Saturday, 09 August 2014 11:30

ኤልያስ! - ሰው ማስደንገጥ ደግ ይመስልሃል!?

Written by  ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
Rate this item
(1 Vote)

          በወዲያኛው ሳምንት የአዲስ አድማስ ዕትምን የውስጥ ገፅ ሳነብ፣ ሁለቱን ጣቶቼን ቀስሬ “ቪቫ ኢሕአዴግ!” ለማለት ትንሽ ሲቀረኝ ነው የ “ፖለቲካ በፈገግታ” ዓምድ መሆኑን የተገነዘብሁ፡፡
ወንድሜ ኤልያስ! - በምናቤ ከምስልህ በስተቀር እስካሁን በአካል አንተዋወቅም፡፡ ለማንኛውም ግን “ሰበር ዜና!” ብለህ ያቀረብከው ጽሑፍ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችንም ጭምር ለጥቂት ሰኮንዶች ደንገጥ አድርጐናል፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ የጽሑፍህ ይዘት ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በመቅረቡና በሳልም ስለሆነ፣ በበኩሌ ወድጄዋለሁ፡፡ በጽሑፍህ ውስጥ የጠቃቀስካቸው ጉዳዮች ውለው አድረው የማይቀሩና የሚመጡ ቢሆኑም፣ ለጊዜው ግን አንቱ እንዳልከው ህልም ናቸው፡፡
መቸም ሰው ሁሉ ይመኛል፡፡ እኔም እመኛለሁ፡፡ ምኞት አይከለከል ነገር ነው! “If wishes were horses, beggars would ride” ይላሉ፣ እንግሊዛዊያን፡፡ ሁላችንም እንዲያ ሆነናል፡፡
ሁኔታዎች ረጋ ብለው በሰከነ መንገድ ይለወጣሉ። የሆነ - ነገር ግን የማይመስሉ ነገሮች ሁሉ ውለው አድረው መታየት ይጀምራሉ፡፡ ለምንም ጉዳይ የማይቸኩለው “ታጋሹ” ኢሕአዴግ መንግሥታችን፤ ይሄ በየጥጋጥጉ ሲያማው የነበረውን “ወሬኛ” ሁሉ ድንገት ሳያስበው ኩም ያደርገዋል፡፡ ሃሜተኛ ደግሞ እንዲህ ሃፍረቱን በስተመጨረሻ መከናነብ ያውቅበታል፡፡ ወትሮስ ተግባር እንጂ ሃሜትና ወሬ ከምን ሲያደርስ ታይቶ ይታወቃል? ምላስ ብቻ!?...ከዚህ ጋር ይሄዳል ብዬ ስላሰብሁ፤ እስቲ ቆየት ካለች ግጥሜ ውስጥ ጥቂት ስንኞች ላስነብባችሁና እኔም ወደ ጨዋታዬ ልግባ፡፡
ሥጋ ሞልቶ በየዓይነቱ፣
ዓቅም አንሶኝ የመግዛቱ፣
ታላቅ ታናሽ አጥቼ፣
ምላስ ብቻ በልቼ፣
አልጠና አለኝ ወገቤ፣
ይኸው ሆኖ ቀለቤ፡፡…
(ጥር 1986)
ወትሮም ቢሆን ተፈላጊው ዕውቀት ሳይኖራቸውና አንድን ነገር ፈጥነው ሊረዱ የማይችሉ ሰዎች እንዲያው በደመ ነፍስ ብቻ እየተነሱ ከህዝብ መካከል የፖለቲካ አዛዥ እየሆኑ በገቡ ጊዜ ብዙ ጥፋት ይደርሳል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮምያ ወረዳዎች ውስጥ የምትኖር አንዲት የገጠር ሴት፣ በአቅራቢያዋ ወደሚገኘው አነስተኛ የመንደር ገበያ ልትሸጠው የሰፋችውን የእንጀራ ማውጫ ሰፌድ እንዳትሸጥ ከመንገዷ ላይ ሆነው ጠብቀው ያስቆሟታል፡፡
“ለከተሜው በርካሽ ዋጋ መሸጥ አትችይም…” እያሉ፣ ሰፌዷን በፈለገችው ዋጋ እንዳትሸጥና ወደ ዩኒየን ገብቶ በውድ እንደሚሸጡላት ተነግሯት፣ እነሱ የወሰኑላትን ገንዘብ ሰጥተዋት ትሸጣለች፡፡ ይኸ በጣም ትንሹ ጉዳይ ነው፡፡ ገበሬውና ሸማቹ እንዳይገናኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ የበርሊን ግንብ ተገንብቷል፡፡
ሰዎች፣ “የእህል ኬላ” ይሉታል - ይህን የአምራቾች ዩኒየን እያሉ የሚጠሩትን ተቋም፡፡ የመንደር ካድሬዎቹ አርሶ አደሩን “ጡት ላጥባህ” ማለት ነው የሚቀራቸው፡፡ ነገረ ሥራቸው ግን ሌላ ነው፡፡ ብቻ እነዚያ ሰዎች፣ አርሶ አደሩን የፈለጉት የምርጫ ወቅት ሲመጣ ለድምፁ ብለው ይሁን ለሌላ ጉዳይ፣ ብቻ ሳያውቁት በጭንቅላታቸው ሳይሆን በደመ ነፍሳቸው የገበያውን ሥርዓት እንዳለ ምስቅልቅሉን አወጡት። የማዳበሪያው ጫና ተጨምሮበት እህልና ጥራጥሬ ተወደደ፡፡ በላተኛውም አማረረ፡፡ መቸውንም ጠግቦለት የማያውቀውን ሆዱን ማከክ ጀመረ፡፡
“…ታዲያ ይህ ሁሉ ምስቅልቅል መፈጠሩን ገዥው ፓርቲ “አልሰማ” ኖሯል ለካ - ነገሩ ከጆሮው ሲደርስ አስቸኳይና የማያዳግም እርምጃ በአባላቱ ላይ እንዲወሰድ በማዘዙ፣ የእህል ኬላውም ፈረሰ፣ እህልም በገበያው ላይ ሞላ፡፡ ሰፌድ እንኳ ለእንጀራ መሳቢያነት ብቻ ሳይሆን፣ ለከባድ መኪና ሾፌሮችና ለከተማ አውቶቡስ አሽከርካሪዎች መቀመጫ ትሆን ዘንድ በብዛት ተሠራጨች፡፡ አይ የሰፌድ እጥረት!...
“…ይሄ የኮንደሚኒየም ነገር ደግሞ የኢሕአዴግን ራስ እያዞረ የመጣ ጉዳይ ሆነ፡፡ ከተማይቱን በሙሉ ቁም ሳጥን በሚመሳስሉ ህንፃዎች እስከ መቼ እገነባታለሁ ብሎ አሰበ፡፡ እነዚህኞቹ የታዩት ወጪ ቆጣቢ መሆናቸው እንጂ፣ ቀደም ብሎ የከተማይቱ ውበት አልታየው ኖሯል፡፡ እናም አሰበ፡፡ ባለ ሙያዎችን ሰበሰበና መላ ምቱ አለ፡፡ መላ ተመታ። ከቀድሞው የበለጠ ወጪ የሌለው ዘዴ ተገኘ። ተዘበራርቀው ፊትና ኋላ እየሆኑ የሚሠሩበት መንገድ ተለውጦ፣ የቀድሞ መጠናቸው ሳይለወጥና ወጪ ሳያንሩ፣ ስድስት ወይም ሰባት ህንፃዎች አንድ ላይ ተጣብቀው መደዳውን እንዲሠሩ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህም በመካከላቸው የባከነው ትርፍራፊ መሬት ተቆጠበ፡፡ ከፊታቸውና ከጀርባቸው መንገድ ተቀድዶ ያማረ ፕላን አገኙ፡፡ ገፃቸው ከፊት በኩል በቅርፃ ቅርጽ እንዲያምሩና የጠጅ ቤቶች ዓይነት ደማቅና ርካሽ ቀለሞች እንዳይቀቡ መመሪያ በመስጠቱ አዲስ አበባ ወደ አውሮፓ ልትጠጋ ከጀለች…
“…ለዓመታት ሲያሳስበኝና ግራ ሲያጋባኝ የኖረው፣ ‹…እስከ መገንጠል› የሚለው አንቀጽ 39 ለምን እስካሁን ሳይሻሻል እንደቆየ ይገርመኝ ነበር። ማስፈራሪያ ይሁን ወይም ሌላ እኔ አላውቅም፡፡ ለማንኛውም በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት፤ ‹…እስከ መገንጠል› የምትለዋ ሐረግ እንድትወጣ ተደረገ፡፡ እኔን ጨምሮ መላው ሕዝብ ተደሰተ፡፡ ኢሕአዴግም የሕዝብን ልብ አገኘ፡፡ ጊዜው ቆየ እንጂ አንድ ፀሐፊ፤ “ማቸነፍስ የሰውን ልብ” ብለው ነበር፡፡ ብቻ…ረጋ እየተባለ፣ ዘግይቶም ቢሆን የህዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው…”
በእንግሊዝኛው፤ “Cheer Leading” እንደሚባለው፣ መንግሥት የሠራቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ብቻ እንድንጽፍ አይጠበቅብንም፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ ባይጠፋውም፣ እኛ ግን ደካማ ጐኑን በመናገራችን እንጠቅመዋለን እንጂ ከቶም አንጐዳውም፡፡ በእርግጥም በመንገድ፣ በከተማ ባቡር፣ በአነስተኛ፣ ጥቃቅን፣ በኮንደሚኒየም፤ (የዲዛይንና ተመሳሳይነትና አልፎ አልፎም የጥራት ጉዳይና ብክነት ከሚነሳ በቀር) መንግሥት ጥሩ ጥሩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ታዲያ እነዚህንና ሌሎች ውጤታማ ሥራዎቹን የመንግሥት ጋዜጠኞችና የራሱ ባለሥልጣናት ስላሉለት በስፋት ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ ውዳሴ ከንቱ እያበዛን አደናጋሪና አዘናጊ መሆን እንደሌለብን እንረዳለን፡፡ “Cheer Leaders ከመሆን እንቆጠባለን፡፡ ለጊዜው ግን እኛ የምናወራው የምናልማትን ኢትዮጵያ ነው፡፡ አዎ አሁንም ህልም አለኝ፡፡
“…እነዚያ ኢሕአዴግን በመጠጋት ከለላ አድርገውት የህዝብ ገንዘብ እየዘረፉ ወደ ኪሳቸው ያደርጉ የነበሩ አባላቱ ጉድ ፈላባቸው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ልክ እንደ ራሱ እየመሰሉት በእነዚህ ሙሰኞች ሲታለል ቆይቶ አሁን ግን ደርሶባቸዋል፡፡ እነሱ ከጨረታውም፣ በየጊዜው ከሚደረጉ ግዙፍ የኮንትራት ውሎችም ለግላቸው ይወስዱት በነበረው ገንዘብ ልክ የእንግሊዝን ባንዲራ በሚመስል መልኩ በመላው ኢትዮጵያ የባቡር መስመዘር ተዘረጋ፡፡ ከሞያሌና ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የሶስት ሰዓት የባቡር ጉዞ ብቻ፡፡ አዎ!... ኢሕአዴግ የሥራ ጓደኞቹ ላይ ጨከን ብሎ አይወስዱ እርምጃ ነው የወሰደው፡፡ ቪቫ! ብሏል ህዝቡ በአንድነት…
“… በዚያ ላይ፣ የግለሰብ ነጻነትና ሰብዓዊ መብት አከባበር ሥር በመስደዱ፤ እዚህም እዚያም ኡኡታ የሚያሰማ ጠፍቷል፡፡ ቋንቋን (ጎሣ) ተመርኩዞ ተካልሎ የነበረው አስተዳደር፣ አሁን ለህዝቡ በሚመች መልኩ ተፈጥሯዊ ገፀ ምድርን ተከትሎ ተዋቅሯል፡፡ በዚህም የዘርና የጎሣ አመለካከት ጠፍቷል፡፡ ሴቱ በእልልታ፣ ወንዱ በሆሆታ ኢህአዴግን ደግፏል፡፡ ሀገሪቱ ልዪ የደስታ ማዕበል ውስጥ ገብታለች፡፡ ኢህአዴግና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጹም ምክር ከልባቸው ሆነው እጅ ለእጅ በመያያዝ ለሀገራቸው ብልፅግና ወደፊት ማየት ጀምረዋል፡፡ በዳዩ ተመክሮ፣ ተበዳዩ ተክሶ ፍፁም ሰላምና ፍቅር በምድሪቱ ሁሉ ላይ ናኘ…”
ክፉ ሥራ ከሌለ ጥላቻ የለም፡፡ መገፋት ከሌለ አመፅ አይኖርም፡፡ ሁሉንም፣ ነገር አንድ ወገን ብቻ ማግበስበስ ከጀመረ ሌላው ወገን ለህልውናው ሲል መንጠቅ ይጀምራል፡፡ መነጣጠቅ ከተጀመረ ግብ ግብ አለ ማለት ነው፡፡ ግብ ግቡ ውሎ የሚያድር ከሆነ ደግሞ ወደ ሌላ ያመራል፡፡ የዚህ ሁሉ ጣጣው ታዲያ ፍቅረ ንዋይ ነው፡፡ ገንዘብ ልብን አሳውሮ ያደነድናል። ልብን አደንድኖ ለገንዘብ፣ በገንዘብ ምክንያት ወንጀሎች ሁሉ ይሰራሉ፡፡ ስለ ገንዘብ የዋሆች ሲናገሩ፣ “የደም ሥር ነው” ይላሉ፡፡ ብልሆች ደግሞ ለፍላጎት ሟሟያ በአግባቡ ካልተጠቀሙበት፤ “ገንዘብ የሰይጣን መሣሪያ ይሆናል” ይሉናል፡፡ ገንዘብን ማምለክ ክፋትና ትዕቢትን ይወልዳል፡፡ ትዕቢትም ኃጢአትን፡፡ የኃጢአት ምንዳው ደግሞ ሞት ነው፡፡ ለማንኛም ገንዘብን በተመለከተ ብዙ ማት ቢቻልም፣ “ገንዘብ!... ገንዘብ!...ገንዘብ!...” የሚለውን የጥላሁን ገሠሠን ዜማ እጋብዛችኋለሁ፡፡
በዚህች ዓለም ላይ ማንኛውም ነገር ሁሉ የራስን መስመር ብቻ ተከትሎ ለአንዲት ሰኮንድም ሳያቋርጥ ይጓዛል፡፡ የወንዝን ተፈጥሯዊ ፍሰት ለአፍታ እንኳ የሚያቆም ማነው? ማዕበልን ማን ይገድባል? የሚሆነው ሊሆን የግድ ነው፡፡
ወንድሜ ኤልያስ! ያንተ ህልም ዓለም ኢትዮጵያ ላይ የኔዋ ታክላበት ምን ዓይነት ዓለምን ጉድ ያሰኘች ሀገር እንደፈጠርን ታሰበህ? በአራድኛው ‹የጨሰች› ሀገር ሆነች አይደል!? የቀንዲሏ ብርሃን እስከ ደመናው ጥግ የሚደርስና የብርሃኗ ፀዳል አየሩን ሞልቶ ከአድማስ እስከ አድማስ የፀለለ ሆኖ አልታየህም? አዎ ያቺ ሀገር ታስፈልገኛለች፡፡ ያ ከስክስ ጫማም ወደ ላይ ሊነሳ የግድ ነው፡፡
ታዲያ ዛሬ ላይ፣ በልብ ውስጥ ኩርፊያ ይሁን ወይም የእንጀራ ነገር ሆኖ፣ ብቻ ውሉ በቅጡ ባልታወቀ ነገር ድምፃቸው የጠፋብን ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፣ በዚያች የእኔና የወንድ ኤልያስ የህልም ዓለም ኢትዮጵያ ጊዜ ሊያስተምሩን ብዕራቸውን ያነሳሉ፡፡ ብዕራቸው ግን ደርቋልና ወረቀቱን ይቧጥጣል፡፡ ምንም ጠብ የሚል ነገር ይጠፋል፡፡ ዛሬ ብዕር ሳይሆን ካቻቪቴ ይሆንብናል። ለማንኛውም ግን በጊዜ አጠቃቀማቸው ይደነቃሉ፡፡
እኔም ኮርኮር አድርጎኝ እዚህ ድረስ ያስወራኝን የኤልያስን ሃሳብ አደንቃለሁ፡፡ ምን ነበር ያለው?
“ሰበር ዜና! - ጠ/ሚኒስትሩ በተቃዋሚዎች ስብሰባ ላይ ተገኙ… “በሽብር” የታሠሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በምህረት ተለቀቁ…” ወዘተ፡፡
በሉ እንግዲህ፣ ሌላ ኮርኳሪ እስካገኝ ድረስ ብብቴን እያደመጥሁ እጠብቃለሁ፡፡ ሰላምና ጤና ለሁላችንም ተመኘሁ!

Read 2823 times