Print this page
Tuesday, 29 July 2014 14:45

ሆላንዳዊያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ አዲስ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ ሊያቋቁሙ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በ30 ሚ.ብር ካፒታል የሚቋቋመው ኩባንያ በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራ ይጀምራል\

   ሆላንዳውያን ባለሃብቶች አዲስ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለማቋቋም የፕሮጀክት አዋጪነት ጥናት እያከናወኑ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
አዲሱ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ ቀድሞ በሆላንድ መንግስት ድጋፍ ተቋቁሞ የነበረውን “ሆላንድ ካር” ይተካል የተባለ ሲሆን አዲሱ ኩባንያ ከ“ሆላንድ ካር” ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ጥናቱን ለማካሄድ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ሚስተር ኤሪክ ትሪዎሽቻ ቫን ስቺሊቲንጋ ተናግረዋል፡፡
ሚስተር ስቺሊቲንጋ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ አዲሱ ኩባንያ “ኢትዮ-ደች ሞተርስ ካምፓኒ” በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቋቁሞ ከቀድሞ የተሻሉና ጥራት ያላቸው አዳዲስ ሞዴል የቤት አውቶሞቢሎችን እየገጣጠመ ለገበያ ያቀርባል ብለዋል፡፡ ከሚያካሂዱት የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናት ጐን ለጐን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በኩባንያው ዙሪያ ውይይት እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ስቺሊቲንጋ፤ መንግስት በቅርቡ ለመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያዎች የታክስ ማሻሻያ ማድረጉ በሆላንድ መንግስት የሚደገፉ ሆላንዳውያን ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ እንደገፋፋቸው ተናግረዋል።
የቀድሞውን “ሆላንድ ካር” እና አዲሱን “ኢትዮ-ደች ሞተርስ” የሚያመሳስላቸው ሁለቱም በሆላንድ መንግስት በጎ ፍቃደኝነት የተቋቋሙ መሆናቸው ብቻ ነው ያሉት ሚስተር ስቺሊቲንጋ፤ አዲሱ ኩባንያ ሆላንዳውያን በኢትዮጵያ የመኪና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክሮ ለመቀጠል ታስቦ የሚቋቋም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለአዲሱ ኩባንያ ጥሬ እቃ እንዲያቀርብ ከቻይናው ጄኤሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ሚ/ር ስቺሊቲንጋ አክለው ገልጸዋል፡፡  

Read 2846 times