Saturday, 09 August 2014 11:19

የሰሞኑ ክስና ሥጋት ውስጥ የወደቀው የግሉ ፕሬስ

Written by 
Rate this item
(16 votes)

በማተሚያ ቤት ክልከላ ከ“ፋክት” በስተቀር ሁሉም አልታተመም
ሁሉም ተከሳሾቹ ክስ አልደረሰንም ብለዋል


“የግል ፕሬሱን ለማሸማቀቅና የስነ-ልቦና ጫና ለመፍጠር የተደረገ ይመስላል”
- ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ
“መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደመጥፎ ነገር አናየውም”
- አንተነህ አብርሃም (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)
“መንግስት ክስ የመሰረተው ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል”
- ዘ ኢኮኖሚስት  


የፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ምሽት በኢቴቪ ባወጣው መግለጫ፤ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የአመፅ ቅስቀሳና የሐሰት ወሬዎች በመንዛት፣ ህገመንግስታዊ ስርዓቱ በሃይል እንዲፈርስና ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባሮችን ፈጽመዋል ባላቸው አምስት መፅሄቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱን ጠቁሟል፡፡
ክስ ተመስርቶባቸው የተባሉት “ፋክት”፣ “ጃኖ”፣ “ሎሚ”፣ “አዲስ ጉዳይ” እና “እንቁ” መፅሄቶች እንዲሁም “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚዎች በበኩላቸው፤ መከሰሳቸውን በሚዲያ ከመስማታቸው ውጭ ምንም ዓይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ገልፀው መከሰሳቸው በሚዲያ መታወጁን ተቃውመውታል፡፡
የግል ፕሬሶቹ መከሰስ በሚዲያ መገለፁን ተከትሎ ማተሚያ ቤቶች “አናትምም” እንዳሏቸው አሳታሚዎች የተናገሩ ሲሆን በዛሬው ዕለት መውጣት ከነበረባቸው የህትመት ውጤቶች ከ “ፋክት” በስተቀር ሁሉም እንደማይታተሙ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ክስ ከቀረበባቸው የግል ፕሬሶች አንዱ የሆነው የ“ሎሚ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ግዛው ታዬ፤ የክስ ዝርዝር እንዳልደረሳቸውና ጉዳዩን የነገራቸው አካል እንደሌለ ጠቁመው፤ ክሱ በቴሌቪዥን መገለፁ በሚዲያ ተቋሙ ጋዜጠኞች ላይ የስነልቦና ጫና ማሳረፉን ተናግረዋል፡፡ “ቀደም ብሎ እንደታሰሩት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች አፈሳ ሊካሄድብን ይችላል በሚል ስጋት ጋዜጠኞች በተረጋጋ ሁኔታ በቢሮአቸው ተቀምጠው ስራቸውን መስራት አልቻሉም” ብለዋል፡፡
መንግስት  የግል ፕሬሶቹ መከሰሳቸውን በሚዲያ ማወጁ ህገ መንግስቱን የጣሰ አካሄድ ነው ያሉት አቶ ግዛው፤ “ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ከፖሊስ ተደውሎ ቀጠሮ ከተሰጠን በኋላ በምንጠየቅበት ጉዳይ ላይ ቃላችንን እንድንሰጥ ይደረግ ነበር፤ ይሄኛው ለየት ያለ አካሄድ ነው” ብለዋል፡፡
የ“አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በሚዲያ ከገለፀው ውጪ ምንም አይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፣ በዛሬው እለት ይወጣ የነበረው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ክሱ በቴሌቪዥን ከተነገረ በኋላ ማተሚያ ቤቱ “አላትምም” በማለቱ መጽሔቱለንባብ ባይበቃም ሰራተኞቻቸው ግን ያለምንም መረበሽ በመደበኛ ስራቸው ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት “አዲስ ጉዳይ” ሌላ ማተሚያ ቤት ታትሞ እንደሚወጣ የጠቆሙት አቶ እንዳልካቸው፤ ተመስርቷል በተባለው ክስ ጉዳይ ድርጅታቸው ከህግ አማካሪዎች ጋር እየተማከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደሌሎቹ ተጠርጣሪ ፕሬሶች ሁሉ የክስ ዝርዝር እንዳልደረሳቸውና የህግ ሰው እንዳላነጋገራቸው የገለፀው የ “ፋክት” መጽሔት አምደኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ መፅሄቱ እንደወትሮው መደበኛ ህትመቷ እንደሚቀጥልና በዛሬው እለትም እንደምትወጣ አስታውቋል፡፡ ከማተሚያ ቤት በኩል እስካሁን የገጠማቸው ችግር እንደሌለም ጋዜጠኛ ተመስገን ጨምሮ ገልጿል፡፡
መንግስት በአደባባይ ይፋ ባደረገው ክስ ፕሬሶቹን ወንጀለኛ ሳይሆን ተጠርጣሪ ማለቱን ያስታወሰው ተመስገን፤ ከዚህ መግለጫ ተነስተው “አናትምላችሁም” የሚሉ ማተሚያ ቤቶች ካሉ ትልቅ ስህተት እየሰሩ ነው ብሏል፡፡
በክሱ ተደናግጠን ስራችንን አናቆምም ያለው ጋዜጠኛው፤ “ወደፊት ይመጣል ብለን የምናስበው “የህዳሴ አብዮት” እስኪካሄድ ድረስ ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ እንደዚህ ያሉ አፈናዎች ለጊዜው ካልሆነ በቀር ዘላቂ አይሆኑም” ብሏል፡፡ “ሠሞነኛው የመንግስት እርምጃ “የህዳሴ አብዮት”ን ለመቀልበስ የሚደረግ መፍጨርጨር ነው፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም፤ መከሰሳችንም አዲስ አይደለም፤ በአብዮታዊ ጋዜጠኝነታችን እንቀጥላለን፤ ትግላችን ቀራኒዮ ድረስ ነው” ብሏል፡፡
የ“እንቁ” መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በበኩላቸው፤ መንግስት ክሱን በአደባባይ ይፋ ካደረገ በኋላ ማተሚያ ቤቶች አናትምም እንዳሏቸውና ዘወትር ቅዳሜ ገበያ ላይ ትውል የነበረችው መጽሔት በዚህ ሣምንት ለገበያ እንደማትበቃ ገልፀዋል፡፡
መንግስት ከዚህ ቀደም በህትመት ውጤቶች ላይ የሚወጡ ፅሁፎች ህግ ጥሰዋል ካለ ዋና አዘጋጁን ይከስ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፤ በዚህኛው ክስ አሣታሚዎች ላይ ማነጣጠሩ ሚዲያዎቹ እንዲዘጉ ያለውን ፍላጐት ያሣያል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በመንግስት የሚዲያ ተቋማት በኩል በእነዚህ የህትመት ውጤቶች ላይ ሰፊ የማጥላላት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በተደጋጋሚ “መንግስት ሆደ ሰፊ ነው፤ ተቀራርበን እንሠራለን” የሚሉ መልዕክቶች በመንግስት ወገን እየተላለፉ ቢቆዩም የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት በተግባር አላየነውም ብለዋል፡፡ “እንቁ” መጽሔት በፕሬስ አዋጁ መሠረት ክስ ቀርቦበት ወንጀለኛነቱ የተረጋገጠበት ጊዜ አለመኖሩን የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፤ አሁን ግን መጽሔቱ በህትመት ኢንዱስትሪው ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን ለመወሰን እንደተቸገሩ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ክስ የቀረበበት የ“ጃኖ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ልባዊ፤  ምንም ዓይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው የክሱ መግለጫ በቴሌቪዥን ከተሰራጨ በኋላ ማተሚያ ቤቶች መጽሔታቸውን አናትምም እንዳሏቸው ገልፀዋል፡፡ “ማተሚያ ቤቶች ፍቃደኛ ካልሆኑ የት ሄደን እናሣትማለን?” ሲሉ የጠየቁት አቶ አስናቀ፤ “የመንግስት መልካም ፍቃድ ከሆነ እንቀጥላለን፤ ካልሆነ ለማቆም እንገደዳለን፤ ነገር ግን ሚዲያው በመንግስት መልካም ፍቃድ ብቻ መንቀሳቀሱ ያሣዝናል” ብለዋል፡፡
በክሱ ውስጥ ያልተካተቱ የግል ፕሬስ አሳታሚዎችና አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በመንግስት ተመሰረተ የተባለው ክስ የግል ሚዲያውን ስጋት ውስጥ እንደከተተው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ወርቁ፤ “የሰሞኑ የመንግስት ክስ ለተቀሩትም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ያስተላለፈ እንደመሆኑ “ማነሽ ባለተራ” እየተባለ በስጋት እንድንሠራ የሚያደርግ ነው፤ ይህ ደግሞ በአሣታሚዎችም ሆነ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጥረው የስነልቦና ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብለዋል፡፡
ሚዲያና ህዝብ ከሚፈላለጉበት ጊዜ አንዱ የምርጫ ወቅት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ክሱ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ይፋ መደረጉ የግል ፕሬሱን ለማሸማቀቅና የስነልቦና ጫና ለመፍጠር ይመስላል ብለዋል፡፡ “ክሱ በቀጥታ አሣታሚው ላይ እንዲያነጣጥር መደረጉ ከአሣታሚዎች ነፃ ሊሆን ይገባዋል በሚባለው የጋዜጣው ኤዲቶሪያል ፖሊስ ላይ ጣልቃ መግባት እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀው፤ ይሄ ደግሞ በዚህም ጋዜጠኞች በሙያቸው ነፃ ሆነው እንዳይሠሩ የሚሸብብ የሚዲያ ድባብ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡
“በመግለጫው ላይ ክሱ ህግን በማያከብሩ ሌሎች ሚዲያዎች ላይም ይቀጥላል መባሉ በአጠቃላይ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት ጥያቄ ውስጥ ከትቶ በነፃ ሚዲያው አካባቢ ፍርሃትና መሸማቀቅ እንዲፈጠር ያደርጋል” ሲሉም አክለው ገልፀዋል፡፡  
“መንግስት በሚዲያ ክሱን ይፋ ማድረጉ አጠቃላይ የሚዲያ ምህዳሩን ይረብሸዋል” ያሉት የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ደምሴ፤  ከሁለት አስርት አመታት እድሜ ያልዘለለውን ፕሬስ ገና ዳዴ እያለ ባለበት ወቅት እንደመንከባከብ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች መወሰዳቸው አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ክስተቱ በሃገራችን ፕሬሶች ላይ መሠረታዊ ችግሮች እንደሚንፀባረቁ ይጠቁማል የሉት አቶ መላኩ፤ ከመንግስት ባለስልጣናት ጫና ባሻገር የሙያ እውቀት ችግር እንደሚንፀባረቅም ተናግረዋል፡፡ ሚዲያው እየተንቀሳቀሰበት ያለው ድባብ በራሱ ጥሩ አይደለም፤ በዚህ የተነሳ የትኛውም ባለሀብት ወደዚህ ዘርፍ መግባት አይፈልግም ሲሉ በአጠቃላይ ሚዲያው በአሣሣቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጋዜጠኛ መላኩ ገልፀዋል፡፡
አዲስ የተቋቋመውና እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ምክትል ሊቀመንበር ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጐስ በበከሉ፤ በመንግስት በኩል እንዲህ መሰሉ እርምጃ እንደሚወሰድ አስቀድሞ ይታወቅ እንደነበር ይናገራል፡፡ ማህበራቸው የመንግስትን እርምጃ እንደሚቃወምና አሁን ባለው የሚዲያ እንቅስቃሴ በተነባቢነትና በተደራሽነት ሰፊ ይዞታ ያላቸውን “ፋክት”፣ “ሎሚ” እና “አዲስ ጉዳይ” መጽሔቶችን መክሰሱ በሚዲያ ባለቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአንባቢያን ላይም ተጽእኖ ያሳርፋል ባይ ነው፡፡
ክሱ በራሱ አደናጋሪ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ስለሺ፤ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሠረት ጥፋት ካለ በእያንዳንዱ ጽሑፍ ተጠያቂው አካል ይጠየቃል እንጂ ተቋማት ላይ ማነጣጠሩ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም በበኩላቸው፤  “ማንኛውም የሚዲያ ተቋም ሲከሰስ አሣሣቢ ቢሆንም መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደመጥፎ ነገር አናየውም” ብለዋል፡፡
የክሱ ሂደት ሲታይ መጽሔቶችም ሆነ ጋዜጣው መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ ቢደረግ መልካም ነው ያሉት አቶ አንተነህ፣ “እኛ እንደ ጥሩ ነገር ያየነው ከሚዲያ ተቋማቱ ጋር ጋዜጠኞች ተደርበው አለመከሰሳቸውን ነው፤ የአሁኑ የመንግስት እርምጃ፣ ጋዜጠኛውን ከመክሰስ ይልቅ ተቋሙም ሃላፊነት እንዲሰማው ለማድረግ የጐላ ጠቀሜታ አለው በሚል የተወሰደ እርምጃ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ክሱን በሚዲያ መግለፁ ሁለት አይነት መልዕክት እንደሚኖረው አቶ አንተነህ ጠቁመው፤ አንደኛው ጋዜጠኛ ጥፋት ካጠፋ በህግ እንደሚጠየቅ ያስተምራል፣ በሌላ በኩል ፍርሃት ያሳድራል ብለዋል፡፡ ፍርሃት መፈጠሩ በበጐ የሚታይ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዞሮ ዞሮ ለህግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ እርምጃው ከሌሎቹ ጊዜያት በተሻለ ረጋ ተብሎ የተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሳታሚዎቹና በሚዲያ ተቋማቱ ላይ የተመሰረተውን ክስ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው  የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን፤ በማናቸውም ወንጀል ጉዳይ የክስ ሂደት የሚጀምረው ከፖሊስ ምርመራ መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ ጉዳይ ፍትህ ማኒስቴር ያቀረበው ክስ አሣታሚዎች ላይ በመሆኑ ስራ አስኪያጆች በቀረበባቸው ክስ ላይ ቃል መስጠት አለባቸው ይላሉ፡፡ “ይህ ስለመደረጉ የተሟላ መረጃ የለኝም፤ ነገር ግን በተለያዩ ሚዲያዎች ቃል አለመስጠታቸው እየተነገረ መሆኑን እየሰማሁ ነው ያሉት ባለሙያው፤ “ክሱ ይፋ የተደረገበት መንገድ ትክክለኛ ነው” የምልበት ምንም የህግ ምክንያት የለኝም፤ ምናልባት የህትመት ጉዳይ የሚመረመር ጉዳይ የለውም፤ ጋዜጠኞች ሲከሰሱ የጊዜ ቀጠሮ አይጠየቅባቸውም ቢባልም ማንኛውም ተሠራ የተባለ ወንጀል በፖሊስ በኩል ሣያልፍ ቀጥታ በአቃቤ ህግ ክስ ይመሠረታል ማለት አይደለም፤ የምርምራ መዝገብ በፖሊስ መደራጀት አለበት” ብለዋል - አቶ አመሃ፡፡
“ፍትህ ሚኒስቴር ክስ መስርቻለሁ ብሎ በሚዲያ መናገሩ ከህግ አንፃር ብዙም ጥያቄ የሚያስነሳ አይመስለኝም” ያሉት አቶ አመሃ፤ “ክስ መመስረቱ የተነገረበት መንገድ ህገወጥ ነው ማለት ባይቻልም አላማው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል፡፡
ከህግ አንፃር በዋናነት ሊታይ የሚገባው የተጠያቂነት ቅደም ተከተል ነው የሚሉት  የህግ ባለሙያው፤ በፕሬስ አዋጁ መሰረት መጀመሪያ የሚጠየቀው ዋና አዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው ዋና አዘጋጁ ከሌለ ወይም ኖሮም የአዘጋጅነትን ሃላፊነት መወጣት የማይችል ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው ሃላፊነቱ ወደ አሣታሚው የሚተላለፈው ይላሉ። “ፍትህ ሚኒስቴር ክሱን ያቀረበው አዘጋጆቹን መጀመሪያ ጠይቆ ነው? ሃላፊነታቸውን መወጣት የማይችሉ ሆኖ አግኝቷቸው ነው ወደ አሣታሚዎች የሄደው? የሚለው ግልጽ አይደለም፤ የህግ አካሄድ ጥያቄም ከዚህ አንፃር ሊነሣ ይችላል” ብለዋል አቶ አመሃ፡፡
የክስ ሂደቱ በፍርድ ቤት እየታየ የሚዲያ ተቋማቱ ከህትመት የሚታገዱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል? ስንል የጠየቅናቸው የህግ አማካሪው፤ አቃቤ ህግ ይታገዱ ብሎ ካመለከተ፣ ተከሳሾች ለእግድ ጥያቄው የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤት አይቶ  ሊያግዳቸው ይችላል ብለዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ሰኔ ወር ታትሞ ከወጣው ዘመን መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “እኛ አገር ነፃ የግል ፕሬሱ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በርከት ያሉት ነፃ አውጪ ናቸው፡፡ ነፃ አውጪ ከሆኑ ውጊያ ገጥመዋል ማለት ነው፡፡ ውጊያ ከገጠሙ እንደማንኛውም ተዋጊ ይታያሉ ማለት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ታዋቂው መጽሄት ዘ ኢኮኖሚስት ከኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋር በተያያዘ ትናንት ለንባብ ባበቃው ዘገባ፣ አገሪቱ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ ቀጥላ ከአፍሪካ አህጉር በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሲፒጄን መረጃ ጠቅሶ የጻፈ ሲሆን፣ መንግስት በመጽሄቶቹና በጋዜጣው ላይ ክስ የመሰረተው፣ ከመጭው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ጭንቀት ውስጥ በመግባቱ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡

Read 8090 times