Saturday, 19 July 2014 12:01

“የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን” የሰሞኑ ግምገማ ከአምናው የተሻለ መሆን አለበት

Written by  ዘላለም በቀለ
Rate this item
(1 Vote)

         የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ አዲስ የተዋቀረው የባለስልጣኑ የማናጅመንት ቡድን ባለፈው ዓመት “ግምገማዊ ስልጠና” አካሂዶ ነበር፡፡ ግምገማው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችን፣ ከፍተኛ ኦፊሰሮችና ሌሎች ሰራተኞችንም ይጨምራል፡፡  የግምገማው ቦታ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ መኝታ እንዲሁም ቁርስና እራትን የምንጠቀመው  በዩኒቨርሰቲው ውስጥ ሲሆን የመፀዳጃ ቤት፣ የሻወርና የምግብ ጥራት ችግር ነበረው፡፡ ይሄን ችግር ለበላይ ሃላፊዎች ስናቀርብ የተሰጠን ምላሽ አስገራሚ ነበር፡፡ “የምናካሂደው አብዮት ስለሆነ እንዲህ ያለ ችግር አንሰማም” ነበር የተባለው፡፡ እኛም  በዝምታ  ግምገማውን ቀጠልንበት፡፡
ግምገማው በየዘርፉ የተካሄደ ሲሆን ምንም እንኳን ሂደቱ አሰልቺ ቢሆንም ጠቃሚ ጉዳዮች የተነሱበት፣ ትችቶች የተሰነዘሩበት፣ የመተራረም ተመክሮ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡
ከተነሱት አንኳር ሃሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮቻቸውና መፍትሔዎቻቸው
ሰዎች ያለሙያቸው ይመደባሉ፡፡ ለምን?
ወገንተኝነት በተቋሙ ይስተዋላል፡፡ ለምን?
አስተዳደሩ ሁሉንም ሰራተኛ  እንደሌባ ያየዋል
የማይመለከታቸው ሰዎች ውጭ ሀገር ለስልጠና ይሄዳሉ፡፡ ለምን?
የሰውና የሃብት አስተዳደር እንዲሁም የኦፕሬሽን ዘርፍ አሰራሩን መፈተሸ አለበት
የፓርቲ አባልና አባል ያልሆነ እኩል መብት ይኑራቸው
ልምድ ያለው ሰራተኛ የሚለቀው አመራሩ ስላልተመቸው ነው፤ ደሞዝ ቀንሶ የሚለቅበት እንቆቅልሽ ይታይ
ለትምህርት ደረጃ ዋጋ ይሰጠው
የአስተዳደር ብቃት የሌላቸው ሰዎች በኃላፊነት ለምን ይመደባሉ? … ወዘተ
አስተዳደሩ ለእነዚህ አስተያየቶች የሰጠው ምላሽ ሁሉንም በሂደት አይተነው እንፈተዋለን የሚል ነበር፡፡ ጉድና ጅራት በስተኋላ ነው እንዲሉ በመጨረሻዎቹ ቀናት ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ፡፡ በአባ ገዳ አዳራሽ ውስጥ ነበርን፡፡ በዋና ዳይሬክተሩ መሪነት “የምታውቁትን አጋልጡ” የሚል ትእዛዝ ከመድረኩ ተሰነዘረ፡፡ ከመቅፅበት ለትወና የተዘጋጁ የሚመስሉ ሰዎች ከግራም ከቀኝም እጅ ማውጣት ጀመሩ፡፡ “እከሌ እንዲህ ነው፣እከሊት እንዲህ ናት” እያሉ የማጋለጥ ሂደቱን ተያያዙት፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሁለቱን ልጥቀስላችሁ፡-
“እከሊት ከደሞዟ በላይ ነው ወጪዋ፡፡ የምትለበሰው ልብስ በጣም ውድ ነው፡፡” ከወደ ግራ በኩል የተሰነዘረ አስተያየት ነበር፡፡
ከወደ ቀኝ በኩል መልስ ተሰጠ “አረብ ሀገር እህቶች ስላሉኝ ነው”
 “አናቅሽም እንዴ --- አሁን ተጣላን እንጂ ባንድ ወቅት ጓደኛዬ በነበርሽ ሰዓት ደሞዛችን አልበቃ ብሎን ሰልቫጅ ተራ ሄደን አልነበር ልብስ የምንገዛው!”
አሳፋሪና ቦታውን የማይመጥን ምልልስ ቀጠለ…
ከወደቀኝ በኩል ሁለተኛ እድል የተሰጠው ሰው “እከሌና እከሊትን ጨምሮ ገንዘብ ከየት እንዳመጡ አላውቅም የሆነ አክሲዮን አቋቁመዋል፡፡” ሲል ተናገረ፡፡
ከመድረኩ ትእዛዝ ተሰማ “አክሲዮን አቋቁማችኋል ከተባላችሁት መካከል አንዳችሁ መልስ ሰጡ”
 “አዎ በእርግጥ አክሲዮን ለማቋቋም ጀምረን ነበር፡፡ ነገር ግን ካፒታላችን ዝቅተኛ ስለሆነ ብዙም አልገፋንበትም፤ ከአመት በፊት ፈርሷል። ባይፈርስም ግን አቅም ካለን አክሲዮንም ሆነ የአክሲዮን ሼር ለመግዛት የሚከለክለን ህግ ያለ አይመስለኝም፡፡”
ግምገማ ሳይሆን ሃሜት ነው የሚመስለው፡፡ በእጅጉ ማስረጃ ላይ ያልተደገፈ ውንጀላ የበዛበትም ነበር፡፡  እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አንድ ሰው በኪራይ ሰብሳቢነት ከተጠረጠረ የሚመለከተው ክፍል በምርመራ ሂደት አጣርቶ ወይ ነፃ ይሆናል ወይም ወደ ፍትሕ አካል ይተላለፋል፡፡ ከላይ የጠቀስኩት አካሄድ ግን በጣም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡
ውጤቱም ማናጅመንቱ እንደጠበቀው አልነበረም፡፡ አብዛኛው ነባርና ልምድ ያለው ሰራተኛ ሁኔታው ስላላማረው መሥሪያ ቤቱን እየለቀቀ ወጣ፡፡ አዳዲስ የተቀጠሩ ሰራተኞችም ለስልጠና የወጣውን ወጪ በመክፈል ሥራቸውን ለቀቁ፡፡ ከዚያም የፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ችግር ከደንበኞች ዘንድ መሰማት ጀመረ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቴሌቪዥን መግለጫ ተሰጠ፡፡ ጋዜጠኛ ጠየቀ፤ “ሰራተኞች በብዛት እየለቀቁ ነው፤ ለምን ይመስልዎታል?” ባለስልጣኑ መለሱ “በእርግጥ እየለቀቁ ነው፤ እኛ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄድን ነው፡፡ ይኸው አልመች ብሏቸው ነው የሚለቁት፡፡”
ጋዜጠኛው፤ “ምኑ ነው አልመች ያላቸው?”
ባለስልጣን “ሌብነት ላይ የምናካሂደው ዘመቻ!”፤ (ያለማስረጃ ሁሉም በሌብነት ተፈረጀ)
የግምገማው ሂደት የተበላሸው በወቅቱ ሁሉም የበላይ አመራር አካላት አዲስ በመሆናቸውና  የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱን ሰራተኛ ሁኔታ ባለመረዳታቸው ይመስለኛል፡፡ አብዛኛውን ሰራተኛ እንደሌባ መፈረጃቸው ነገሩን አበላሽቶታል፡፡
አሁን ግን ብዙ ነገር የተረዱ ይመስለኛልና ባለፈው ሳምንት በአዋሳ የተጀመረው ግምገማ ጥንቃቄ የተሞላበትና ሰራተኛውን የሚያስበረግግ ሳይሆን የሚያርም፣ ሞራል የሚሰጥና ለመስሪያ ቤቱ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርግ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስኬታማ የግምገማ ጊዜ እመኛለሁ!

Read 1795 times