Saturday, 09 August 2014 11:23

የጠ/ሚኒስትሩ የደሞዝ ጭማሪ እንዳይረሳ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(23 votes)

 የኢህአዴግ ዲሞክራሲና የቴሌ ኔትዎርክ ተመሳሰሉብኝ
ደሞዝ የተጨመረው ለምርጫው ነው ለኑሮ ውድነቱ?

እኔ የምለው … አንዳንድ የመንግስት ተቋማት በእነሱ ብሶ ለምንድነው ቁጣ ቁጣ የሚላቸው? (“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” አሉ!) ከምሬ እኮ ነው… እኛ የተበደልነው አርፈን ተቀምጠን እነሱ እየተመላለሱ ይቆጡናል፡፡ (ኧረ “ፌር” አይደለም!) ያውም እኮ ሳንደርስባቸው ነው፤ ቤታችን ድረስ እየመጡ - በኢቴቪ መስኮት፡፡ ከሁሉም አንጀት የሚያበግነው ደግሞ ትላንት እኛው በድምፃችን ይመሩናል ብለን የመረጥናቸው ተወካዮቻችን፣ ማታ ማታ በቲቪ እየመጡ መቆጣታቸው ነው፡፡ (ለ90 ሚ. ህዝብ ማስጠንቀቂያ አይፃፍማ!) ይሄን ሁሉ ያስቀባጠረኝ የሰሞኑ የኢትዮ- ቴሌኮም ቁጣ የተቀላቀለበት መግለጫ ነው፡፡ (እኛ ሳንቆጣ እሱ ይቆጣን?!)
በእርግጥ መጀመሪያ የምስራቹን ነበር ያስቀደመው፡፡ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹን በስኬት ማጠናቀቁን በድል አድራጊነት ስሜት አበሰረን፡፡ (የቴሌ ድል የእኛም ድል ነው!) እንደመሰለኝ… የቁጣው መንስኤ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ጥያቄ ነው፡፡ “ደንበኞች አሁንም የአገልግሎት ጥራት ችግሮች አሉ እያሉ ነው” የሚል ጥያቄ ሳያነሳ አልቀረም - ጋዜጠኛው፡፡ (ግን እኮ አልዋሸም!) ይሄኔ ነው ቁጣ ቁጣ ያለው - “አገልጋያችን” ኢትዮ-ቴሌኮም፡፡
አያችሁ… እዚህ አገር ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ቢሆን እኮ የሚቆጣው ደንበኛ እንጂ አገልግሎት ሰጪው አይደለም፡፡ የሚቆጣው ህዝብ እንጂ መንግስት አይደለም፡፡ (መንግስትማ አገልጋይ ነው!) እኔ የምላችሁ… “ደንበኛ ንጉስ ነው” የሚለው አባባል እኛ አገር “ደንበኛ እርኩስ ነው” በሚል ተቀይሯል እንዴ? …በእርግጥ የኛ አገር ነጋዴዎች ወይም አገልግሎት ሰጪዎች “The Customer is always right” (ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው)  የምትለዋን አባባል ሲሰሙ “መስሎሃል!” እንደሚሉ ነገረ ስራቸው ያስታውቃል፡፡ እናም …ቢቆጡን፣ ቢያንገላቱን፣ መብራት ቢከለክሉን፣ ኔትዎርክ ቢነጥቁን፣ ውሃ ቢወስዱብን፣ ታክሲ የለም ቢሉን፣ ዘይት ቢያጠፉብን፣ ስኳር ቢያስወድዱብን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢፈጥሩብን ወዘተ… ዝም ብለን መቀበል ብቻ ነው፡፡ ለምን “ደንበኛ ንጉስ”  ሳይሆን “እርኩስ ነው”  
እናላችሁ… የኢትዮ ቴሌኮሙ ኃላፊ በኢቴቪ መስኮት ገጭ ብለው የመንግስት “የገቢ ኩራት” ስለሆነው መ/ቤታቸው ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ፡፡ የኔትዎርክ ማሻሻያው “ነዳጅ እንደሚበላ አሮጌ መኪና ሆነ” (አባባሉ የእኔ ነው!) ሲባሉ… አልካዱም፡፡ “በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ኔትዎርክ ይጠፋል” የሚለውን ቅሬታም ተቀብለዋል፡፡ በመጨረሻ ግን “እናስ ምን ይጠበስ?!” ዓይነት ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ “ይሄን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሰራ እኮ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ያጋጥማሉ” አሉን፡፡ (ኔትዎርክ በዓመት አንዴ ጠፋ ብለን የምንሞላቀቅ “ቅንጡዎች”  አደረጉን እኮ!) በመካያውም… “የኔትዎርክም ሆነ ሌሎች ችግሮች በሂደት ይፈታሉ” … ብለው ገላገሉን፡፡ ይሄኔ ነው ኢህአዴግ ነፍሴ ትዝ ያለኝ፡፡ ኢህአዴግ ሁሌም ዲሞክራሲው ተንገራገጨ ወይም መልካም አስተዳደሩ ተሰናከለ አሊያም የሰብዓዊ መብት አያያዙ እያሳጣን ነው…በተባለ ቁጥር “በሂደት ይፈታል” ይለናል፡፡ የእሱ አይደለም የገረመኝ፡፡ የቴሌኮም መድገም ነው፡፡ (አወያይ መመሳሰል አሉ!)
ለዚህም ነው የኢህአዴግ ዲሞክራሲና የቴሌ ኔትዎርክ የተመሳሰለብኝ፡፡ (ሁለቱም የኋሊት ነው የሚጓዙት ልበል!) ለማንኛውም በሂደት ይፈታል ተብላችኋል - ኔትዎርኩ!!
በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር “ዕድለኛ” መሆኑን የተገነዘብኩት በቀደም ዕለት ከንቲባው በኢቴቪ መግለጫ ሲሰጡ ነው፡፡ እንዴት አትሉም? ለውሃው፣ ለመብራቱ፣ ለኔትዎርኩ፣ ለትራንስፖርት ችግሩ ወዘተ ጣታችንን መቀሰር የነበረብን መስተዳደሩ ላይ ነበር (“አስተዳድራችኋለሁ” ብሎን የለ?) እንደ ዕድል ሆኖ ግን ማንም ጠይቆት አያውቅም፡፡ (“ኮንዶሚኒየም ሰሪ ነው” ተብሎ ይሆን?) የሚገርማችሁ ግን የከተማው መስተዳድር  አልተጠየቅሁም ብሎ ዝም አላለም፡፡ ከንቲባው ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በ2007 ዓ.ም የምናለቃቅስባቸው ብዙዎቹ ችግሮቻችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈቱ ነግረውናል፡፡ የከተማዋን የውሃ ችግር ለመፍታት 4 ፕሮጀክቶች ይተገበራሉ (በአዲስ ዓመት ውሃ በሽበሽ!) የኮንዶሚኒየም ግንባታው ተጧጡፎ ይቀጥላል (“እንኳን የተመዘገበ ያልተመዘገበም ቤት ያገኛል” በሚል ተርጉሜዋለሁ!) ብዙ ሺ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ (“ሥራ አጥ ከጎረቤት አገር ማስመጣት ሳይኖርብን አይቀርም” ብያለሁ!)
ለመብራት ችግሩ ደግሞ ከቻይና ጋር አማራጭ የሶላር ኃይል ለመትከል ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለ መሰለኝ (ቻይና ትኑርበት እንጂ “የሻማ ፕሮጀክትም” ቢሆን ይሳካል!) ከንቲባው ብዙ ባለስልጣኖች አውቀው የሚሸሹትን የትራንስፖርት ችግር በማንሳታቸው ብቻ አድንቄአቸዋለሁ (እኔ የአርቲስት ሳይሆን የባለስልጣን አድናቂ ነኝ!) በእርግጥ አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች አዲሱ የከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የትራንስፖት ችግር ድባቅ እንደሚመታ ሲናገሩ ሰምቻለሁ (“ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” አሉ!)
ከንቲባውን የበለጠ የማደንቃቸው ግን መቼ መሰላችሁ? ከ3 ዓመት በላይ ወረፋ እየጠበቀ ታክሲ ለሚሳፈረው የአዲስ አበባ “ቻይ ህዝብ” ልዩ ሽልማት ያስፈልገዋል ብለው ፓርላማውን ያሳመኑ ጊዜ ነው፡፡ ያኔ ያለማቅማማት “ፈርሙልኝ” እላቸዋለሁ፡፡ ያኔ “ጀግናዬ” ይሆናሉ፡፡
እኔ የምላችሁ… የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንደተባለው ለሐምሌ ባይደርስም መጠኑ ተነገረን አይደል! (ህገወጥ ነጋዴዎች እንኳንም ሰሙት!) በነገራችሁ ላይ አንድ ጋዜጣ ጭማሪው እስከ 110%  እንደሚደርስ የፃፈው ከየት አምጥቶ ነው? (ህልሙን መሆን አለበት!) ይሄን የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይ ከሰማሁ ጀምሮ እኔን ሲያሳስበኝ የቆየውን ግን የመንግስት ሰራተኛው ስንት ይጨመርለታል የሚለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ምን ቢጨመርለት የኑሮ ውድነቱ ይቀማዋላ፡፡ በዚያ ላይ ታክሱ፣ የህዳሴ ግድብ መዋጮው፣ የአባልነት ክፍያ (ይሄ እንኳን ለኢህአዴጎች ብቻ ነው!) ለጡረታ የሚቆረጠው … በቅርቡ ደግሞ 3 በመቶ የጤና መድህን ዋስትና መቆረጥ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ከሚያገኘው የሚሰጠው ይበልጣል፡፡ ለዚህ ነው የመንግስት ሰራተኛ የደሞዝ ጭማሪ እምብዛም ያላሳሰበኝ፡፡
እኔን ከምር ያሳሰበኝ ምን መሰላችሁ? የጠ/ሚኒስትሩ የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይ ነው፡፡ አያችሁ… እሳቸው እንደኔና እንደናንተ የ“ደሞዝ ጭማሪዬ የታለ”? ብለው መጠየቅ አይችሉም (ክብራቸው አይፈቅድላቸውማ!) እናም ለመንግስት ሰራተኛ ሁሉ የተወሰነለትን የደሞዝ ጭማሪ ሳያገኙ ሊረሳሳ ይችላል፡፡ የእዚህን ሁሉ የመንግስት ሰራተኛ የደሞዝ ጭማሪ በቲቪ እያበሰሩ የሳቸው ግን ተረስቶ ይቀራል፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ደሞዛቸው ስንት እንደሆነ የተጠየቁ ጊዜ ወደ 6ሺህ 500 ብር ገደማ መሆኑን ገልጸው አዲሱ ጭማሪ ግን ገና እንዳልደረሳቸው መናገራቸውን አታስታውሱም? (አያችሁ እኔም የፈራሁት ይሄን ነው!) እስቲ አስቡት.. እቺም ደሞዝ ሆና ስትረሳ! እኔ የምለው ግን… መቼ ነው ይሄ የጠ/ሚኒስትር ደሞዝ በወጉ የሚስተካከለው? (የአገር ገፅታ እኮ ያበላሻል!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል.. ፈረንጅ ቢሰማ እኮ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትሮች በደሞዝ ሳይሆን በበጐ ፈቃደኝነት ነው የሚሰሩት ሊል ይችላል፡፡ ለአንድ መሪ በወር 300 ዶላር ደሞዝ ነው እንዴ? የኪስ ገንዘብም እኮ አይሆንም፡፡ (“ንቀውናል” አሉ መንጌ!) እውነቱን እንነጋገር አይደል… ለጠ/ሚኒስትራችን 6ሺህ ብር በመክፈል የምናተርፈው ምንም የአገር ሃብትና ንብረት የለም፡፡ ይልቁንስ ለእሳቸው የማያሳማ ክፍያ እየከፈልን የአገር ሃብትን ከመንግስትና ከግል ሙሰኞች ብንጠብቅ ነው የሚሻለው፡፡ ለጊዜው ያንገበገበኝ የጠ/ሚኒስትሩ ደሞዝ ስለሆነ ነው እንጂ የፓርላማ አባላትም የባሰ ነው፡፡ የእነሱ ደሞዝ ደግሞ 200 ዶላር ገደማ ቢሆን ነው፤ በእኛ ወደ 4ሺ ብር አካባቢ ማለት ነው! መቼም የመንግስት ባለስልጣናትን ደሞዝ ለማሻሻል የውጭ አገር ተሞክሮ ወይም የቻይና አማካሪዎች አያስፈልጉንም፡፡ እቺን እንኳን እስቲ ራሳችን እንስራት!!

Read 4552 times