Saturday, 02 August 2014 11:07

አረና ፓርቲ ተከፋፈለ መባሉን አስተባበለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   አረና ፓርቲ ተከፋፈለ ሲል የዘገበው አፍሪካን ኢንተለጀንስ ዶትኮም፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የተወሰኑ አባላት ራሳቸውን ከፓርቲው እንዳገለሉ ቢናገሩም የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ በፓርቲው ውሳኔ መባረራቸውን እንደገለፀ ትላንት ጠቆመ፡፡ አረና በበኩሉ፤ ፓርቲው ተከፋፈለ መባሉን አስተባብሏል፡፡ በፓርቲው ውስጥ የስነ ምግባር ጥሰት የፈፀሙ አባላት ላይ በፓርቲው ህገ-ደንብ መሰረት የተወሰነ ቅጣት ከመጣሉ በስተቀር ፓርቲው በምንም ሁኔታ የመከፋፈል ችግር ውስጥ አልገባም ሲሉ የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በርሄ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

“አባላቱ የዲሲፕሊን ቅጣት የተጣለባቸው የፓርቲውንና የአመራሩን ስም ወደማጥፋትና ወደ አላስፈላጊ አሉባልታ በመግባታቸው ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ እነዚህ የአመራር አካላትና አባላት፣ ፓርቲውን የሚጉዳ ሴራ እንደፈፀሙና በወንጀልም ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል በግምገማ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ “አንድ ተራ አባል፤ የፈፀመው ጥፋት ከፓርቲው እስከማባረር የሚደርስ በመሆኑ የስራ አስፈፃሚው እንዲባረር ወስኖበታል” ያሉት የአረና ሊቀመንበር፤ አንድ የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚቴ አባል ደግሞ ጉዳዩ በቁጥጥር ኮሚቴው እንዲታይ ከተደረገ በኋላ ፓርቲው የሚቀጥለውን ጉባኤ እስኪያካሂድ ድረስ ከቁጥጥር ኮሚቴው አባልነቱ ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡

በዲሲፕሊን ጥሰት የተገመገሙ ሁለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጉዳያቸው በማዕከላዊ ኮሚቴው እንዲታይ ከተደረገ በኋላ፣ ሺሻይ አዘናው የተባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በፓርቲውና በአመራሩ ላይ ያደረሰውን ስም ማጥፋትና አሉባልታ እንዲያስተባብል የ14 ቀን ጊዜ እንደተሰጠው የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ ግለሰቡ ከጥፋቱ ሊታቀብ ቀርቶ በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ቢሄድም ውሳኔ ለመወሰን፣ የተሰጠው የጊዜ ገደብ እስኪጠናቀቅ እየጠበቁ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ይሄው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የፓርቲውን ስም ከማጥፋቱም ባሻገር ለሁለት አመት የአባልነት መዋጮ አለመክፈሉ፣ እንዲሁም በተመደበበት ኃላፊነት ላይ በአግባቡ እየሰራ አለመሆኑ በግምገማ ተረጋግጧል” ብለዋል - አቶ ብርሃኑ፡፡

ሌላው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መምህር ታደሰ ቢተውልኝ፤ በስራውና በፓርቲው ላይ እያሳየ ባለው የስነ-ምግባር ጉድለት ቀላል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ሊቀመንበሩ ጠቁመው፤ “ለምን ማስጠንቀቂያ ይሰጠኛል” በሚል የፓርቲውን መታወቂያ ቢሮ ጥሎና ተቆጥቶ መሄዱን ተናግረዋል። “የተባረረው ተራ አባልም ቢሆን ዓምና በተደጋጋሚ በፈፀመው ጥፋት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እንደነበር ያብራሩት አቶ ብርሃኑ፤ “ከላይ በተዘረዘሩት ጥፋቶች የተባረሩና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የፓርቲው አመራሮችና አባላት “አረና ተከፋፈለ፤ ተሰነጣጠቀ” በሚል በየፌስቡኩና በየዌብሳይቱ ቢያስወሩም ፓርቲው ግን ህግና ደንቡን ተከትሎ በተጠናከረ ሁኔታ ስራውን ቀጥሏል” ብለዋል፡፡ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ግለሰቦቹ በሚያስወሩት አሉባልታ መደናገር ሳይሰማቸው ስራቸውን በአግባቡ እንዲቀጥሉም አሳስበዋል - የፓርቲው ሊቀመንበር፡፡

Read 4025 times