Saturday, 09 August 2014 11:16

አለማቀፉ የጉዲፈቻ ተቋም በሙስናና በማጭበርበር ሕፃናትን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ መውሰዱን ኃላፊው አመኑ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ለክልል ባለስልጣንና ለአንድ የስራ ሃላፊ ገንዘብና ውድ ስጦታ ሰጥቻለሁ ብለዋል

ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ‘ኢንተርናሽናል አዶፕሽን ጋይድስ’ የተባለ አለማቀፍ የጉዲፈቻ ተቋም የውጭ ፕሮግራም ክፍል ሃላፊ በመሆን ለረጅም አመታት ያገለገሉት  አሊያስ ቢቬንስ፣ ተቋሙ በሙስናና በማጭበርበር ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ይወስድ እንደነበር በሳውዝ ካሮሊና የፌደራል ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንደሰጡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡  
የአሜሪካ መንግስት የፍትህ ተቋም ባለፈው ረቡዕ ያወጣውን መግለጫ የጠቀሰው ዘገባው፣ የስራ ሃላፊው እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2009 በነበሩት አመታት ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ሲሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና የስራ ሃላፊዎች ጉቦ መስጠታቸውን እንዲሁም ለአሜሪካ መንግስት ሐሰተኛ የጉዲፈቻ ሠነድ በማቅረብ የማጭበርብር ድርጊት ሲፈጽሙ እንደቆዩ ማመናቸውን ጠቁሟል።
የ42 አመቷ አሊያንስ ቢቬንስ ከሌሎች አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር ከኢትዮጵያ የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ጋር ተፈራርመናቸዋል ያሉትን  የተጭበረበሩ የጉዲፈቻ ስምምነቶችና  ተያያዥ ሃሰተኛ ሰነዶች ለአሜሪካ መንግስት መስጠታቸውን እንዳመኑ የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህ መልኩ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑት፣ ከተቋሙ ጋር የጉዲፈቻ ስምምነት አድርገዋል በተባሉት የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያልተመዘገቡና ተገቢው እንክብካቤ ያልተደረገላቸው መሆናቸው እንደተረጋገጠም አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን  የመንግስት ባለስልጣንና የስራ ሃላፊ የድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማሳመን እንዲሁም  በጥቅማጥቅሞች ደልለው ወደ አሜሪካ በመውሰድ፣ የህጻናቱ የቪዛ ጉዳይ በቀላሉ እንዲያልቅና ጉዲፈቻውን በማጭበርበር ለማሳካት እንዲዲያግዟቸው ማድረጋቸውንም አምነዋል ብሏል- የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡ የድርጊቱ ተባባሪ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል በመንግስት ትምህርት ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰብ እንደሚገኙበት ለሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት የተናገሩት ቢቬንስ ፣ ግለሰቡ በአሜሪካ ለሚገኙ የጉዲፈቻ አሳዳጊዎች የህጻናቱን የጤናና ማህበራዊ ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ በመስጠት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከተቋሙ ገንዘብ እንደተከፈላቸውና ውድ ስጦታዎች እንደተበረከቱላቸው ተናግረዋል፡፡
የክልል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ሌላው የድርጊቱ ተባባሪም፣ ስልጣናቸውን በመጠቀም  ተቋሙ በአገራት መካከል የሚያከናውናቸው የጉዲፈቻ ስራ ማመልከቻዎች በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኙና ህገወጥ ተልዕኮውን እንዲያሳካ በማገዛቸው፣ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የውጪ አገራት ጉዞ ከማድረጋቸውም በላይ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደተሰጣቸውም ሃላፊው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቢቬንስን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት፣ከጥቂት ቀናት በኋላ በተከሳሹ ላይ ተገቢውን ቅጣት ይጥልባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 3187 times