Saturday, 09 August 2014 11:13

100ሺ አባላት ያሉት ዘመናዊ እቁብ ተጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(35 votes)

       በየወሩ 350 ብር በማዋጣት የከፍተኛ ንብረት ባለቤት ለመሆን የሚያስችል ዘመናዊ የእቁብ ፕሮግራም መጀመሩ ሰሞኑን ተገለፀ፡፡ የእቁብ ፕሮግራሙ፤ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው 100 ሺ አባላት ሲኖሩት በሰባት ዓመት ወይም በ90 ወራት ጊዜ ውስጥ ሁሉም አባላት ባለእድል ሆነው ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
አንድ መቶ ሺህ አባላት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲመዘገቡ ተደርጎ የመጀመሪያዎቹ 40 ያህል እጣዎች የሚወጡ ሲሆን የመጀመሪያው እጣም ከአንድ ወር በኋላ በሸራተን አዲስ ሆቴል እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡
የእቁብ ፕሮግራሙን የሚያከናውኑት “ጎጆ እቁብ” እና “ዋይኤችኤ ኢንዱስትሪያል” ሲሆኑ በእጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ላይ የሚሳተፈው ደግሞ “ሲምቦል ቴክኖሎጂ” እንደሆነ ታውቋል፡፡  ከትናንት በስቲያ በድርጅቶቹ የውል ስምምነት ፊርማ ላይ እንደተገለፀው፤ “ዋይኤችኤ ኢንዱስትሪያል” ለባለዕድለኞች የሚሰጡ ንብረቶችን ከኩባንያዎች ጋር በመሆን ያቀርባል፡፡
በየወሩ 350 ብር እየከፈሉ አባል የሚሆኑ እቁብተኞች በ90 ወራት ውስጥ 31 ሺህ 500 ብር የሚያዋጡ ሲሆን በዚህ ገንዘብ በእጣው ከተካተቱት የጭነት መኪና፣ ከባድ ማሽኖች፣ መኖሪያ ቤት፣ ሚኒባስ፣ ሎደር ግሬደርና ኤክስካቫተር  የመሳሰሉት ንብረቶች ተጋሪ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በእጣው ለባለ እቁብተኞች የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እንደ ሞኤንኮ፣ ሬስ ኢንጂነሪንግ፣ ኒያላ ሞተርስና አምቼ ባሉ ኩባንያዎች የሚቀርቡ ሲሆን የመኖሪያ አፓርታማ በማቅረብ ደግሞ በላከማል እና የቻይና ቤት አልሚ ድርጅት እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
እቁቡ እንደማንኛውም ባህላዊ እቁብ ዳኛ፣ ዋና ፀሐፊና አቃቢ ነዋይን ጨምሮ ህጋዊ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚኖረው የጠቆሙት የፕሮግራሙ ከዋኞች፤ የሚሰበሰበው ገንዘብ የስራውን ሂደት በሚመሩት ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክና አቢሲኒያ ባንክ በተከፈተ የሂሳብ መዝገብ ይቀመጣል ብለዋል፡፡
የእቁቡን አሰባሰብ ሂደት ያብራሩት የ“ጎጆ እቁብ” መስራችና ስራ አሥኪያጅ አቶ ናደው ጌታሁን፤ ምዝገባ እንደተጠናቀቀና የመጀመሪያው ዙር ባለዕጣዎች (እድለኞች) እንደታወቁ በ5 የስራ ቀናት ጊዜ ውስጥ በገንዘብ ገቢ ያደርጋል፤ የእጣ ቁጥሩም በአጭር የሞባይል መልዕክት ይነገረዋል ብለዋል፡፡
ይህ አይነቱ ዘመናዊ እቁብ እንደ ቻይናና አሜሪካ ባሉ ያደጉ አገራት እንደሚሰራበት የጠቆሙት አቶ ናደው፤ድርጅታቸው ከስራ ሂደቱ 2 በመቶ ኮሚሽን እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡

Read 9364 times