Saturday, 19 July 2014 12:41

የደራሲ መስፍን ኃ/ማርያም የህይወት ታሪክ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሳሙኤል ጆንሰን “The chief glory of every people a rises from its authors” ይላል። (የአንድ ህዝብ ደማቅ ስምና ታሪክ ከወለዳቸው ፀሐፍትና ደራስያን ጭምር ይፈልቃል እንደማለት ነው) እውነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንድ ደራሲ የሕይወት ታሪክም የአንድ አገርና ሕዝብ ታሪክም ሲሆን አስተውለናል፡፡ የቅዱስ ያሬድ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና የመሳሰሉት ለውስጣችን ታላቅ ኃይል የሚሰጠን የፈጠራ ስራቸው ብቻ ሳይሆን የዚህች ሀገር መሰረት የሆነው የአኗኗር ዘይቤና ፈሊጣቸው ጭምር ነው፡፡
ፑሽኪን ለሩሲያ፣ ብረሽት ለጀርመን፣ ባልዛክ ለፈረንሳይ፣ ሼክስፒር ለእንግሊዝ፣ ሔሚንግዌይ ለአሜሪካ ሕዝብ የታሪኮቻቸው ምንጮች ናቸው፡፡
እነኚህ ደራሲያንና ሌሎችም ሁሉ በፈጠራቸው የሂደት ወቅት አድሏዊ ሆነው አያውቁም፡፡ ሂሳዊ የማይሆኑትና አልፎ አልፎ ሚዛናቸው የሚዛባው መፍረድ ሲጀምሩ ወይም ፍርድ ሲሰጡ ነው፡፡ ታድያ እነዚህን ሁለት የሥነ ጽሑፍ ምሰሶዎች ጠብቀው የተፃፉ ሥራዎችን ሲያስነብበን የኖረን አንድ የጥበብ ሰው አጥተናል፡፡
ሀገራችንና የጥበብ ወዳጆች የሆንን ሁሉ አንድን ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰው አጥተናል፡፡
ሀገራችን ባለቅኔ፣ ተርጓሚና ትሁት መምህር የሆነውን ልጇን አጥታለች፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ታላቁን የወግ አባት አጥተናል፡፡ ወግ ለመቀመር የተፈጥሮ ችሎታውን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አጣምሮ የተካነን ሸጋ ደራሲ አጥተናል፡፡ ባሻው ዘውግ አሳምሮ መፃፍ የሚችል ደመና - ገላጭ ትንሽ ፈጣሪ አጥተናል፡፡
ታላቁ የወግ አባት መስፍን ሀብተማርያም ተለይቶናል፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም የወግን ምንነት ያስተማረን ብቻ ሳይሆን በተለይ የርዕዮትንና የአብዮትን ዜማ ብቻ በውድም ሆነ በግድ እንድንጋተው በተገደድንበት በዚያን ዘመን ሆነ ዛሬ በዕውቅ የወግ ሥራዎቹ የህይወትን ጐምዛዛነትና ጫና ሊያቀልልን የጣረ የጥበብ ሰው ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም ሕይወትን፣ ተፈጥሮን፣ ኑሮንና እነዚህን የሚያጫፍሩትን ዐብይት ክስተቶች ከግለሰብ እስከ ህብረተሰብ ባለው ማንነት ዙሪያ በገሀድ የሚታዩ ድርጊቶችን በመዘርዘር፣ አካባቢያችንና ዘመናችንን በይበልጥም በሰዋዊ ማንነታችን ስንቀበለው በምንችለውና በሚያረካ ኪነታዊ ጉዞ እንድንቃኝ ያደረገ የጥበብ ጀግናችን ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም በሥነ - ወግ፤ ቋንቋችንን የፈተሸ፣ ተራ ቃላት የምንላቸውንና ልንዘነጋቸው የተቃረቡ ዘየዎችን መልሰው ነፍስ እንዲዘሩ ያደረገ የቋንቋ ጠቢብ ነው፡፡
የመስፍን ሀ/ማርያም ወጎች ሁላችንም የምናቃቸው በቋንቋቸው ማራኪና በአቀራረባቸው ሚዛናዊነት፣ በምርጥ ምሳሌያቸው፣ በምጣኔያቸውና ማዝናናት በመቻላቸው ነው፡፡ በተለይ ሥነ - ወግ ዋነኛው ባህሪይው ማዝናናት መሆኑን የምንረዳው ከመስፍን ሀ/ማርያም ጽሑፎች ነው ብንል አልተሳሳትንም፡፡
ማዝናናት ሲባል ፈገግ ማስደረግን፣ ማሣቅን የሚያጠቃልል ቢሆንም ከዚህ በዘለለ የመስፍን ሃ/ማርያም ወጐች በተራነት የማይጠበቅ ት.ግ.ር.ም.ት፣ የማይረሳ አድናቆትና “እንዲህ ነው ለካ” የሚያሰኝ የመንፈስ ደስታ እያላበሱንና እነዚህንም ዘና ባልንበት እያዋዙ፣ ዘና ባልንበት ቁምነገሮችን አሾልከው እየወረወሩ፣ ነፍስና ስጋችንን እያጫወቱ፣ ለብዙ ዘመን ያሸጋገሩን ናቸው፡፡
ተውኔት የቤተ-መቅደስና የቤተ መንግስት ዜና መዋዕል ዘጋቢ ብቻ ከመሆን ታላቋ ፊቷን ወደ ዝቅተኛው የሕብረተሰብ ሕይወት እንድታዞር ፋና ወጊውን ሥራ የፈፀሙ እንዳሉ ሁሉ፣ መስፍን ሀ/ማርያም በተለይ በተለይ በሥነ - ወግ ስራዎቹ የድሐውን ሕዝብ ጓዳ - ጐድጓዳ በርብሮ፣ የድሀ ወገናችንን ወግና - ታሪኩን ደስታና - ሀዘኑን ሕይወትና - ሞቱን በቅርበት እንድንረዳ ያጋዘን የዘመናችን የወግ አባት ነው።
ከሁሉም ከሁሉም የወግ አባቱ መስፍን ሃ/ማርያም፣ ጥበብን - እምነቱ፣ ጥበብን ትሁት ተሰጥኦው…ጥበብን ለይስሙላ ተሳልሟት ያለፈ፣ ገባ - ወጣ እያለ የጐበኛት ሳይሆን በጥበብ ፍቅር ወድቆ (ላይፈታት ተክሊል ደፍቶ) ላይፈታት ቁርባን፣ ቃል ኪዳን ቋጥሮ - ሳይፈታት፣ እድሜ ህይወቱን የሰዋላት ሰው ነው፡፡
መስፍን ሀ/ማርያም በ1937 ዓ.ም ከአባቱ ከአቶ ሀ/ማርያም ሞገስና ከእናቱ ከወ/ሮ ደስታ አየለ ተወልዶ ባለፈው እሁድ በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ጋሽ መስፍን ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ሞጆ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እስካጠናቀቀበት ቀን ድረስ በአንቦ እንዲሁም ከ1958 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ - ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን የማዕረግ ተሸላሚ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ጋሽ መስፍን በ1964 ዓ.ም ባህር ተሻግሮ ካናዳ ቫንኩቦር በሚገኘው በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ልቦለድን፣ ኢ-ልቦለድን፣ ተውኔትንና ሥነ - ግጥምን የጥናቱ ትኩረት በማድረግ “በፈጠራ ሥነ ጽሑፍ” (creative writing) የማስተርስ ዲግሪውን በ1966 ዓ.ም አግኝቷል፡፡
ጋሽ መስፍን ሀ/ማርያም በሥራው ዓለም ለ3 ዓመታት በኤርትራ በተለይ በአስመራና በምፅዋ የአማርኛ ቋንቋን አስተምሯል፡፡
ከ1963-1976 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም የተለያዩ የሥነ - ጽሑፍ ኮርሶችን ያስተማረ ሲሆን ከዚህ ጐን ለጐን በኢትዮጵያ ሬዲዮና በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ጋሽ መስፍን በድርሰት ዓለም “የቡና ቤት ሥዕሎች”፣ “አውደ ዓመት”፣ “የሌሊት ድምጾች”፣ እና ሌሎች የወግ መጽሐፍትን አበርክቶልናል፡፡ “አዜብና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶችን”፣ እንዲሁም የተረት መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ “በቆንጆ ልጅ ፈተና” ሥነ - ግጥሙም እናውቀዋለን፡፡
ጋሽ መስፍን ወደ 550 የሚጠጉ የተለያዩ መጣጥፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በማውጣት ከዘመን ዘመን እያጫወተና እያስተማረ አሸጋግሮናል፡፡ ጋሽ መስፍን ከድርሰቶቹ በተጨማሪ ሃያሲም ነበር፡፡ ጋሽ መስፍን ሳይቤሪያ በዘመተው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ጦር ጋር በመዝመት በአስተርጓሚነት አገልግሏል፡፡
የአብራኩ ክፋይ የሆኑ የሁለት ወንድ ልጆችና የአራት ሴት ልጆች አባትም ነው፡፡
ጋሽ መስፍን በመጨረሻዎቹ የእስትንፋስ ሰዓታቱ ልጁን ሀ/ማርያም መስፍንንና ቃልኪዳን መስፍንን አሳድጉልኝ፣ ለወግ አብቁልኝ እያለ ሲወተውትና ሲማፀን ነው ሕይወቱ ያለፈችው፡፡
ጋሽ መስፍን The Merchant of Fear የምትሰኝ አጭር ልቦለዱንና ሌሎች ያልታተሙ ሥራዎቹ ለንባብ ይበቁለት ዘንድ ሲማፀን ቆይቶ ለአንዴና ለሁሌም ተለይቶናል፡፡
ይህ ሁላችንም የምንወደው፣ ይህ ትሁት፣ ይህ ቅን፣ ይህ የኑሮ ጫና ሳይበግረው ዘመኑን ሙሉ ያገለገለንን ታላቅ የጥበብ ሰው፣ የመጨረሻ ሰዓት ኑዛዜውን ያገለገለው የሀገራችን ህዝብና የጥበብ ወዳጆች ሁሉ እውን እንደሚያደርጉት የፀና እምነቴ ነው፡፡
በመጨረሻም በዚህ በታላቁ የጥበብ ሰውና የወግ አባት በሆነው በደራሲ መስፍን ሃ/ማርያም የቀብር ስነስርዓት ላይ ተገኝታችሁ ቤተሰቦቹን ያጽናናችሁትን ሁሉ በልጆቹ፣ በዘመዶቹ፣ በኢ.ደ.ማ አባላት፣ በራሴና በጥበብ ወዳጆች ሁሉ ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
ታላቁ አምላክ ይህን ፍዳውን ሁሉ በምድር ዓለም የጨረሰን የጥበብ አባት መስፍን ሃ/ማርያምን ነፍሱን በገነት ያሳርፋት ዘንድ እንለምናለን፡፡
አመሰግናለሁ

Read 4227 times