Saturday, 19 July 2014 11:37

ከአቅም በላይ በሆነ የሕትመት ችግር ፕሬሱም፣ አንባቢውም፣ ደንበኛም እየተጐዳ ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የ”ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” መግለጫ


መሰባሰብ ከጀመረ ሁለት ዓመት የሆነውና ሕጋዊ ዕውቅና በሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ያገኘው “ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በተደጋጋሚ ስብሰባዎቹ ከሕዝቡና ከደንበኞቹ ለአባል ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚቀርቡትን ሐሳቦች አስተያየቶችና ቅሬታዎች ሲመረምርና ሲወያይበት ሰንብቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውም ለአንባቢዎች መልስ ለመስጠት ይህን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ከሚጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማ አይስማማ ሌላ ነገር ሆኖ በጋራ አንባቢው ኅብረተሰብ የሚያቀርበው ቅሬታ አለ፡፡ ቅሬታውም “ምነው በወቅቱ አትወጡም?”፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት ወሬ ትሰጡናላችሁ፣ ምነው ጠቆረ፣ ምነው ባለ ቀለም የነበረው ጠፋ፣ ምነው ተዳከማችሁ፣ ምነው ጊዜ ያለፈበት የሥራና የጨረታ ማስታወቂያ ታስነብቡናላችሁ ወዘተ. ይላል፡፡
ከጋዜጣና ከመጽሔቶች ጋር በማስታወቂያና በስፖንሰርሺፕ የሚገናኝ አካልም ማስታወቂያችን በወቅቱ አልወጣም፣ ጊዜ አልፎበታል፣ ጭራሽ ባለቀለም የነበረው ጥቁርና ነጭ ሆኗል፣ ጭራሽ ቀለሙ ጠቁሮና ደብዝዞ አይታይም አይነበብም ለመክፈል እንቸገራለን ይላል፡፡
“ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ” በማኅበሩ ተደጋጋሚ ስብሰባ እነዚህን በዝርዝርና በጥልቀት ተወያይቶ የሕዝብ ቅሬታና የደንቦች አቤቱታ እውነት እንደሆነ ተቀብሏል፤ አምኗል፡፡ ችግሩ ምን ላይ እንደሆነም ለሕዝብ ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡
በተከታታይና በተለያዩ መንገዶች በፕሬስ ሕትመቶች ላይ እየታየ ያለው ችግር በዋነኛነት ከማተሚያ ቤት ጋር የተየያዘ ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እናሳትማለን። አንዳንዶቻችን በሌሎች ማተሚያ ቤቶች እናሳትማለን።
በተደጋጋሚ የሚታየው የማተሚያ ቤት ችግር አንዱ የሕትመት ማሽን ተበላሸ እየተባለ ጋዜጦችና መጽሔቶች በወቅቱ እንዳይወጡ መደረጉ ነው፡፡ የፈተና ወረቀት እየታተመ ስለሆነ ጋዜጣና መጽሔት በወቅቱ አይታተምም የሚልም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የፕሬስ ውጤቶች ቅዳሜና እሑድ መውጣት ያለባቸው ረቡዕና ሐሙስ ሲወጡ ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ቢዝነሱን በእጅጉ እየጐዳ ነው፡፡
ሌላው ችግር ገፅ ቀንሱ ወረቀት የለም ቀለም የለም የሚል ነው፡፡ ይህም ጋዜጦችና መጽሔቶች አንባቢዎች ከሚፈልጉትና ደንበኞች ከተዋዋሉት ጋር የሚሄድ ቁጥር እንዳያገኝ እያደረገና ሰውን እየጐዳ ነው፡፡
ቀለም የለም፣ ፕሌት የለም እየተባለ መልካችሁንና ይዘታችሁን ቀይሩ የሚል ጫናም ከማተሚያ ቤቶች እየመጣ ነው፡፡ ይህም በእጅጉ ቢዝነሱን እየጐዳ ነው፡፡
በተለይ በተለይ ደግሞ ደንበኞችን አክብሮና ተወያይቶ አወያይቶ የገበያ ዋጋን ከመወሰን ይልቅ በድንገት ዋጋ ተጨምሯል እያሉ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሣራና ጫና መፍጠር በእጅጉ አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ ሆኗል፡፡ የጥራት ጉድለትና ጋዜጦችና፣ መጽሔት ፎቶዎቻቸውና ጽሑፎቻቸው መነበብ በማይችሉበት ሁኔታ ተጨማልቆ መውጣትም ሌላው አስፈሪና አሳፋሪ፣ ቢዝነስን በእጅጉ እየጐዳ ያለ ተግባር ሆኗል፡፡
የተከበረው አንባቢ ኅብረተሰብና የቢዝነስ አጋራችን የሆነው አካል ችግራችን ከላይ እንደተጠቀሰው ከአቅማችን በላይ መሆኑን እንዲገነዘብልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ የምንጠቀምበት ማተሚያ ቤት የራሱ የፕሬሱ አይደለምና ‹‹ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ›› የማተሚያ ቤትን ችግር የራሱ ማተሚያ ቤት በማቋቋም ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህም በአጭር ጊዜ እውን ለማድረግ ቀላል ስለማይሆን ይህ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ከመንግሥት ጋር ሆኖ ብርሃንና ሰላምና ሌሎች ማተሚያ ቤቶች የሚፈጥሩትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡
በቅርብም ችግሩን በጋራ ዓይተንና ተወያይተን በጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር በሚመለከተው አካል በኩል የቀጠሮ ቀን ጥያቄ አቅርበናል፡፡
እኛም የማኅበሩ አባላት የፕሬሶችን ችግር ለመፍታት ራሳችን ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ለማድረግና ድክመቶቻችንንም፣ ችግሮቻችንንም አስወግደን በመጠናከር የሚገባንን ሁሉ ለማድረግ ተነስተናል፡፡ ከመንግሥት ጋር ሆነን ችግሩን ለመፍታትም መንግሥትን ጠይቀናል፡፡
ይህ እንዲህ ሆኖ ሕዝብም ዋነኛውና ወሳኙ አካል ስለሆነና የቆምንለት ዓላማ ተገቢ መረጃ ለሕዝብ በወቅቱና በጥራት መስጠትና ሕዝብን ማገልገል ስለሆነ ሕዝብም ችግራችንን ተረድቶ ይበልጥ የምናገለግልበትን አቅም እንድንገነባ በትዕግስት ከጐናችን እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማኅበር በኢትዮጵያ
            ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም.          

Read 3394 times