Saturday, 09 August 2014 11:10

ንግድ ባንክ ስኬታማ ሆኛለሁ፤ ትርፌም አድጓል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው  የበጀት ዓመት ከግሉ ዘርፍ 34.9 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡንና የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም ወደ 193.3 ሚሊዮን ብር በማሳደግ 9.7 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ፤ በበጀት አመቱ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ  ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ38.8 ሚሊዮን ብር ይበልጣል ብሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባንኩ ለተለያዩ የኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፎች 79 ቢሊዮን ብር ያበደረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 38.2 ቢሊዮን ብሩን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መልሶ መሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል፡፡ በውጭ ምንዛሬ ረገድም 5.5 ቢሊዮን ዶላር የሰበሰበ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው በ720 ሚሊዮን  ዶላር እንደሚበልጥ ታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 17.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን አጠቃላይ ሃብቱ  ወደ 242.7 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን የባንኩ መግለጫ አመልክቷል፡፡ የቅርንጫፍ ባንኮች ቁጥሩንም በ137 ከፍ አድርጎ በጠቅላላው የ832 ቅርንጫፎች ባለቤት ሆኗል ተብሏል፡፡ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግም በኮር ባንኪንግ ሲስተም 634 ቅርንጫፍ ባንኮችን በማስተሳሰር ለደንበኞች አገልግሎቱን እያዳረሰ ነው ያሉት የባንኩ ስራ አመራሮች፤የሴቶች የቁጠባ ሂሳብና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የመሳሰሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ማስተዋወቅ እንደቻለ ጠቁሟል፡፡

Read 1988 times