Tuesday, 29 July 2014 14:53

ጋዜጠኛ አዚዛ መሃመድና ሌሎች እስረኞች ለሐሙስ ተቀጠሩ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ባለፈው ሳምንት አርብ በታላቁ አንዋር መስጊድ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ በፖሊስ የታሰሩ የእምነቱ ተከታዮች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ፍ/ቤት ቀርበው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው።
የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሃመድ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት አባል ወ/ሪት ወይንሸት ሞላና የእስልምና እምነት ተከታዮች ከትናንት በስቲያ ረፋዱ ላይ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የቂርቆስ ክ/ከተማ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በመጠየቁ ፍ/ቤቱ ለመጪው ሐሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አዚዛ መሐመድ ባለፈው አርብ ስራዋን ለማከናወን በታላቁ አንዋር መስጊድ አካባቢ መገኘቷን የጠቆሙት የስራ ባልደረቦቿ፤ እስካሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለችና ለምን እንደታሰረች ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ም/ቤት አባል ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ ተቃውሞው በተነሳበት ዕለት በደረሰባት ድብደባ እጇ የተጎዳ ሲሆን ወደ ፍ/ቤት ስትመጣ እጇ በፋሻ ተጠቅልሎ ታይታለች፡፡
ባለፈው አርብ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ለጁምዓ ስግደት ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ የሄዱ የእምነቱ ተከታዮች፤ “የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈቱ”፣ “መብታችን ይከበር” እና ሌሎች  መፈክሮችን በማሰማት ጠንከር ያለ ተቃውሞ የገለፁ ሲሆን ድብደባ ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የእምነቱ ተከታዮች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ፖሊስ ለተቃውሞው መንስኤ ይሆናሉ ብሎ የጠረጠራቸውን በእስር ያቆየ ሲሆን ሌሎቹ በዚያኑ ዕለት ሌሊትና በነጋታው መፈታታቸው ተዘግቧል፡፡  

Read 3020 times