Saturday, 02 August 2014 11:32

ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል! (ስንቱ ጋ ይሁን?)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ባለስልጣናት ሥልጣን የማይለቁት “የስልጣን ጡር” ስለሚፈሩ ነው

        ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ስል ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ እንዳትገቡ፡፡ ያልተቀኘሁትን ቅኔም ለመፍታት እንዳትሞክሩ፡፡ እኔ ለማለት የፈለግሁት ኢህአዴግ በግራና በቀኝ በልማት ስለተጠመደ፣ ይህችን አገር በቅጡ ለመምራት “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ነው፡፡ እመኑኝ፤ በአማካሪ በምናምን ሊወጣው የሚችለው ጉዳይ አይደለም። በ“ረዳት መንግስት” ብቻ እንጂ፡፡ ያውም እኮ ቀና “ረዳት መንግስት” ከተገኘ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ልማታዊው አውራ ፓርቲ፤ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በራሱ ጥፋት ነው (ለመወንጀል ሳይሆን ለመተቸት ያህል ነው!) የመንግስት ሹማምንቱን በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ መመልመሉ ነው ለዚህ ያበቃው (የፓርቲ ፍቅር ሌላ ብቃት ሌላ!) እስቲ አስቡት… ኢህአዴግ እተማመንባቸዋለሁ ብሎ ከሾማቸው የፓርቲው ታማኝ አባላት መካከል ስንቶቹ በሙስና ተዘፍቀው ዘብጥያ እንደወረዱ! ልማታዊ ህዝብ ይፈጥራሉ የተባሉ ስንት ሹመኞች የኪራይ ሰብሳቢ ሰራዊት መልምለውና አሰልጥነው ቁጭ እንዳሉ! (“የት ይደርሳል የተባለ ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው” አሉ!)
እኔ የምለው… ኢህአዴግ “ታማኝ” ናቸው ብሎ ከሾማቸው በኋላ ሙሰኛ ሆነው ለተገኙት አባላቱ ተጠያቂው ማነው?(እንደ ደንቡማ ኢህአዴግ ነበር!)
ይሄን ሁሉ ያመጣሁት ዝም ብዬ ለወቀሳ ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል እስከመባል የደረሰው ራሱ የሾማቸው ኃላፊዎች ስራቸውን በቅጡ ስለማይሰሩ እንደሆነ ለማስረገጥም ጭምር ነው፡፡  አንድም በአቅም ማነስ፣ አንድም ደግሞ በልግመት፡፡ (የአቅም ግንባታ መ/ቤት ተዘግቷል እንዴ?)
ይሄውላችሁ…. አንዳንድ ከተጨባጩ እውነታ የተራራቁ ፖለቲከኞች (ኢህአዴግ “ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች” የሚላቸው!) በምርጫ ዋዜማ ላይ እንደሚሉት፤ “ኢህአዴግ አብቅቶለታል፤ አንድ ሐሙስ ነው የቀረው!” ምናምን የሚል ነገር አልወጣኝም (ኧረ ወደፊትም አይወጣኝ!) “ረዳት መንግስት” የሚለው ሃሳብ ከተተገበረ እኮ ኢህአዴግ እንኳን ሊያበቃለት አዲስ ጉልበት ነው የሚያገኘው (እንደ ውለታ እንዲቆጠርልኝ ፈልጌ ግን አይደለም!)
በእርግጥ ሃሳቡ ከፀደቀ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ሁሉ ሊረቀቅ ይችላል፡፡ ለምን መሰላችሁ? “ረዳት መንግስት” የሚለው ትንሽ አወዛጋቢ ሊመስል ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ሌላ ምርጫ የለም። ለነገሩ የመንግስትና የስልጣን ጉዳይ ሁሌም ስለሚያወዛግበን ነው እንጂ ቀላል ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…ለሳይንቲስት ረዳት ሳይንቲስት፣ ለሃኪም ረዳት ሃኪም፣ ለዳኛ ረዳት ዳኛ ወዘተ… እንዳለው ሁሉ፣ ለኢህአዴግ መንግስትም “ረዳት መንግስት” እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነው፡፡ (ህግና ደንብ አውጥቶ ማለቴ ነው!) “ረዳት መንግስት” ከየት ይመጣል? እኔ አላውቅም፡፡ እንዴት ይደራጃል? እሱንም አላውቅም፡፡ (እኔ መፍትሔ አፍላቂ ብቻ ነኝ!)
እዚህ ጋ አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገው፣ ኢህአዴግ እንደካምቦዲያ መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ስልጣን ይጋራ እያልኩ አለመሆኔን ነው፡፡ ሥልጣን ማጋራትም ሆነ መጋራት ሃጢያት ሆኖ ግን አይደለም፡፡ (ላወቀበትማ ሥልጣኔ ነበር!) የዚህ ፅሁፌ ዓላማ “የሥልጣን ማኔፌስቶ” ማዘጋጀት ባለመሆኑ ብቻ ነው፡፡ እናም ሲፈልግ ኢህአዴግ ራሱ ሊያደራጀው ወይም ደግሞ እንደ ማኔጅመንት ኩባንያ ከውጭ አገር በቅጥር ሊያስመጣው ይችላል። ዋናው ነገር ግን “ረዳት መንግስት” በአፋጣኝ እንደሚያስፈልገው ማወቁ ላይ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ይሄ “ረዳት መንግስት” የሚለው ነገር በመንግስት አስተዳደር የዳበረ ልምድ አለን ከሚሉት ከየትኞቹም የዓለም አገራት ያልተቀዳ ኦሪጂናል “አገር በቀል” ሃሳብ ነው፡፡ (ከስንዴ እስከ ጸረ-ሽብር ህግ ከእነሱ ቀድተን እንችለዋለን እንዴ?) እናላችሁ… ኢህአዴግ በል ካለውና እግረ መንገድ ከመንግስት ሥልጣን ጋር እንዲለማመዱ ካሰበ… አቅም ያላቸውን ተቃዋሚዎች “ረዳት መንግስቱ” አድርጎ ሊሾማቸው ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ከአገሬ ተቃዋሚዎች ይልቅ ቻይናን ነው የማምነው የሚል ከሆነም (ማለቱ አይቀርም!) እንደ ኩባንያ ማኔጅመንት በኮንትራት አስመጥቶ በ “ረዳት መንግስትነት” ሊያሰራቸው ይችላል፡፡ ምርጫው የሥልጣኑ ባለቤት ነው፡፡ (የኢህአዴግ ማለቴ ነው!)
ሰሞኑን የወጣው “ብሉምበርግ” የተሰኘ የፋይናንስ መጽሔት፤ በአዲስ አበባ ተቋቁሞ ጫማ ስለሚያመርት የቻይና ኩባንያ ያወጣውን አንድ ዘገባ አነበብኩ፡፡ ኩባንያው አሁን 3ሺ500 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በ8 ዓመት ውስጥ የሰራተኞቹን ቁጥር 50ሺ የማድረስ ዕቅድ እንዳለው ቻይናዊው ባለቤት ለብሉምበርግ ገልጿል፡፡ እኔን ያስገረመኝ ግን የአንድ ኢትዮጵያዊ ጫማ ሰሪና የቻይና አቻው የደሞዝ ልዩነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው 40 ዶላር (800 ብር ገደማ) ሲያገኝ ቻይናዊው 400 ዶላር (8ሺ ብር ገደማ) ያገኛል ብሏል - መጽሔቱ፡፡ ኢትዮጵያዊ ጫማ ሰሪ በሰዓት ስንት እንደሚከፈለው ታውቃላችሁ? 25 ሳንቲም ገደማ ነው፡፡ ወይም በቀን 2 ዶላር፡፡ በኒውዮርክ የአንድ ስኒ ቡና ዋጋም 2 ዶላር ገደማ ነው፡፡ አበሻ አገር ጉልበት እርካሽ ነው ወይስ ነፃ? (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!)
ወደ ጉዳያችን እንመለስ ---ኢህአዴግ ለ“ረዳት መንግስትነት” ቻይናዎችን ከመረጠ ጉዳዩን   ከህግ አንፃር መመርመር ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ (ተቃዋሚዎች እቺን ካገኙ እኮ “ለቅኝ ገዢ አገርን አሳልፎ መስጠት” በሚል መንግስትን ሊከሱት ይችላሉ!)
ይሄውላችሁ ---- አንዳንድ ካድሬዎች፤ ደርግና ንጉሱ እንኳን ያለ “ረዳት ገዝተው” የለም ወይ ብለው ሊያሳጡኝ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ግን እኮ ድሮና ዘንድሮ ለየቅል ናቸው፡፡ መቼም 40 ሚ. ህዝብ መምራትና 90 ሚ ህዝብ መምራት አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚያ ላይ የድሮ መንግስታት ሚናቸው የአባትነት ብቻ ነበር፡፡ ኢህአዴግ እኮ የአባትነትም፣ የእናትነትም (“የእንጀራ እናት” የሚሉትም አሉ!) የታላቅ ወንድምነትም፣ የመንግስትነትም ሚና ነው የሚጫወተው፡፡ (“ማን አስገደደው?” ለሚሉ መልስ የለኝም!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህማ “ሥራ ብዙ” ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል ሃዲድና አስፋልት ያነጥፋል (“የመንገድ መንግስት” ሲሉ ሰማሁ ልበል?) በሌላ በኩል ለቤት ፈላጊዎች ኮንዶሚኒየም ገንብቶ ለማስረከብ ደፋ ቀና ይላል፡፡ (በርና መስኮት የለውም ቢባልም!) እዚያ አባይ ማዶ ደግሞ ከግብጽ ጋር ስንት የተባባልንበትን የህዳሴ ግድብ ይገነባል፡፡
ይሄ ሁሉ ሳያንሰው የስኳር ፋብሪካዎችም እሱኑ ነው የሚጠብቁት፡፡ (እሱንስ ለሆላንዶች ሰጥቶ በተገላገለ!) ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ መሰረታዊ የንግድ እቃዎች ከውጭ እያስመጣ “አለ በጅምላ” በተባለው መደብር በኩል ያከፋፍላል፡፡ (ነጋዴን አላምንም ብሎ ነው አሉ!) በዚያ ላይ የፖለቲካ ሥራውም ትንፋሽ ያሳጣው ይመስላል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ ምናምን እኮ አይደለም፡፡ በሽብርተኝነት የጠረጠራቸውን ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያኖች፣ ፖለቲከኞች… ከያሉበት ሰብስቦ ማሰር…ፍ/ቤት ማቅረብ፣ መክሰስ፣ ማስፈረድ፣ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ኮስተር ያለ የአበሻ መልስ መስጠት… ይሄም የመንግስት ሥራ ነው፡፡ ታዲያ … በእሱስ ይፈረዳል? (ቆይ ስንት ቦታ ይሁን?!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል ----- የፈረንጅ መንግስት ቢሆን ገና ድሮ “በቃኝ” ብሎ ራሱን ከስልጣን ያሰናብት ነበር፡፡ የአበሻ መንግስት ግን “ብረት” ነው፡፡ (አበሻ እጅ አይሰጥም!)  በዚያ ላይ ሹመትን የመሰለ ክቡር ስጦታ ጥለን መሄድ ባህላችን አይደለም (የስልጣን ጡር እንፈራለን!) በዚህ መሃል ነው ብዙ ውጥንቅጥ የተፈጠረው፡፡ በዚህ መሃል ነው የውሃ፣ የመብራት፣ የኢንተርኔትና የኔትዎርክ መጥፋትና መቆራረጥ እንዲሁም የትራንስፖርት ችግር መከራችንን ያበሉን፡፡ በዚህ መሃል ነው ብንጮህ ብንጮህ የሚሰማን ያጣነው። (ኢህአዴግ በብዙ የልማት ሥራዎች ተወጥሯላ!) ለዚህ ነው አይፈረድበትም የምለው፡፡ ግን መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ደግሞ “ረዳት መንግስት” ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ከመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች የሸቀጦችን ዋጋ በማናር ኢኮኖሚውን ለግሽበት እንዳይዳርጉት በአንድ ወገን በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ፣ በሌላ ወገን ሸቀጦችን በየመ/ቤቱ አከፋፍላለሁ ብሏል፡፡(ሰሞኑን በደርግ ዘመን የረሳሁትን የቀበሌ ሃሎ ሃሎ ሰማሁ ልበል!)
ወዳጆቼ… ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ብዬ በእርግጠኝነት የምናገረው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ችግሩን ስላየሁለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከሳጥኑ ውጪ (Out of the box እንዲሉ) የሚያስቡ መፍትሔ አፍላቂ አማካሪዎችም መቅጠር ይኖርበታል፡፡ በመንግስት ደሞዝ ሳይሆን ወፈር ባለ ደሞዝ! (የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ምነው ሐምሌን ተሻገረ?) እናላችሁ…ለስንት ዓመት የተወዘፈና ሊፈታ ያልቻለ የችግር ተራራ እኮ እንዲህ በቀላሉ አይናድም፡፡ (ደማሚት ሁሉ ይፈልጋል!)

Read 4034 times