Print this page
Tuesday, 29 July 2014 14:37

አቢሲኒያ የካርድ የሞባይልና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አገልግሎት ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

          በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ ለገንዘብ አስቀማጮች በየወሩ ወለድ በመክፈል፣ የውድ እቃዎችና ሰነዶች ማስቀመጫ ሳጥን አገልግሎት፣ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሂሳቦችን በጥምረት በማንቀሳቀሰና ልዩ የቁጠባ ሂሳብ በመክፈት ፈር ቀዳጅ የሆነው አቢሲኒያ ባንክ፤ ሰሞኑን የተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የካርድና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ የባንክ አገልግሎት መጀመሩን ገልጿል፡፡
ትናንት ረፋድ ላዩ በጊዮን ሆቴል የባንኩ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት፤ በተንቀሳቃሽ ስልክ የግል ሂሳብ እንቅስቃሴ ማወቅ፣ ከአንድ ሂሳብ ወደ ሌላው ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የተለያዩ ክፍያዎችንና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን በባንኩ ማግኘት ይቻላል፡፡

በካርድ የባንክ አገልግሎት ደግሞ ገንዘብ ማውጣት፣ የባንክ እንቅስቃሴዎችን መግለጫ ማግኘት፣ ያለውን ሂሳብ ማወቅ፣ ገንዘብ መላክና መቀበል እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያ መክፈልና መሰል አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻል  ታውቋል፡፡ ካርዱ “ሐበሻ ካርድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ካርዱ የኤቲኤም ማሽኖች ባሉባቸው የንግድ ማዕከሎች በዓላትን ጨምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ባንኩ “በኤቲ ኤም” እና “ፖስ” (ፖይንት ኦቭ ሴል ማሽን) የተገለፁትንና መሰል አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ ሶስት አይነት ኤሌክትሮኒካል ካርዶች ማዘጋጀቱን የገለፁት ኃላፊዎቹ፤ “ሐበሻ ጎልድ ካርድ”፣ “ሐበሻ ዴቢት ካርድ” እና “ሐበሻ ፕሪፔይድ ካርድ” በመባል እንደተሰየሙ ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም ካርዶቹ ገንዘብ ከኤቲኤም ለማውጣት ትንሹ የገንዘብ መጠን 50 ብር ሲሆን ከፍተኛው በሀበሻ ጎልድ ካርድ 15 ሺ፣ በሃበሻ ዴቢት ካርድ 10 ሺ እንዲሁም በሃበሻ ካርድ አራት ሺ ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ቅርንጫፎቹ 102 የደረሱትና 2,800 ሰራተኞች ያሉት አቢሲኒያ ባንክ፤ 50 ያህል የኤቲኤም ማሽኖችን በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች የተከለ ሲሆን፣ ወደ 200 የሚደርሹ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖችን በአዲስ አበባ በሚገኙ የገበያ ማዕከላት እያሰራጨ እንደሚገኝ የባንኩ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡  

Read 2061 times