Saturday, 19 July 2014 11:49

ኢህአዴግ አንዴ ገዢ ፓርቲ፤ አንዴ ተቃዋሚ ሆኖ መተወን ከብዶታል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)


በመጪው ምርጫ የኢህአዴግ ደጋፊ የሆነ ”ተቃዋሚ ፓርቲ” ያስፈልገናል
ዶ/ር አሸብር ኢህአዴግን በድጋሚ ማሸነፍ አይፈልጉም!
ኢቴቪን የተመለከተ ዶክመንተሪ የሚሰራ አገር ወዳድ እንዴት ጠፋ?


ባለፈው ቅዳሜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ የቀረበው የዶ/ር አሸብር ቃለ ምልልስ በእጅጉ አዝናንቶኛል፡፡ (ቃለ ምልልስ ነው ወይስ ማመልከቻ?) ባይገርማችሁ… በቃለ ምልልሱ ላይ የተናገሩት በአብዛኛው ለህዝቡ ሳይሆን  ለኢህአዴግ ፅ/ቤት ነው የሚመስለው፡፡ (እኛ ገዢ ፓርቲ አይደለንማ!)  እኚህ ሰው የዛሬ 4 ዓመት ለምርጫ ሲወዳደሩም ዘና እንዳደረጉን ትዝ ይለኛል - “የኢህአዴግ ደጋፊ፤ የግል ተወዳዳሪ ነኝ” በማለት፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊ ነኝ ቢሉም ኢህአዴግ ያቀረበውን እጩ ተፎካካሪ አሸንፈው ፓርላማ የገቡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ዶ/ር አሸብር በ2002 ምርጫ ከኢህአዴግ ጋር ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ግን  የወደዱት አይመስለኝም። እኔ ከቃለ-ምልልሳቸው የተረዳሁት መፀፀታቸውን ነው፡፡ በምርጫው የተወዳደሩት አንድ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ግለሰብ በፈፀሙባቸው በደል እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ሩ፤ ፈፅሞ ኢህአዴግን ተቃውመው አለመወዳደራቸውን አስረግጠው ተናገረዋል፡፡ (ኢህአዴግ እጩውን ቀይሮ ቢሆን ኖሮ አልወዳደርም ነበር ብለዋል!) እኔ የምለው… ሰው ለምርጫ የሚወዳደረው ህዝብ ለማገልገል ነው ወይስ በደል ለመቀበል?  (ለሁለቱም ይቻላል እንዳትሉኝ!)
በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ገና ባይወስኑም ድንገት በምርጫው ቢሳተፉ እንኳ ኢህአዴግን በድጋሚ ባይወዳደሩት ደስ እንደሚላቸው ተናግረዋል (በድጋሚ እንዳያሸንፉት ፈርተው እኮ ነው!) ከንግግራቸው ትንሽ ግራ ያጋባኝ ግን  ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ መዝኖ ፈተናውን አልፈሃል ወይም ወድቀሃል ይበለኝ-- ያሉት ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ እኮ የራሱን አባል እንጂ የግል ተወዳዳሪ ገምግሞ አያውቅም፡፡ (በክፍያ የግምገማ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ይሆን እንዴ?)
የዶክተር አሸብር ቃለምልልስ የሚያዝናና ብቻ ሳይሆን የሚያስገርምም ነው፡፡ በፓርላማው የተቃዋሚዎች አለመኖር ብዙም የሚያሳስባቸው አይመስሉም - ከቃለ ምልልሱ እንደተረዳሁት፡፡ እንደሳቸው ዓይነት “የኢህአዴግ ደጋፊ የግል ተወዳዳሪ” ካሉ በቂ ነው ብለው የደመደሙ ይመስላል፡፡ ለዚህ ነው ፓርላማው ውስጥ 100 ፐርሰንት አንድ ፓርቲ ቢሆን ነውር የለውም ያሉት፡፡ (እንኳንም የግል ተወዳዳሪ ሆኑልን!) ገዢው ፓርቲ ቢሆኑ እኮ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያከትምለት ነበር፡፡ በግል ክሊኒክ ባለቤትነት የሚታወቁት ዶ/ር አሸብር  ነጋዴዎች ከባንክ ብድር ማግኘት አልቻልንም ማለታቸውን በተመለከተ የሰጡት አስተያየትም አግራሞት የሚፈጥር ነው፡፡ እንደውም የሚበደር ነው የጠፋው ብለዋል፡፡ ምናልባት በቅርቡ ስብሰባ ተካፍለው ከመጡበት አገር ጋር ተምታቶባቸው ይሆን እንዴ? (“ጋዜጠኛዋ ስለኢትዮጵያ እኮ ነው የምጠይቅዎት!” ብላ በድጋሚ ጥያቄዋን ማንሳት ነበረባት!)
በተረፈ ግን እሳቸው “የኢህአዴግ ደጋፊ የግል ተወዳዳሪ” እንደሚሉት ሁሉ፣ ለ2007 ምርጫ  የኢህአዴግ ደጋፊ ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም ያስፈልገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ - ትንሽ ዘና እንድንል ያደርገናል፡፡ እንኳን በፓርቲ ደረጃ የግል ተወዳዳሪ እንኳን እንዴት እንደሚያዝናና አይታችሁት የለ! ምርጫ ቦርድ ለእንዲህ ያለ ፓርቲ ፈቃድ ይሰጥ ይሆን? (አጣሩልኛ!)     
አሁን ደግሞ ወደ ሌላ አጀንዳ እንለፍ፡፡ መንግስት “ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” እያለ በተደጋጋሚ ሲናገር እየሰማነው ነው፡፡ በተግባር ግን ገና አላስመሰከረም ይላሉ - አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ እውነታቸውን ይሆን? (በመረጃ ላይ ተደግፎ መወቃቀስ የሥልጣኔ ምልክት ነው!)
ኢህአዴግ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ህልም እንዳለው በይፋ ሲናገር “ዓይንህን ላፈር” የሚሉት ወገኖች ሳይቀሩ “ዋው!” ብለው ነበር - በአድናቆት!! (ማድነቅ ሲያንሳቸው ነው!) ገዢ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጎልበት እንዲህ ያለ ቁርጠኝነት ሲያሳይ እንኳንስ በጦቢያ በአፍሪካም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡
በ2002 አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ በ98 ነጥብ ምናምን (ከመቶ ማለት ነው!) ድምፅ ምርጫውን ማሸነፉን ተከትሎ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በመስቀል አደባባይ ለታደመው የኢህአዴግ ደጋፊና ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር “ያሸነፈው ይሄኛው ወይም ያኛው ፓርቲ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ማለታቸው ይታወሳል (የማንዴላን ንግግር እኮ ነው የሚመስለው!) ይሄን ጊዜ ታዲያ ብዙዎች “ኢህአዴግ ልብ ገዛ” ብለው ነበር፡፡ (አይጠቀምበትም እንጂ ራሱ አለው እኮ!)
ጠ/ሚኒስትሩ፤በዚያው ሰሞን ለኢቴቪ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች በፓርላማ ውክልና ባያገኙም መንግስታቸው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበትን መንገድ እንደሚያመቻች ተናግረው ነበር። ይሄኔ ነው ኢህአዴግ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ “ዋው!” የሚል አድናቆት የተቸረው፡፡ (አሁን ግን  ሁለቱም  አድናቆቶች በእጁ ላይ የሉም!)
ኢህአዴግ ክፉ ሆኖ ሳይሆን እንደዕድል ሆኖበት ሁለቱንም የተናገራቸውን ነገሮች ሳያሳካ ቀርቷል፡፡ ሲመኝ የኖረውን  ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አልፈጠረም። ፓርላማ ያልገቡ ተቃዋሚዎች በአገር ጉዳይ ላይ የመምከር ዕድል ያገኛሉ ያለውም አልተሳካለትም፡፡ ሁለት አልሞ ሁለቱንም ስቷል! (አልሞ መተኮስን ረስቷል ልበል?)  በነገራችሁ  ላይ በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመፈጠሩ ከማንም በላይ እኔን ነው የጎዳኝ ሲል ተናዝዟል - ኢህአዴግ፡፡ የተቃዋሚዎችን ሚና ራሱ እንዲወጣ መገደዱን በመግለፅ፡፡  (አንዴ ገዢ ፓርቲ፣ አንዴ ተቃዋሚ እየሆኑ መተወን  ፈታኝ ነው!) ትራጄዲው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የተመኘውን ጠንካራ ተቃዋሚ የመፍጠር ህልሙን አለማሳካቱ ሳያንሰው በፓርላማ የተፈረጁ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ማፍራቱ ነው፡፡ (ወደድንም ጠላንም የእኛው እዳዎች ናቸው!)
እኔ የምለው … በወዲያኛው ሳምንት ኢቴቪ በግል ፕሬሱ አጀማመርና ሂደት ላይ ያቀረበውን ዶክመንተሪ እንዴት አያችሁት? ለኔ መቼም ከሌላው ጊዜ በእጅጉ የተሻለ ነበር፡፡ የአቅሙን ያህል ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሯል። ሙሉ በሙሉ ሚዛናዊ ነው እንዳንለው ግን ቢያንስ  ስም ሳይጠቀስ በምስል እየታዩ ሲወነጀሉ የነበሩትን የፕሬስ ውጤቶች ሃሳብ አላካተተም፡፡ በነገራችሁ ላይ አንድ የኢህአዴግ ኃላፊ የግል ፕሬስ ዓላማ ምን መሆን እንዳለበት ሲያስረዱ፤ “የግል ፕሬስ ፈቃድ ማውጣት ያለበት ኢህአዴግን ለመጣል  ሳይሆን የዛሬ 50 እና 100 ዓመት እነ “ዎል ስትሪት” የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልሞ መሆን አለበት“ ብለዋል - በዶክመንተሪው ላይ፡፡ (እነ “ዎል ስትሪት” የኒዮሊበራል አቀንቃኞች አይደሉም እንዴ?)
በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ በግሉ ፕሬስ፣ በቀለም አብዮት፣ በተቃዋሚዎች፣ በአሸባሪዎችና በአክራሪዎች ዙሪያ ዶክመንተሪዎች እየሰራ ለማቅረብ እንዴት መከራውን እንደበላ እማኞቹ እኛ ነን፡፡ (እንደ ኢቴቪ  የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሚናውን የተወጣ የለም!) ግን ምን ያደርጋል? የሰራን የማድነቅና የማበረታታት ባህል የለንም፡፡ እናም አንዴም ሳይሸለምና ሳይደነቅ ወደ ኮርፖሬሽንነት ሊለወጥ ነው፡፡ እሺ ሽልማቱም ይቅር .. እንዴት አንድ እንኳን ዶክመንተሪ የሚሰራለት ያጣል? የአገር ዶክመንተሪ እየሰራ ህፀፅ የሚነቅስ ተቋም፣የእሱን ዶክመንተሪ ሰርቶ ህፀፁን የሚነቅስለት እንዴት ያጣል ?(“የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” ማለት ይሄኔ ነው!)
ኢቴቪ በግል ፕሬሱ ዙሪያ ያሰናዳውን ዶክመንተሪ ባቀረበልን ማግስት (መቼም ግጥምጥሞሽ መሆን አለበት!) ከሰባት አስርት ዓመታት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት “የወረቀት ዋጋ እጅግ ንሯል” በማለት፣ የህትመት ዋጋ ላይ ከ25-35 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ ይሄም የግል ፕሬሱን ህልውና ስጋት ላይ እንደጣለ አሳታሚዎች በምሬት ተናግረዋል፡፡ ልብ በሉ! የዋጋ ጭማሪው የ5 ወይም የ10 በመቶ አይደለም፡፡ እርግጠኛ ነኝ ማተሚያ ቤቱ የግል ቢሆን ኖሮ ሌሎች አማራጮችን ይወስዳል እንጂ ይሄን ሁሉ ጭማሪ በአንድ ጊዜ ደንበኞቹ ላይ አይጭንም፡፡ ብርሃንና ሰላም ግን ይሄ ሁሉ ደንታ አልሰጠውም (“ልማታዊ የመንግስት ተቋም” ነዋ!)
በነገራችሁ ላይ እንኳን ዋጋ ሲጨምር ቀርቶ የእሁድ ጋዜጣን ማክሰኞ፣ የቅዳሜውን እሁድ ሲያወጣም እኮ ደንታ ሰጥቶት አያውቅም፡፡ (ለምን ብሎ ይጨነቃል?) ብርሃንና ሰላም እኮ እንደእነ ቴሌና መብራት ኃይል  ነው፡፡(ደንበኞቹ አማራጭ እንደሌላቸው አሳምሮ ያውቃል!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል --- ጨክነን ከቻይና ማተሚያ ቤቶች ጋር ብንቀራረብ እኮ ከብርሃንና ሰላም የተሻለ ፈጣን አገልግሎት እናገኛለን፡፡ ተርብ የሆኑ የቻይና የህትመት ባለሙያዎች አስር የማይሞሉ  የኢትዮጵያ ሳምንታዊ ጋዜጦችን  በእለቱ ማውጣት አያቅታቸውም! (ቢዝነስና ፖለቲካን አይቀላቅሉማ!)   
መነሻዬ ላይ ኢህአዴግ “ለአገሪቱ ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” እያለ መወትወቱን ያነሳሁት ለዋዛ ፈዛዛ አይደለም፡፡ ለቁምነገር ነው፡፡ አያችሁ… የዲሞክራሲ ነገር ከልቡ የሚያሳስበው ከሆነ የህትመት ዋጋ ጭማሪውን እንደሌላው ጊዜ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሊያልፈው አይችልም፡፡ የግል ፕሬሱ ከጨዋታ ውጭ ሆነ ማለት የዲሞክራሲ ሥርአቱን እንዴት ከስሩ እንደሚነቀንቀው መገመት አያቅተውም፡፡ የቱንም ያህል የግሉ ፕሬስ ባይመቸውም ለዲሞክራሲው መጎልበት ሲል አንድ ነገር ማድረጉ አይቀርም፡፡ (ማመልከቻ መሰለብኝ እንዴ? ነው እኮ!)
ይኸውላችሁ--- ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የህትመት ወረቀት ላይ የተጣለውን ቀረጥ በማንሳት ብቻ መንግስት ለዲሞክራሲው መጎልበት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት ይችላል፡፡ (“ለዲሞክራሲ ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ”--እንዲሉ) ያለዚያ እኮ የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የቆየበትን ዕድሜ ያህል ሳያስቆጥር እንኳ ሊያከትም ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የዶ/ር አሸብር አስተያየት ምን እንደሆነ ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ (ዘና ለማለት እኮ ነው!) 

Read 5534 times