Tuesday, 29 July 2014 14:44

የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ጋዜጠኞችን ሸለመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ከ “ጤና ለሁሉም ዘመቻ” ጋር በመተባበር ባዘጋጀው “የጤና መድህንን ለህዝብ የማስተዋወቅ ዘመቻ” አገር አቀፍ የዘገባ ውድድር ያሸነፉ ጋዜጠኞችን ከትናንት በስቲያ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባከናወነው ስነስርዓት ሸለመ፡፡
የህትመት፣ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የድረ-ገጽ በሚሉ አራት ምድቦች በተከፋፈለውና ጋዜጠኞች የማህበራዊ ጤና መድህንን በተመለከተ ለአንባቢ፣ ለተመልካችና ለአድማጭ ያቀረቧቸውን ዘገባዎች ለውድድር ባቀረቡበት በዚህ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡ አሸናፊዎች ከኤጀንሲው ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ከዶ/ር መንግስቱ በቀለ እጅ የላፕቶፕ፣ የዘመናዊ ሞባይል ቀፎ፣ የፎቶግራፍ ካሜራና የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ዶ/ር መንግስቱ ሽልማቱን ለአሸናፊዎች ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ጋዜጠኞች፣ የድረ-ገጽ ጸሃፊያንና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር  ኤጀንሲው ለያዘው ዕቅድ መሳካት ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው፣ ኤጀንሲው በቀጣይም መሰል ስራዎችን በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የ “ጤና ለሁሉም ዘመቻ” ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት እምሻው በበኩላቸው፣ የጤና መድህን በገንዘብ እጦት ምክንያት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረው በህመም ለሚሰቃዩና ለሞት ለሚዳረጉ ዜጎች ትልቅ መፍትሄ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የጤና መድህን ስርዓትን በተመለከተ በህብረተሰቡ ውስጥ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ብዙ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመው፣ በዕለቱ ለሽልማት የበቁትም ሆኑ ሌሎች ጋዜጠኞች ስርዓቱን ለመዘርጋት በሚደረገው ቀጣይ እንቅስቃሴ ውስጥም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ቢሮና ከብሮድካስት ባለስልጣን የተውጣጡ የውድድሩ ዳኞች ባካሄዱት ግምገማ፤ በህትመት ዘርፍ መላኩ ብርሃኑ ከአዲስ ጉዳይ መጽሄት፣ ምህረት አስቻለው ከሪፖርተር ጋዜጣ፣ ስመኝ ግዛው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ተሸልመዋል፡፡
በድረ-ገጽ ዘርፍ ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፣ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ፣ ጋዜጠኛ ኢዮብ ካሣ ሲያሸንፉ፤ በሬዲዮ ዘርፍ ጋዜጠኛ ገዛኸኝ ተስፋዬ እና ጋዜጠኛ ገናናው ለማ ከደቡብ ክልል መገናኛ ብዙሃን፣ ጋዜጠኛ ገመቺስ ምህረቴ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት፤ በቴሌቪዥን ዘርፍ ደግሞ ጋዜጠኛ ሰለሞን ገዳ በብቸኝነት አሸናፊ ሆኗል፡፡

Read 2544 times