Saturday, 19 July 2014 11:34

በጣም አንጣላ፤ ከታረቅን እንዳይቆጨን

Written by 
Rate this item
(16 votes)

(ኣፀቢቕና ኣይንበኣስ፣ እንተ ተዓረቕና ከይንጠዓስ)

አንድ የአሜሪካ ጋዜጣ ላይ የሚከተለው ሰፍሯል፡፡ የሚከተለው ኩባንያ (መሥሪያ ቤት) አባል መሆን ይፈልጋሉ?” በሚል ርዕስ፡፡ ነገሩ ዕውነት ነው፡፡ ግን ላታምኑ ትችላላችሁ፡፡
ይህ ኩባንያ ከ500 ጥቂት ከፍ ያሉ ሠራተኞች አሉት፡፡
ኩባንያው የሚከተለው ስታቲስቲክስ አለው፡-
ካሉት አባላት 29ኙ በሚስቶቻቸው ላይ ግፍ በመፈፀም ተከሰዋል፡፡
7ቱ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ታስረው ነበር፡፡
19ኙ የተሳሳተ ቼክ በፈረም ተከሰዋል፡፡
117ቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁለት የንግድ ተቋማትን ኪሣራ ላይ ጥለዋል፡፡
3ቱ አስገድደው ደፍረዋል፡፡
71ዱ ከዚህ ቀደም ባደረሱት ጥፋት ክሬዲት ካርድ ማግኘት አይፈቀድላቸውም፡፡
14ቱ ከአንደዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
8ቱ ከሱቅ ዕቃ ሲመነትፉ ተይዘው ታስረዋል፡፡
21ዱ በአሁኑ ጊዜ ክሳቸውን ለመከላከል ፍ/ቤት ይመላለሳሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 84ቱ ጠጥተውና ሰክረው በመንዳት ታስረዋል፡፡
እነዚህን ሁሉ ያቀፈው ይህ ድርጅት፤ የትኛው ይመስላችኋል?
ምናልባት የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ ተሳስታችኋል (ሊሆን አይችልም ማለት ግን አይደለም)
አላወቃችሁም? ተስፋ ቆረጣችሁ?
መልሱ ምን መሰላችሁ?
535 አባላት ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ነው፡፡
በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጐችን የሚያወጡትና ሁላችንንም ቀጥ - ለጥ ብላችሁ ተገዙ የሚሉን እነዚሁ የግብዝ ጥርቅሞች ናቸው፡፡
*   *   *
አመራሮች “የራስህን ዐይን ጉድፍ ሳታይ የሌላውን ጉድፍ ለማውጣት አትሞክር” የሚለውን፣ ራስን የማፅዳት መርህ የማወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሴቶች ላይ ያለን የበላይነት አባዜ ሳይወገድ፣ እጃችን ከማጭበርበር ወንጀል ሳይፀዳ፣ በየንግድ ተቋማቱ ውስጥ የተነካካንበትን ሁኔታ ሳናጠራ፤ ከተለያዩ ሱሶች የተገላገልን ሳንሆንና ከአልባሌ ወንጀሎች ክስ የራቀ የኋላ ታሪክ ሳይኖረን፤ ሌሎችን መምራት አዳጋች መሆኑ መቼም፤ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ በትምህርት ራስን ማብቃት ዋና ነገር ቢሆንም፤ በሥነ-ምግባራዊና ሥነ-ሰብዓዊ ክሂል ካልተደገፈ ጉዟችን ጎዶሎ ይሆንብናል፡፡
ዛሬ ሀገራችን የምትፈልጋቸው አያሌ ባለሙያዎች፣ በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉቱ፤ ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ልዩ ልዩ ንጥረ-ባህሪ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ክሂል ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉትን ያገናዘበ ቢሆን ይበጃል፡፡
ልዩነትን መወያየት የሚፈልግ ሰው ያስፈልጋል፡፡ (a bone to pick እንዲሉ)
መቼም ቢሆን ድብቅ ፍላጐት ያለው ሰው ጣጣ ነው፡፡ (an axe to grind እንዲሉ) ከዚያ ይሰውረን፣ የሚል ግልጽ ሰው ያሻናል፡፡
አንድ የተበላሸ ፍሬ ሙሉውን በርሜል ያበላሸዋል፡፡ አንድ ሞሳኝ ሰውም እንደዚያው ሁሉንም ሰው ያበላሻል፡፡
የተሳሳተው ዛፍ ላይ መጮህ (Barking up the wrong tree እንዲሉ) የተሳሳተ ጉዳይ ላይ ከተሳሳተ ሰው ጋር ማውራት ጅልነት መሆኑን የተገነዘበ የፖለቲካ መሪ፤ ያሻናል፡፡
ፈረንጆቹ ወይ ህፃን ወይ አዋቂ አለመሆን አለመታደል ነው ይሉናል (Between hay and grass እንዲሉ) ይህንን ልብ ያለ የፖለቲካ ሰው ይስጠን፡፡
ታገስ (Hold your horses ነው ነገሩ) ትልቅ የህይወት መርህ ነው፡፡ ዕለት ሠርክ ትዕግስት የሚጠይቁ አያሌ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እነዚያን ለመወጣት የሚችል ሰው ይባርክልን፡፡
ሁሉን ነገር (kit and caboodle እንዲሉ) አጠቃሎ የማየት አስተውሎት ያለው የበሰለ ተቃዋሚ ይሰጠን ዘንድ እንፀልይ፡፡
“ከፈረሱ አፍ ስማ” የሚለው መርህ የገባቸው ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በወሬ፣ በሃሜት፣ በጥቆማ፣ በስማ - በለው ከሚወቅሱና ከሚከሱ ይገላግሉናልና፡፡
Iron in the fire ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ሁሉ ቦታ ጥልቅ ማለት አይገባም፡፡ ሁኔታዎችን ከማባባስና የከፉ ከማድረግ በቀር ምንም የረባ ዕድገት አናመጣም - በየነደደበት በመዶል፡፡
You aint the only duck in the pond ይህ ማለት በቁም ትርጉሙ ስናየው ኩሬው ውስጥ ያለኸው ዳክዬ አንተ ብቻ አይደህም የሚል ሲሆን፤ አገሩ ሁሉ ስላንተ የሚያወራ እንዳይመስልህ ማለትም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸውን ያህል ጠባያት በአግባቡና በቅጡ ከተቀዳጀን፤ ለመጪው ምርጫ፣ ፋይዳ መኖር ለዕለት - ተዕለት ዲሞክራሲያዊ አሂዶአችን፣ መሳካት ለፍትሕ - ርትዕ ርሃባችን መወገድ፣ ለመልካም አስተዳደር ዕውነተኛ ገጽታችን መበልፀግ፣ ለእጅ አመላችንና ለዕምነት ክልስነታችን መወገድ መጠነኛ አስተዋጽኦ ያደርግልናል፡፡
 “በሀገራችን ምርጫ በመጣ ሰዓት መንግስት ደግ ይሆናል” የሚል ሐሜታ ሁሌ ይነገራል። መንግስትም ይሰማል፡፡ ህዝብም ያውቃል፡፡ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም ዲሞክራሪያዊት ሂደት መሆኑን ማመን አለብን፡፡ ተለዋጭ ሁኔታን መቋቋም ያስፈልጋል፡፡
እነሆ ይሆኑናል፣ ይበጁናል፣ የምንላቸውን ሰዎች ስንመርጥ ሙያ - ከምግባር፣ ልብ -ከልቦና ያላቸው ቢሆን መልካም ነው፡፡ “አስወርተህ ሹመኝ፣ ዘርፌ አበላሃለሁ” የሚሊ መሆን የለባቸውም፡፡ ገዢ ፓርቲና ተገዢ ፓርቲ የጋራ የጨዋታ ሜዳ፣ የጋራ የጨዋታ ሕግ፣ ባላቸው አገር ደግሞ ሁነኛ ምርጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ፣ ጤናማ ላገር ማሰብ ነው፡፡ አዎንታዊነት ነው! የሻከረው ሊላግ፣ የከረረው ሊላላ፣ የጎደጎደው ሊሞላ ይችል ዘንድ የሁሉም ቅን ልቦና ያስፈልጋል፡፡ እስከመቼ ተሸካክረን? እስከመቼ ተቆሳስለን? እስከመቼ ተወነጃጅለን? እርስ በርስም ሆነ፣ ጎራ ለይተንስ እስከመቼ ተጠላልፈን? እስከመቼስ ብቻዬን እሰራዋለሁ ብለን እንዘልቀዋለን፡፡ ዕውነት ለሀገር ብለን ከሆነ ደፋ ቀና የምንለው፣ ዕውነት ለህዝብ ብለን ከሆነ በፖለቲካ የምንሞራረደው፤ በጠላትነት መፈራረጅና ለመጠፋፋት የምንሽቀዳደምበት ሜዳ ምንጠራ ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ የሄድነውን መንገድ ዘወር ብለን ስናይ በራሳችን ላይ መሳቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ታሪካችን የጠብ ነው፡፡ የመጣላት ነው፡፡ ቢያንስ ምርጫዎች ሲደጋገሙ ከጠቡ ቀነስ እያደረጉልን፣ እያሰለጠኑን መሄድ አለባቸው፡፡ “በጣም አንጣላ፤ ከታረቅን እንዳይቆጨን” የሚለው የትግሪኛ ተረት ይህን ይነግረናል፡፡

Read 5483 times