Saturday, 12 July 2014 12:46

በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ! “አንድ ይሁዲ ዘፋኝ በምጣድ መጥበስ እፈልጋለሁ!”

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

    በአብዛኛው የፖለቲካ መሪዎች ስኬትና ውድቀት የተመሰረተው በሚያከናውኗቸው ተግባራት ብቻ ሳይሆን ከአንደበታቸው በሚሰነዝሯቸው ቃላትም ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የፖለቲካ መሪዎች ከመናገራቸው በፊት ሁለት ሶስቴ ማሰብና ንግግራቸው ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት በቅጡ ማገናዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተቻለ መጠንም ራሳቸውን ከአፍ ወለምታ መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡
በፈረንሳይ ብሄራዊ ግንባር (Front Nationale) የተሰኘውን የፈረንሳይ አክራሪ ብሄርተኛ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት የሚታወቁትና በጥቁሮች፣ በስደተኞች አይሁዳውያንና በሮማዎች ላይ ባላቸው ከፍተኛ ጥላቻና የዘረኝነት አቋም በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በምድረ አውሮፓ ስማቸው የናኘው ዦን ማሩ ለፔን፤ ባለፈው ሳምንት አይሁዳውያንን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ከፍተኛ አቧራ አስነስቷል፡፡
ንግግራቸው ያነጣጠረው ቁጥራቸው በርከት ያለ አይሁዳውያን በተካተቱበት የፈረንሳይ አርቲስቶች ቡድን ላይ ሲሆን ለሰነዘሩት ክፉ ንግግር ሰበብ የሆናቸውም የብሔራዊ ግንባር ፓርቲያቸው በቅርቡ በተካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ የተቀዳጀውን ከፍተኛ ውጤት የአርቲስቶች ቡድኑ ተቃውሞ በማውገዙ ነው። አዛውንቱ ፖለቲከኛ ባቀረቡት ንግግር፤  “በሚቀጥለው ጊዜ ለእነዚያ ይሁዲ የአርቲስት ጥርቃሞዎች ሰፋ ያለ ምድጃ እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ ለአሁኑ ግን በዚህ ምጣድ የምጠብሰው አንድ ይሁዲ ዘፋኝ እፈልጋለሁ!” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እኒህ ነውጠኛ የፖለቲካ መሪ፤ በዚህ እጅግ ዘረኛ ንግግራቸው ስለምድጃ ያነሱት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በናትዚ ጀርመን እጅ ወድቀው በጋዝ ታፍነው ከተገደሉ በኋላ በትልቅ የማቃጠያ ምድጃ ተቃጥለው ያለቁበትን ሁኔታ ለመጠቆምና አሁንም ለአይሁዶች የሚገባው ቅጣት ይህ ነው ለማለት ነው። ዦን ማሪ ለፔን፤ በዘረኝነታቸውና በልቅ አንደበታቸው የታወቁ ቢሆንም ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ባላቸው ፈረንሳይ ይሁዲ ማህበረሰቦች ላይ የሰነዘሩት የአሁኑ መርዘኛ ንግግር ያስነሳው የፖለቲካ እሳት ግን እንዳለፉት ጊዜያት በቀላል ውግዘትና ተቃውሞ ብቻ የሚያልፍ አልሆነም፡፡ ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፈረንሳይ የፖለቲካ መድረክ የተሻለ ተቀባይነትና ድጋፍ እያገኘ የመጣውን የብሄራዊ ግንባር ፓርቲ ከስሩ የሚነቀንቅ ሆኗል፡፡ በአክራሪ ብሄርተኛ የፖለቲካ አቋሟና በዘረኝነቷ ከአባቷ ተለይታ የማትታየው የፓርቲው ሊቀመንበር ማሪን ለፔን እንኳን ንግግሩ በፓርቲው ህልውናና የወደፊት እንቅስቃሴ ላይ የደቀነው ከፍተኛ አደጋ በግልጽ ታይቷታል፡፡ ስለዚህም አደጋውን ለመከላከል ስትል በአባቷ ላይ እንድትነሳ ተገደደች፡፡  እናም፤ ማሪን ለፔን አደባባይ ቆመችና እንዲህ አለች:- “የፈረንሳይ አይሁድ ማህበረሰብን በተመለከተ አባቴ እንዲያ ያለ ንግግር በመናገሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ስህተት ፈጽሟል፡፡”
ይህን የሰሙት ሽማግሌው አባቷ ዦን ማሩ ለፔን ግን ስህተታቸውን አምነው ለመቀበል ጨርሶ አልፈለጉም። ይልቁንም “ለዚህ ያበቃኋት ልጅ በእኔ ላይ ከፍ ያለ ክህደት በመፈፀም ከጀርባዬ ወግታኛለች” በማለት ተቃውሞአቸውን ገለፁ፡፡
ዦን ማሪ ለፔን በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ባለፈው አርብ የብሄራዊ ግንባር ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ሰብስበው “ጎበዝ! በጠንካራ ብሄርተኛ አቋሙ የታወቀውን ፓርቲያችንን ወደ ተራና አጨብጫቢ ፓርቲነት እንዲቀየር በማድረግ አመራሩ ትልቅ የፖለቲካ ስህተት እየፈፀመ እንደሆነ ልብ በሉልኝ!” በማለት በተፈጠረው የፖለቲካ እሳት ላይ ነዳጅ ጨምረው ይበልጡኑ አጋጋሉት፡፡ፈረንሳውያን አሁን በጉጉት እየጠበቁት ያለው ልጅት ማሪን ለፔን በፓርቲዋ ላይ እየነደደ ያለውን እሳት እንዴት እንደምታጠፋው ለማየት ነው፡፡

Read 3672 times