Print this page
Tuesday, 29 July 2014 15:01

የጎንደር ታሪክ በተመራማሪው ዓይን

Written by 
Rate this item
(22 votes)

ባለፈው ሳምንት በጎንደር የቅማንቶች መብት ተሟጋች ከሆኑት ከአቶ ነጋ ጌጤ ጋር ባደረግነው ቃለ-ምልልስ “ጎንደር የቅማንቶች ናት” በማለት ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው አቶ ሲሳይ ሳህሌ በጎንደር ታሪክና ሥልጣኔ ዙሪያ የሰጡንን ማብራሪያ እናቀርባለን፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ቃለ-ምልልስ ያደረገላቸው የታሪክ ተመራማሪ፣ የፈረንሳይ ከተማ “ቬንሰንት - ጎንደር ያልተማከለ የትብብር ስምምነት የራስ ግንብ ሙዚየም ፕሮጀክት አስተባባሪም ናቸው፡፡

 ጎንደር እንዴት ተመሰረተች?
በ1623 ሰኔ ወር ላይ አፄ ሱንስዮስ ለልጃቸው ለአፄ ፋሲል በህይወት እያሉ ስልጣናቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሜንዴዝ የሚባል የካቶሊክ ሚሽነሪ መጥቶ ነበር፡፡ አዘዞ (አሁን አፄ ቴዎድሮስ ኤርፖርት ያለበት ቦታ)፣ ጎርጎራ እና ደንቀዝ የሚባሉ ቦታዎች ሶስት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች ተሰርተው ነበር፡፡ ደንቀዝ ላይ ያለው እንደ ቤተመንግስትም ያገለግል ነበር፡፡ አፄ ሱስንዮስ ስልጣናቸውን አስተላልፈው ያረፉትም በዚሁ የካቶሊክ ደብር ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አፄ ፋሲለደስ የህዝቡን ፍቃድ ለማሟላት ኢየሱሳውያኑን ከሃገር አባረሩ፡፡ ስልጣናቸውን ተቀብለው አፄ ከተባሉ ከ4 ዓመታት በኋላ አሁን ቤተመንግስታቸው ከሚገኝበት ቦታ መጥተው የዛሬዋን ጎንደር ሊመሰርቱ ችለዋል፡፡
ለምን ወደ ጎንደር መምጣት አስፈለጋቸው? እዚያው አባታቸው የነበሩበት ቦታ ላይ መንግስታቸውን መመስረት አይችሉም ነበር?
በሶስት ምክንያቶች ነው እንደዚያ ያደረጉት። አንደኛው ከእምነት አንፃር፣ ጎርጎራ ካቶሊካውያኑ የነበሩበት ቦታ ስለነበር የረከሰ ነው ተብሎ ታመነ። ስለዚህ አዲስ ቦታ መቀየር አስፈለጋቸው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት፣ ጎርጎራ ወባማ አካባቢ ስለነበር ሰራዊታቸውን ፈጀባቸው፡፡ እናም ከጤና አኳያ የአሁኑ ጎንደር ተመራጭ ሆነ፡፡ ሦስተኛው ምክንያት፣ ጎንደር ወይና ደጋ አየር ንብረትና ከ40 በላይ ምንጮች ያላት ነበረች፡፡ በወንዞችም የተከበበች በመሆኗም የሰራዊቱን የውሃ ፍላጎት ታሟላ ነበር፡፡
አሁን ቤተ መንግስቱ ያለበት ቦታ 2200 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ዙሪያውን ደግሞ እስከ 3 ሺህ ሜትር ከፍታ ያላቸው ተራራዎች አሉ። እነዚህ ተራራዎች የአየር ወለድ በሽታ ቢመጣ ወደ ከተማዋ አያስገቡም/አያሳልፉም ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከጦር ስትራቴጂ አንፃርም በተራራ መከበቧ ጠላት በቀላሉ እንዳይገባ ይከላከላል፡፡ ተራራዎቹ በትልልቅ ዛፎች የተጠቀጠቁ መሆናቸውም የማገዶ ፍጆታን ያሟላሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንቶች ጎንደር በ1628 ዓ.ም ተመሰረተች፡፡
አፄ ፋሲለደስ በ1660 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የጎንደር ህዝብ ብዛት 27 ሺህ ደርሶ ነበር። ይሄ የሚያሳየው ከተማዋ በወቅቱ እጅግ ሰፊ መሆኗን ነው፡፡ በእነ እቴጌ ምን ትዋብ ዘመን ደግሞ የህዝብ ብዛቱ እስከ 100 ሺህ ደርሶ ነበር፡፡
ከብሄር፣ ከሃይማኖት አንፃር ምን አይነት ማህበረሰብ ነበር የሚኖርባት?
እንደውም ጎንደርን በወቅቱ ከነበሩት የሃገሪቱ አካባቢዎች ለየት የሚያደርጋት ቤተ እስራኤሎች፣ ባህላዊ እምነት ተከታዮች፣ ሙስሊሞች፣ የውጭ ዝርያ ያላቸው ቱርኮች… ሁሉም አንድ ላይ እንደልባቸው ተስማምተው የሚኖሩባት መሆኑ ነበር፡፡ በተለያዩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ይኖሩባት ነበር፡፡ አናፂዎች፣ ግንበኞቹ፣ ሸማ ሰሪዎች፣ የብረታ ብረትና የወርቅ ስራ የሚሰሩ እንዲሁም ነጋዴዎች ሁሉ አንድ ላይ ይኖሩባት ነበር፡፡ በጊዜው ንግዱን በሚገባ ያውቁታል ተብሎ ስለሚታመን ነጋድራሶች ከሙስሊሞች ነበር የሚመረጡት፡፡
አፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግስታቸውን ካሳነፁ በኋላ በዙሪያው ሰባት ቤተ-ክርስቲያኖችን አሰርተዋል፡፡ በየጊዜው ነገስታቱ እየተተኩ ለ120 ዓመታት እጅግ የረቀቀ የህንፃ ግንባታ ጥበብን ሰርተው አልፈዋል፡፡ የጎንደር ስልጣኔ የመጨረሻዋ ንግስት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብም የራሳቸውን ቤተ-መንግስትና ቤተ-ክርስቲያን አሳንፀዋል ቁስቋም ትባላለች፡፡
አፄ ፋሲል ለምን 7 ቤተ-ክርስቲያናትን በዙሪያቸው አሰሩ?
በወቅቱ እንደሚታወቀው ነገስታቱ በእምነታቸው ጠንካሮች ነበሩ፡፡ የጊዮርጊስ ታቦት ዘማች ታቦት ነው፤ ተዋጊ ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት ጊዜም ቢሆን አፄ ምኒልክ ይዘው ዘምተዋል። የድንግል ማርያም ደግሞ ከንግስቲቱ ማረፊያ ቤት አጠገብ እንድትተከል ተደርጓል፡፡ ከትውፊቱ ከተቀበልነው ታሪክ እንደምንረዳው፣ አፄ ፋሲል ቤተ መንግስታቸውን ሲገነቡ አውሬ ሲያስቸግራቸው ባህታውያን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን ታቦትን ትከል ብለው ሲመክሯቸው ያንን አደረጉ፡፡ መብረቅ ሲያስቸግራቸው የቅዱስ ሚካኤልን ታቦት፣ በሽታ ሲያስቸግራቸው የዓለም መድኀኒት የሆነውን የመድኀኒዓለም ታቦት እንዲተክሉ ተመከሩ፡፡ በዚህ ሂደት ነው ደብራቱን በዙሪያቸው የተከሉት ተብሎ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል በወቅቱ ካቶሊኮች ተባረው “ፋሲል ይንገስ ሃይማኖት ይመለስ” ተብሎ ሲታወጅ፣ አፄው ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ፅናት ለማሳየት በርካታ ቤተ-ክርስቲያናትን እንደተከሉ ይታመናል፡፡
በዚያን ጊዜ የቤተ-መንግስቱ የአኗኗር ስርአት ምን ይመስል ነበር?
በአጠቃላይ የቤተ መንግስቱ ቅጥር ግቢ 70 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው ያረፈው፡፡ 12 በሮችም አሉት፡፡ ወደ ቅፅሩ የሚገባው እንደየደረጃውና ማዕረጉ በሚፈቅድለት በር ብቻ ነው፡፡ ራስች በር - ራሶች ብቻ የሚገቡበት ነው፣ የንጉሱ በር (ጃንተከል በር) ንጉሱ ብቻ የሚገቡበት ነው፡፡ ግምጃ ቤት በር የሚባል አለ - የግምጃ ቤት አስተናባሪዎች የሚገቡበት ነው፡፡ ቀጭን አሸዋ በር የሚባል አለ ይህ የግንባታ እቃዎች የሚገቡበት በር ብቻ ነው፡፡ እርግብ በር የሚባለው ደግሞ የደናግላን እና የመነኮሳት በር ነው፡፡ እንቢልታ ነፊዎች ብቻ የሚገቡበት ደግሞ እንቢልታ በር ይባላል፡፡ በሃዘን ጊዜ ሃዘንተኞች የሚገቡበት በር ተዝካሮ በር ይባላል፡፡ ተዝካሮ በር ፊት ከቤተመንግስቱ በስተደቡብ ባለው አነስተኛ ሜዳ ላይ አስከሬን ተቀምጦ ይለቀሳል፡፡ በጥንቱ የጎንደር ባህል ቦታው ሰዎች ሲሞቱ አስከሬናቸው ተቀምጦ ረዘም ላለ ሰአት ለቅሶና የሽኝት ስነ ስርዓት የሚከወንበት ነው፡፡ ባልደራስ በር የሚባለው ደግሞ ፈረሰኞችና የፈረሰኛ አዛዥ በር ነው፡፡ የንጉሱ ፕሮቶኮሎች የሚገቡበት በር ደግሞ “ኳሊ” በር ይባላል፡፡ በዚህ በኩል ባለጉዳዮችም ሆኑ የንጉሱ የቅርብ አጋዞች ይስተናገዱ ነበር፡፡
ንጉሡ በወቅቱ የከተማውን ህዝብ ግብር ያበሉ ነበር?
እንግዲህ በኢትዮጵያ ታሪክ ንጉሱ ግብር ካላበላ ምኑን ንጉስ ሆነው ይባል ነበር፡፡ ግብር ማስገበርም አለበት፡፡ ግብር በወርቅ፣ በብር፣ በከብት፣ በአሞሌ፣ በጥይት በመሳሰሉት መልክ ከነዋሪው ይሰበሰባል። ንጉሱ ደግሞ በምትኩ ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ግብር ሰብስቦ በየጊዜው ያበላል፡፡ ራሶችና መኳንንቶችም በየአውራጃቸው ላለ ህዝብ ግብር ማብላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብር ሲበላ ሰው እንደማዕረጉ ነው የሚቀመጠው፡፡ መጀመሪያ ንጉሱ ይቀመጣሉ፤ ከዚያ ንግስቲቷ ይቀጥላሉ፣ እጨጌውና የአክሱም ንቡረ ዕድ ይከተላሉ፡፡ እንዲህ እንዲያ እያለ መኳንንቱ በየደረጃቸው ይቀመጣሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከፋሲካ በኋላ ነው ግብር የሚበላው፤ በበአላትም እንደአስፈላጊነቱ ንጉሱ ደግሶ ህዝቡን ያበላል፡፡  
ዳኝነት እና ፍርድስ እንዴት ነበር የሚከናወነው?
ዳኝነት እሚሰጠው እምነትን መሰረት በማድረግ ነበር፡፡ የእምነት ወይም ከፍተኛ ሃገራዊ ጉዳይ ከሆነና በመኳንንቱ መወሰን የማይችል ከሆነም ዙፋን ችሎት ላይ ይቀርባል፡፡ በእምነት ጉዳይ ክርክር ስለመካሄዱ ሁሌም በምሳሌነት የሚጠቀሰው የአልፈንዞ ሜንዴዝ እና የእጨጌ ጊዮርጊስ ክርክር ነው፡፡ በወቅቱ አልፈንዞ ሜንዴስ ከእጨጌው የሚቀርብለትን መከራከሪያ መመለስ አቅቶት ነበርና አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው። “ስላሴዎች ሁል ጊዜ ፀጉራቸውን የማይላጩት ለምንድን ነው?” በማለት እሳቸውም “አንተ ቅንድብህን ትላጨዋለህን?” ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት፡፡ ቀጥሎም “የአብ ፊቱ ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡ እሳቸውም ጧፍ አበሩና “የዚህ መብራት ፊቱ ወዴት ነው?” አሉት፡፡ መልስ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ፊት በሁሉም አቅጣጫ ነው ብለው ክርክሩን ረቱት ይባላል፡፡
ከፋሲል በኋላ አፄ (ፃድቁ) ዮሐንስ ነበሩ፡፡ እሳቸው የእንስሳትን መብት እስከማስጠበቅ የደረሱ ሰው ናቸው፡፡ ከደግነታቸው ብዛት ትልቅ ደውል በውጨ በኩል አስተክለው ነበር፡፡ ዳኝነት ጎደለብኝ ተበደልኩ የሚል ሰው መጥቶ ይደውላል፡፡ ከዚያም ይገባና ከንጉሱ ዘንድ ፍርድ አግኝቶ ይሄዳል፡፡ አንድ ጊዜ ምን ሆነ፡- ዝናብ እየዘነበ ነበር፡፡ ደውሉ ይደወላል፡፡ በዚህ ዝናብ ማን ፍርድ የጎደለበት ይሆን የመጣው ብለው እልፍኝ አስከልካያቸውን ይልኩታል፡፡ “ኧረ ጃንሆይ  አህያ ነው እንጂ ሰውስ የለም” ይላቸዋል፡፡ አህያውን አስገባው አሉት፡፡ አህያው ሲታይ ጀርባው ተጋግጧል፡፡ ባለቤቱ ተፈልጎ ይቅረብ ተባለና መጣ፡፡ “ለምን እንዲህ አደረክ፣ እድሜ ልኩን ያገለገለህን አህያህን ለምን ጣልከው?” ሲሉ ሰውየውን ገስጸው ቀጥተው ላኩት፡፡ አህያው ደግሞ በቤተ መንግስት ውስጥ ገብስና ባቄላ እየበላ እንዲኖርና ከቁስሉ እንዲያገግም ተደረገ፡፡ በዚያውም “የተገጠበ አህያ ጭነት እንዳይጫን” የሚለው አዋጅ ታወጀ፤ ጭኖ የተገኘም ይቀጣ ነበር፡፡ ያኔ ነው የእንስሳት መብት የታወጀው፡፡
ጎንደር የ44 ታቦታት መገኛ ሲባል ምን ማለት ነው?
ጎንደር ከመመስረቷ በፊት በአካባቢው አራት ደብሮች ነበሩ፡፡ አንደኛው አርባዕቱ እንስሣ ይባላል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ቃአ ኢየሱስ የሚባል አለ፡፡ ጊዮርጊስ በሌላ አቅጣጫ አለ፤ አበራ ጊዮርጊስ የሚባልም አለ። ከዚያ በኋላ አፄ ፋሲል 7 ተከሉ፡፡ ፃድቁ ዮሐንስ 2 ተከሉ፣ አድያም ሰገድ ኢያሱ ደብረ ብርሃን ስላሴ ጨምሮ 2 ተከሉ፡፡ እንዲህ እንዲያ እያሉ ነገስታቱ በተፈራረቁ ቁጥር አዳዲስ ደብሮችን ሲተክሉ ኖሩ። በዚህ ሂደት በእነዚህ ነገስታት 30 ተተከሉ። 14 ያህሉ ደግሞ ቀድሞም የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተደምረው ጎንደር የ44 ታቦት መገኛ ሃገር ተባለች፡፡ ኋላ ላይ በደርቡሽ ጦርነት 4 ያህሉ ተቃጥለው ነበር፡፡ ሃገሬው የተቃጠሉትን እንደገና ሰርቷቸው ነበር፡፡ አሁን ሁለቱ እየተሰሩ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ደብሮች በብዛት የተተከሉ ቢሆንም የጥንቱን የጎንደር ስልጣኔ ለማስታወስ 44ቱ ታቦታት የጎላ ቦታ አላቸው፡፡
ጎንደር የሚለው ስያሜስ ከየት የመጣ ነው?
ብዙ አፈታሪኮች አሉ፣ ነገር ግን ዋናው ማየት ያለብን የታሪክ ጥራዞችን ነው፡፡ የአፄ አምደፅዮን ዜና መዋዕል ላይ “ጎንደር” የሚለው ስም ሰፍሯል። ጎንደር ከመመስረቷ ከ300 ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ወደ አፈታሪኩ ስንመለስ ቃሉ የማን እንደሆነ ባይታወቅም ጉንዳ ሃገር ወይም ትልቅ ሃገር ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጓንግ እና ዳራ ከሚሉ ሁለት ቃላት የመጣ ሲሆን በአንገረብ እና ቃሃ ወንዝ መካከል ስላለች ነው ይህ ስም የተሰጣት ይላሉ፡፡ ግን የተጨበጠ ነገር የለውም፡፡
ነገስታቱ ይህን የቤተመንግስቱን ቦታ ከመያዛቸው በፊት ቦታው ላይ ምን ነበር?
እንደ አፈታሪክ እዚህ ቦታ ላይ (አሁን ቤተመንግስቱ ያለበት) ውሃ ነበር ይባላል፡፡ ውሃውን አድርቀው ቤተ መንግስታቸውን ሰሩ፤ አንዳንድ ታሪክ ደግሞ ቦታው የባላባቶች/የእርሻ ቦታ ነበር ይላሉ። ሌሎች አፈታሪኮች አፄ ፋሲል አደን ወጥተው አንዳንዶች ጎሽ ይላሉ ሌላው አንበሳ ይላል እያባረሩ መጥተው እዚህ ቦታ ሲደርሱ ተሰወረባቸው፤ ባህታዊ ተገልጦ ቤተ መንግስትህን የምትሰራበት ቦታ ይሄ ነው ብሎ ነገራቸው ይባላል፡፡ ከዚያ በፊት መላዕኩ ራጉኤል “ጎ” የሚባል ቦታ ላይ ትነግሳለህ ብሎ በራዕይ ይነግራቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ “ጎ” ሲላቸው ቦታውን ፍለጋ ጎዛራ፣ ጎጃም፣ ጎርጎራ ሄደው በመጨረሻ ጎንደር ፀንቶላቸዋል ነው የሚባለው። ነገር ግን በዚህ አካባቢ አድባራት በፊትም መኖራቸውን ስናይ ሰዎች ይኖሩበት እንደነበር ያመላክተናል፡፡
የኖህ መቃብር ነው የሚል ታሪክም ይነገራል?
ሰዎች የራሳቸውን ታሪክ ይዘው ሊነሱ ይችላሉ። እኔም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ነገር ሰእየሰማሁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በ1960ዎቹ የተፃፈ አንድ ታሪክ የሚያሳየው፤ ፋሲል ቤተመንግስቱን እንደ ኖህ መርከብ አድርጎ እንደሰራው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ታሪክ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፤ ግን ሰፊና ጥልቀት ያለው ጥናት ይፈልጋል፡፡
በ150 ዓመታቱ የጎንደር ስልጣኔ ከታዩ ዘመናዊ ነገሮች ጥቂቶቹን ቢጠቅሱልን…
የቤተ መንግስቱ የህንፃ ጥበብ ዋናው ነው፡፡ አንዳንዶች የውጭ ሰዎች እጅ አለበት ይላሉ፤ ነገር ግን አሰራሩ በፊትም በአክሱም ዘመነ መንግስት የነበረ ነው፡፡ ህንዳውያንም ሆነ ፓርቹጋሎች ከመምጣታቸው በፊት እንደነበር ይናገራል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1563-97 ዓ.ም የነገሱት አፄ ሰርፀድንግል ቤተ መንግስታቸው እንፈራዜ የምትባል ቦታ (ከጎንደር ወደ ባህርዳር ሲሄድ 60 ከሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ) ላይ የሚገኝ ቤተ መንግስት ላይ ይህ ቴክኖሎጂ ተሰርቶበታል፡፡ ስለዚህ የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት የተባለው አያሳምንም፡፡
ሌላው ግዙፍ የሆኑ የንግድ መስመሮች - እስከ አውሮፓ፣ ኤሽያ የሚዘልቁ ተፈጥረው ነበር፡፡ የቤተ መንግስቱን አኗኗር ካየን ደግሞ ዘመናዊ ነበር፡፡ ዛሬ ፋሽን የምንለው… በዚያን ጊዜ ቀጭን ፈታዮች በሚባሉ ባለሙያዎች ለቤተ መንግስቱ ወይዛዝርት በየአይነቱ አልባሳት እየተሰሩ ያንን ፋሽን ይከተሉ ነበር፡፡ ዛሬ “ስቲም” የምንለው ያኔ “ወሸባ” ይባል ነበር፡፡ የፀጉር፣ የንቅሳት አይነት እንደፋሽን ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ዶሮ አስራ ሁለት ብልት አላት እንላለን። ያ መለኪያ የወጣው በወ/ሮ ምንትዋብ ጊዜ ነው። የዓሣ አሰራርና የተለያዩ የምግብ አሰራሮች ያኔ የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ስርአት እንግዲህ ወደ ከተማው ተስፋፍቷል፡፡ እኛ ዛሬ የተጣራ ውሃ እያልን የታሸገ ውሃ እንጠጣለን፡፡ ይሄ በዚያን ጊዜም ይደረግ ነበር። የፈረስ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ዛሬ የመኪና ፓርኪንግ እንደምንለው በአፄ በከፋ ዘመን ባለ ዘጠኝ በር ዘመናዊ የፈረስ ማቆሚያ /ፓርኪንግ/ ተሰርቶ ነበር፡፡ እንግዶች ፈረሶቻቸውን እዚያ ነበር የሚያቆሙት፡፡
በ5 ዓመት የጣሊያን ወረራ ቤተ መንግስቱ ለጣሊያን ገዢዎች መቀመጫነት አገልግሏል ይባላል?   
በሚገባ አገልግሏል፡፡ እንዲያውም ጣሊያን ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ ነበር የሚያስተዳድረው። ከጃን ተከል በታች ያለው የሃገሬው ወይም የሃበሻ መንደር ነበር፡፡ አሁን ፒያሳ የምንለው ደግሞ የጣሊያኖች ነበር፡፡ ያኔ ሃበሾች ወደ ነጮች መንደር መዝለቅ አይፈቀድላቸውም፡፡ በቤተ መንግስቱ ውስጥም ለግብር በሚቀመጡበት ወቅት ነጮቹ በተመረጠ ቦታ ሃገሬው በሌላ ቦታ ሳይቀላቀሉ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ምግብ ሲቀርብም ነጮቹ በስርአቱ ይመገባሉ፡፡ ሃበሾቹ ተሻምተው እንዲመገቡ ይደረግ ነበር፡፡ ጣሊያን ቤተ መንግስታቱ በጥቁሮች መሰራታቸውን አምኖ ላለመቀበል “የፖርቹጋል ግንቦች” ይላቸው ነበር፡፡ የከተማዋን ስያሜዎችም በብዛት ቀይሮ ነበር፡፡
ጃንተከል ዋርካ ዝነኛ ነው፤ ስለሱ ታሪክ ይንገሩን…
ጃንተከል እንግዲህ አፄ ፋሲል ተከሉት ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚያም ነው ጃንሆይ የተከሉት ለማለት ጃን ተከል የተባለው፡፡ በወቅቱ የሃገር ሽማግሌዎች በስሩ ተቀምጠው ይወያዩ ነበር፡፡ ስቅላትን የመሳሰሉ ፍርዶችም ይፈፀሙበት እንደነበር በስፋት ይነገራል።

Read 18292 times
Administrator

Latest from Administrator