Saturday, 02 August 2014 11:23

ክረምት የሚያወጣውን ምግብ፤ ዳገት የሚያወጣውን ጉልበት ባለቤቱ ያውቀዋል!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(ዘር ያጣን ሸረት፣ አናነ ያጣን ጉርበት፣ አባመታ ይኸን)- የጉራጊኛ ተረት

አንድ የአፍሪካ ተረት እንዲህ ይላል :-
ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ከፍተኛ የመኩራራት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡
ሚስት - “በሩን ዝጋና ተኛ” ትለዋለች ባሏን፡፡
ባል - “አንቺ ምን ሥራ ይዘሽ ነው እኔ በር የምዘጋው!” ይላታል፡፡
የፉክክር በር ሳይዘጋ ያድራል ወደሚለው ተረት የሚያመራ ይሆናል፡፡
ባል በመጨረሻ አንድ ዘዴ አመጣ - ውርርድ!
“ኧረ ካሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ቃል የተነፈሰ፤ በሩን ይዝጋ” አለ፡፡
ሚስትም ተስማማች፡፡
ዝም ዝም ሆነ ነገሩ፡፡
በመካከል አንድ ለማኝ መጣና፤
“ስለማሪያም ተዘከሩኝ” አለ፡፡ መልስ የለም፡፡
“በአምላክ እህል አቅምሱኝ” አለ፡፡
የሚሰማው የለም፡፡
ገባ ወደቤት፡፡ ከዚያ ከብረት ድስቱ ውስጥ ምን የመሰለ አጥንት አግኝቶ መጋጥ ጀመረ፡፡ ባልም እያየ ዝም፡፡ ሚስትም እያየች ዝም፡፡ አንተንፍስ ብለዋላ! በማህል ለማኝ ሃይ የሚለው ስላጣ መጋጡን ቀጠለ፡፡ ለማኙ አጥንቱን ግጦ ሲጨርስ በገመድ አስሮ ሚስቲቱ አንገት ላይ አንጠለጠለው፡፡ እሷ አሁንም ዝም አለች፡፡
ቀጥሎ አንድ ውሻ መጣ፡፡ እሚስት አንገት ላይ የተንጠለጠለውን አጥንት መላስ ጀመረ። ይሄኔ ሚስቲቱ ትዕግሥቷ አለቀና፤
“ሂድ ከዚህ!” ብላ አባረረችው፡፡
ባል - “በቃ ውርርዱን ተሸንፈሻል!” አላት፡፡
ሚስት በመሸነፏ ተናዳ ኩርፊያዋን ቀጠለች፡፡ ራት ሳይበሉ ተኙ፡፡ ባዶ ሆዳቸውን አደሩ።
ጠዋት -
ባል “አየሽ ውድ ባለቤቴ፤ ከሚበልጥሽ ሰው አትወራረጂ፡፡
ትርፉ ጦም ማደር ነው!” አላት ይባላል፡፡
                                                   *    *    *
የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ማለት ይሄው ነው፡፡
“እኔን አይመለከትም፤ ሌላ ሰው ጠይቅ፤ እኔ አልታገልም፤ አንተው እንዳመጣብህ ታገል…እኔ በልቻለሁ፤ ያልበላው መከራውን ይይ…” ዛሬ የሀገራችን ፈሊጥ መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም! እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሀገር ማደጓ ዘበት ነው፡፡ ከጠዋት እስካሁን የምናየው የሀገራችን ሁኔታ ሌላው ሞቶ፣ ሌላው ተሰውቶ፣ የሚፈራውን ፍሬ እኔ ልብላ…ሌላው በቆሰለ በታሰረበት እኔ ስሜ ይጠራ፣ እኔ ዝና ላፍራበት ማለት ባህላችን እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡
በመሠረቱ “ሁሉ ኮርቻ ላይ ከወጣ አለንጋ ማን ሊይዝ ነው?” እንደተባለው፤ ፈረሱን የሚነዳ፣ የሚለጉምና የሚያራግፍ እንዳይጠፋ ያሰጋል፡፡ ሁሉ ፖለቲከኛ፣ ሁሉ ተናጋሪ፣ ሁሉ እኔ ነኝ የሀገር ጉዳይ የሚያገባኝ ካለ፤ ፖለቲካል ሳይንስ የተማረ ሁሉ መቅለጡ ነው በአንፃሩ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” ለማለት የሚቸኩል ፖለቲከኛ የበዛበትም አገር ከፍሬው ገለባው ይበዛል፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን በምኒልክ አንደበት እንዲህ ይለናል፡-
“…አየህ እያሱ…ያገርህን ያበሻን ቤት አሰራር ተጨባጭ አገነባብ ባጭር ምሳሌ ላስተምርህ። ያበሻ ቤቱ፣ ያበሻ ጣራው ምሰሶ ጉልላቱ፣ ያበሻ ማዕዱ፣ ምድጃና መሶቡ፣ ያበሻ አውድማው አዳራሹና አደባባዩ እንደፀሐይ ክብ ብርሃን ጮራ እንደቀለበት የሕብር ዙሪያ እንደ ክበብ ነው…ባህልህን አስጠንቅረህ ካላወቅህ አገርህም አያውቅህ! ሕዝብህንም አታውቀው! ሕዝብህን ማወቅ ማለት የህዝብህን የባህል ብልት ጠንቅቀህ መገንዘብ ነው፡፡ ህዝብህን ማወቅ ደግሞ አገርህን ማወቅ ነው፡፡ ማንነቱን ያላጤንክለትን ሕዝብ ነገ ማስተዳደሩ ያቅትሃል እያሱ፡፡”
የሕዝብ ባህሉ እስትንፋሱ ነው፡፡ መናገሩ ነው፡፡ እንደልቡ መሆኑ ነው፡፡ ተናገር ብለህ “ቀስቅሰክ” ብለህ አትከሰውም፡፡ አለበለዚያ አገር የለውም፡፡ የህዝብ መብት ማንም እንዳሻው የሚቀለብሰው፣ እንዳሻው ዳር ድንበሩን የሚወስነው አሊያም “የአተረጓጐም ጉዳይ ነው” እያለ እንዳመቸው የሚያጣምመው አይደለም፡፡
አብዛኛው ነገረ - ሥራችን “ሲያቃጥል በማንኪያ ሲበርድ በእጅ” ዓይነት የሆነው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ “ከባዕድ ወስደህ ወደዘመድህ ዞረህ ጉረስ”ም ሌላው ፈሊጣችን ነው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በፊት ሁነኛ ተቃዋሚ አጣን ይሉ የነበሩ፤ ተቃዋሚ ሲመጣ የአገር እንቅፋትና አሽክላ እንደፈጠሩ አይተናል፡፡ ተቃዋሚ ሲጠፋ በራሳቸው ማህል የተቃውሞ አውሎ - ንፋስ አስነስተው ተከፋፍለው፤ ተሰነጣጥቀው፤ እርስ በርስ ጐራ ለይተው ግራና ቀኝ ተባብለው እንደተጠፋፉም ታዝበናል፡፡ በራሳቸው ዕብጠት ወደ መፈንዳት የሄዱም እንደነበሩ ምስክር ሆነናል፡፡ ግራና ቀኝ መንገደና ተባበለው መፈረጃቸውንም ሰምተናል፣ አይተናል፡፡ ሁሉንም ጉልበተኛ እስኪውጣቸው “ዲሞክራሲ የእኛ ብቻ ናት”፤ “እንደኛ ፕሮግራም የሚጥም የትም አይገኝም!”፤ ‹እንደኛ ምርጫ “Fair” and “Free” የትም የለም› ይላሉ፡፡
ታሪክ ግን ታሪክ ሆነው እንደሚቀሩ ይዘግባል፡፡ ንድፈ - ሀሳብ ቀማሪዎቻቸውም ሆኑ አፈ - ጉባኤዎቻቸው፤ ወሬ አንጓቾቻቸውም ሆኑ ወናፎቻቸው ወይም መለከተ - ጥሩምባዎቻቸው ደሞ ለሌላ መንግሥት ማንባረቃቸውን፣ ማናፈታቸውን መቀጠላቸውንም ልብ እንላለን፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን ህዝቡ፣ ባለ ይዞታው፣ ባለ አገሩ፤ “ክረምት የሚያወጣውን ምግብ፣ ዳገት የሚያወጣውን ጉልበት፤ ባለቤቱ ያቀዋል” የሚለው የጉራጌ ተረት ደርዙ ይሄ መሆኑን ያቃል!!

Read 4724 times