Tuesday, 29 July 2014 14:54

ጫማ ምን ክብር ቢኖረው፣ ሁል ጊዜ ከእግር ሥር ነው! የትግሪኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ የአፍጋኒስታኖች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ሚስቱ ድርስ-እርጉዝ ሆና ስለነበር ለሚወለደው ወይም ለምትወለደው ልጅ አልጋ ሊያሰራ፤ ወደ አልጋ ሰሪ ሄደ፡፡  ያ አልጋ ሰሪ አናጢ፤
“ምን ፈልገህ ወደኔ መጣህ?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“ለልጄ አልጋ ላሰራ ፈልጌ ነው” ይላል አባት፡፡
“መልካም፡፡የህፃን ልጅ አልጋ ግምቱ የታወቀ ስለሆነ አሳምሬ እሰራልሃለሁ” አለው፡፡
አባት፤ በጉዳዩ ተስማምቶ፤
“በል እንካ ቃብድህን፡፡ አደራ ደህና አድርገህ ስራልኝ” ብሎ ገንዘቡን ሰጠው፡፡
አባት የልጁ መወለድ እየቀረበ ስለመጣ ወደ አናጢው እየሄደ፤
“እህስ፤ ምን አደረስክልኝ?” ይለዋል፡፡
“ቆይ ትንሽ ጠብቅ” ይላል አናጢ፡፡
አባት ሌላም ቀን ይመጣል፡፡
የአናጢው መልስ፤
“ቆይ ትንሽ ጠብቀኝ” ሆነ፡፡
በዚህ ማህል ልጁ ተወለደ፡፡ አደገ፡፡
ጎረመሰ፡፡ ጎለመሰና ሚስት አገባ፡፡ ሚስቱ ፀነሰች፡፡ አረገዘች፡፡
ልጁ እንግዲህ አባት ነውና፤ ኃላፊነት አለበትና፤ ወደ አባቱ ሄዶ፤
“አባቴ ሆይ! መቼም አንተ ልምድ አለህና ለሚወለደው ልጄ አልጋ ከየት እንደምገዛለት ንገረኝ?” አለው፡፡
አባትየውም፤
“የውልህ ልጄ! የዛሬ ሃያ ዓመት፤ ለአንድ አናጢ አንተ ስትወለድ የምትተኛበት አልጋ ላሰራ ቀብድ ሰጥቼው ነበር፡፡ ሂድና አልጋው አልቆ ከሆነ፤ ቀሪውን ከፍለህ አልጋውን አምጣና ልጅህ ይተኛበታል!” አለው፡፡
ልጅየውም ተደስቶ ወደ አናጢው ሄደና፤
“ጌታው፤ ከዚህ ቀደም አባቴ አልጋ ሊያሰራ ገንዘብ ከፍሎህ ነበር፡፡ እሱን ለመውሰድ ነበር የመጣሁት”
አናጢውም፤
“እናንተ ሰዎች አልጋ በጥድፊያ አይሰራም፡፡ አትጨቅጭቁኝ፡፡ አታጣድፉኝ፡፡ እኔ የጥድፍ ጥድፍ ስራ አልወድም፡፡ ካልፈለጋችሁ ገንዘባችሁን ልመልስላችሁ እችላለሁ!” አለ፡፡
                                               *            *              *
ለልጅ አልጋ ማሰራተን የመሰለ ቁምነገር የለም፡፡ ትውልድን እንደመታደግ ነው፡፡
ከሃያ ዓመት በኋላ “አታጣድፉኝ!” ከሚል ይሠውረን!
የአልጋ ነገር ሁሌም አሳሳቢ ነው፡፡ አዲስ ህፃንም ይተኛበት የቆየ፤ ችግር አያጣውም፡፡ አልጋ ሲሰራ ጥድፊያ አይወድም፡፡ ሃያ ዓመት ቢፈጅም ጥድፊያ አይወድም፡፡ ሰሪውም በቀላሉ አይለቅም! “የጥድፊያው ጥቅም ለሠሪው ነው ለአሠሪው?” ነው ጥያቄው፡፡ ማስተዋልን የመሰለ ነገር የለም ዞሮ ዞሮ፡፡
ምንም ሆነ ምን ድህነትን ማሸነፍ ግዳችን ነው! “ነጭ ደሀ ነጭ ብር ይወልዳል” ቢሉም አበሳውን ማስታወስ ተጨምሮ መሆን አለበት፡፡ ቢያንስ እንደ ፀሐፌ-ተውኔት “ስደተኛ ዘላን ሶማሌ በሄደበት ሣር ወይም አሣር ይጠብቀዋል” የሚል የአምሣ ባምሳ ግምት (Probability) ፈጥሮ ስለአገር ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ ምሁሩም፣ መሀይሙም፣ ጠቢቡም፣ ግብዙም ስለአገር ጨለምተኛ (Pessimist) ሆኖ የትም አንደርስም!!
እንደሌላው ዓለም ሁሉ፤ ያለጥርጥር ልማት በኢትዮጵያ፤ ሂደት እንጂ ግብ ብቻ አይደለም፡፡
የጥንቱን የጠዋቱን የሀገራችንንና የውጪውን አገር ልማታዊ መንፈስ እንድናይ ይረዳን ዘንድ ጸጋዬ ገ/መድህን በምኒልክ አንደበት የሚከተለውን ይለናል፡-
“አውሮጳውያን የእጅ-ሥራ ዕድገታቸው፣ የዘመናዊ ሥልጣኔያቸው፣ የቱን ያህል ይደንቃል፡፡ እቴ ጣይቱ፡፡ መሣሪያ፣ መኪና፣ ፋብሪካ፣ የባህር መልህቅ፣ የመሬት መንኮራኩር ሥራቸው የቱን ያህል ይመጥቃል፡፡ የመንገድ ድልድያቸው፣ ወፍጮአቸው፣ ትምህርታቸው፣ እርሻቸው፣ ባንክ የሚሉት የገንዘብ ብልፅግና ዘዴአቸው፣ አውራ ጎዳኖቻቸው፣ ውሃ በቧንቧና ቃል በሽቦ እሚስብ፣ ነፋስ መላላኪያቸው፣ ብርሃን በክር እሚጠልፍ የሌት ሻማቸው፣ ሰፊ ከተማ ሙሉ ከፋሲል ግንብ የሚበልጡ ህንፃዎቻቸው፣ እቴ ጣይቱ አባ ማስያስና ኢንጂነር ኢልግ አጫውተውሽ የለ?! ብቻ ወደኛ የሚልኩብን ጦራቸውን ብቻ ነው፡፡”
ከላይ የተጠቀሰውን ስንመረምር፤
ዕደ ጥበብ ከዚያ ተነስቶ ዛሬ የት ደረሰ? ፋብሪካ የት ደረሰ? ባህርና ትራንዚት ምን ያህል ተራቀቀ? ትራንስፖርትና መገናኛ ምን ያህል አዘገመ ወይም ፈጥኖ ሄደ? የመንገድ፣ የድልድይ ሥራ ምን ያህል ረቀቀ? እርሻ ምን ያህል ሜካናይዝድ ሆነ? (በደርግ ዘመን ከፊል-ካፒታሊዝሙ ይስፋፋ መስሏቸው ትራክተሮች አስመጥተው “በሶሻሊዝም ተወረሰብኝ!” የሚሉ (ኮማንድ - ኢኮኖሚ ነብሱን ይማረውና) አንድ ባለሀብት፤ “ከጓድ ሊቀመንበር ጋር ወደፊት!” እና “ሶሻሊዝም ይለምልም” የሚል መፈክር ባዩ ቁጥር፤ እጃቸውን በጭብጨባ እያጣፉ “አጀብ!... ትራክተር!” ይሉ ነበር አሉ፡፡
የዛሬ ኢንቬስተር ይሄን አይልም ብለን ተስፋ እናደርጋለን! የባንክ ሥርዓታችንስ የት ደረሰ? ባንክ ውስጥ ካለን ገንዘብና በየሰዉ ትራስ ስር ካለው ገንዘብ የቱ ይበዛል? ሁለቱንም ነብሳቸውን ይማርና የቀድሞው መሪ ለባንኮች፤ “ከእናንተ አየለ (አይ.ኤም.ኤፍ) ይሻላል፡፡ ገንዘቡ በአጁ  አለ፡፡ ያንቀሳቅሰዋል!” ብለው ነበር አሉ፡፡ “ነፋስ መላላኪያችን” የት ደረሰ ማለት ያባት ነው (3G እና 4G እንዲሉ!) ብርሃን በክር የሚጠልፍልን መብራት ኃይልስ? ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡ ግንባታና ህንፃዎቻችንስ? ሰው ሰው ይሸታሉን? ለኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ያላቸው አስተዋፅኦ የሚተነትንልን የቱ ኢኮኖሚስት፣ የቱስ ባለሥልጣን ነው? ማንም ይሁን ምን፣ ገዢም ይሁን ተገዢ፣ ባለሃይማኖትም ሆነ ኢሃይማኖታዊ፣ የተማረም ሆነ ያልተማረ፣ አገር ውስጥ ያለም ሆነ ዲያስፖራ፣ ሀሳባዊም ሆነ ቁስ-አካላዊ፣ የእኛም ይሁን የውጪ ኃይል… ምኒልክ እንዳሉት… “ወደኛ የሚልኩት ጦራቸውን ብቻ” የሚለውን ነዋሪው ዜጋ እንደምን ያየዋል? መባባል አለብን፡፡ ሁሉ ነገር መጨረሻው ፀብ መሆኑን እንደምን እንየው? መቼ ነው ስለ አዎንታዊ ማንነታችን ደርዝ ያለው ግንዛቤ እምንጨብጠው?
እነዚህን ጥያቄዎች እያሰላሰልን ከገዢም ያልሆኑ ከተገዢም ያልሆኑ “የአየር ባየር ነጋዴዎች” እንዲሉ፤ “የአየር ባየር ፖለቲከኞች” ኋላ የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያቤት (ፖለቲካ ሲገባው) የማይምራቸው እንደማለት፤ ፍፃሜያቸው መሬት የሆነ፤
“ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው”  
እንደሚባሉ ያሉ አያሌ ናቸው፡፡ “መንገድ ሲበላሽ ትራፊክ ይበዛል፡፡ አገር ሲበላሽ ጃርት ያፈራል” የሚባለውን የጥንት አባባል ዛሬም ልንደግመው ተገደናል፡፡ ይህን ጉዳይ በትግሪኛ ተረት ብናስቀምጠው፤ “ጫማ ምን ክብር ቢኖረው፤ ሁል ጊዜም እግር ሥር ነው” ይሆናል!!  


Read 6827 times