማለት ብቻ እንዲህ እያሉ መጻፍ ትዝብት ውስጥ የሚጥል ጉዳይ ይመስለኛል - ያውም ከአንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን፡፡  በመጨረሻም መጽሐፉ በአቀራረቡ፣ በአተራረኩ እና በታሪክ አወራረዱ የአቶ በረከትን የመጻፍ ችሎታ የማያሳማ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይዘቱ ምንም ሆነ ምንም መጽሐፍ መጻፋቸው በራሱ ሌሎች እንዲጽፉ የሚገፋፋ፣ በጽሑፉ ላይ እንዲወያዩ እና ወደ እውነት እንዲጠጉ በር የሚከፍት በመሆኑ አቶ በረከት “የሁለቱ ምርጫዎች ወግ”ን  በመጻፋቸው ሊመሰገኑ ይገባል እላለሁ፡ በተረፈ ያነበቡት ደግሞ ሐሳባቸውን ቢያጋሩ ለመማማር ይጠቅመናል ይበረታታልም፡፡

 

 

 

 

 

Read 16860 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 15:30