Saturday, 12 July 2014 12:22

ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከጠፉ መንግስትም ይጎዳል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

የተቃዋሚዎችን ጥርስ ከማውለቅ የመኪናቸውን ጎማ ማስተንፈስ!  
የብራዚልና የጀርመን ጨዋታ የ97 ምርጫን አስታወሰኝ (ዱብዕዳ!)

አብዛኞቹ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሰሞኑን በብራዚል ላይ የደረሰውን ያልተጠበቀ ሽንፈት ለማመን አቅቷቸው ነው የሰነበቱት፡፡ የጀርመን ቡድን በእግር ኳስ ጥበብ ዝናዋ በናኘው ብራዚል ላይ 7 ጎሎችን አግብቶ ጉድ ይሰራታል ብሎ ማን ገመተ። (እንደ 97ቱ ምርጫ ማለት እኮ ነው!) ቢገመትማ ዱብእዳነቱ ይቀራል፡፡ አንዳንድ ሁሉ ነገር በሃርድ የሚመስላቸው  የኢህአዴግ ፍሬሽ ካድሬዎች፤ ኳስና ምርጫን ምን አገናኛቸው ብለው ሊደነፉ ይችላሉ (መደንፋት መብታቸው ነው!) እኛ ግን ምን እንደሚያገናኛቸው በእርጋታ የማስረዳት አገራዊ ሃላፊነት ተጥሎብናል፡፡ አንደኛ ሁለቱም ውድድሮች ናቸው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የሁለቱም ውጤት ዱብዕዳ ነው፡፡ የኢህአዴግም የብራዚልም ሽንፈት!!
በነገራችሁ ላይ በ97ቱ ምርጫ የአዲስ አበባን ውጤት አምኖ መቀበል የተሳናቸው የኢህአዴግ አመራሮች ብቻ አልነበሩም፡፡ ራሳቸው የቅንጅት መሪዎችም በዝረራ እናሸንፋለን ብለው አልገመቱም ነበር፡፡ (ለዚህ ይሆን እንዴ አያያዙን ያላወቁበት?!)
በብራዚልና በጀርመን ጨዋታ የብራዚልን ዱብዕዳ የሆነ ሽንፈት ማመን ያቃታቸው ቡድኖቹ ሳይሆኑ ደጋፊዎቹ ነበሩ (ቀላል አነቡ!) እኔ የምለው… በምርጫ መሸነፍ ያስለቅሳል እንዴ? (ያስደነፋል እንጂ አያስለቅስም!) ከአገራችን የቴሌቪዥን ተመልካቾችም የብራዚልን ሽንፈት ማመን ያቃታቸው አልጠፉም፡፡ አንዱ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ “የእኔ ቴሌቪዥን ተሳስቶ እንዳይሆን” በሚል ጓደኛውን ደውሎ እንደጠየቀው ሰምቻለሁ፡፡ በነጋታው በጨዋታው ዙሪያ በተደረገ ጨዋታ ደግሞ “የሆነ ነገር አዙረውባቸው መሆን አለበት እንጂ…” ሲሉ አንዳንድ የብራዚል ደጋፊዎች በጀርመን ቡድን ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል። የብራዚል የእግር ኳስ ባለሙያዎችና አንጋፋ ተጫዋቾች ግን ሽንፈቱን A blessing in disguise ነው ብለውታል። (ሳይደግስ አይጣላም እንደማለት!) “ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ ራሳችንን በቅጡ እንድንፈትሽ ዕድል ሰጥቶናል” ሲሉም ተፅናንተዋል። እኔ ግን “አያድርስ” ብየዋለሁ - የብራዚልን ያልተጠበቀ ሽንፈት። ፓርቲዎች በምርጫ ሲሸነፉ ሰማይ የተደፋባቸው ከሚመስሉ It is a blessing in disguise ማለትን ቢለምዱ መልካም ነበር፡፡ (ክንዳቸውን ሳይንተራሱ?)   
አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ጨዋታ እንግባ። ዚምባብዌ ውስጥ ነው አሉ - በአዛውንቱ የሙጋቤ አገር፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጥባጭ (Rogue) ዝሆኖች ከተፈቀደላቸው የመኖርያ ክልል በመውጣት የነዋሪዎችን ማሳና ጎጆ እየደረማመሱት ይሄዱ ጀመር። በፖለቲካ ቋንቋ “ነውጠኛ” ሆኑ ማለት ነው- ዝሆኖቹ፡፡ የዚምባቡዌ መንግስት ደግሞ ለ“ነውጠኛ ተቃዋሚዎች” እንጂ ለነውጠኛ ዝሆኖች ምላሽ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ እናም ትንሽ ታገሳቸው። ዝሆኖቹ ግን መደረማመሱ ተመቻቸው መሰለኝ ደጋግመው ወደ ገበሬዎቹ ማሳ በመመላለስ የከፋ ውድመት አደረሱ፡፡
ይሄኔ መንግስት በነውጠኛ ተቃዋሚዎች ላይ መውሰድ የለመደውን እርምጃ ሊወስድባቸው የጦር መሳሪያውን መወልወል ጀመረ - ቃታ ሊስብ፡፡ የማታ ማታ ግን አማካሪ አይጥፋ ሃሳቡን ቀየረ፡፡ እርምጃው በዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት መብት ተሟጋቾች ዘንድ መብጠልጠልንና መወንጀልን ስለሚያስከትል ሌላ መላ ተዘየደ - በአማካሪዎቹ ሃሳብ አመንጭነት። እናም የዚምባብዌ መንግስት በተለያዩ ድረ-ገፆችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተከታዩን መልእክት አሰራጨ፡-
“በመላው ዓለም ለዱር እንስሳት መብት ተሟጋች ነን የምትሉ ወገኖች ሁሉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዱርዬ ዝሆኖች ከመኖሪያቸው ክልል ወጥተው የህብረተሰቡን ህይወት እየረበሹ ነውና… በፍጥነት ደርሳችሁ በራሳችሁ ትራንስፖርት ሰብስባችሁ በመውሰድ ለምትፈልጉት ጉዳይ (ለሰርከስ ይሁን ለሌላ) መጠቀም እንደምትችሉ እያሳወቅን፤ ይሄን በአስቸኳይ ባታደርጉ ግን በዝሆኖቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እንደምንገደድ እንገልፃለን”
መረጃው በተሰራጨ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከዱር እንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች አንዱ በፈጣን አውሮፕላን ዚምባብዌ ገጭ አለ። ወዲያው ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ዝሆኖቹን ሰበሰበ፡፡ እድሜ ለመብት ተሟጋቾች! የዚምባብዌ ዝሆኖች “ነውጠኛ” በሚል ተፈርጀው በጅምላ ከመረሸን ተረፉ፡፡ የበለጠ ከሚያውቃቸው የአፍሪካ መንግስት ይልቅ በዱር እንስሳትነታቸው (በመንፈስ እንደማለት ነው) ብቻ የሚያውቃቸው ምዕራባዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት ህይወታቸውን ታደጋቸው፡፡ ለነውጠኞቹ ዝሆኖች  ተወልውሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ለተቃዋሚዎች (ለስልጣን ተቀናቃኞች ማለት ነው!) ተብሎ ተቀመጠ። (ለማስፈራርያ እኮ ነው!)
ከላይ የቀረበውን ታሪክ ያወጋኝ አንድ የቅርብ ወዳጄ ነው - አነበብኩት ብሎ፡፡ እኔ ታዲያ ወዲያው አንድ  ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንዲሉ… ዝሆኖቹ ከጅምላ ጭፍጨፋ የዳኑበትን ምስጢር ለአፍሪካ ተቃዋሚዎች ለምን አንጠቀምበትም አልኩኝ - ለራሴ፡፡ ትንሽ በውስጤ ካብሰለሰልኩት በኋላ ግን ይኸው ለናንተም አቀረብኩት፡፡ በዝሆኖቹ ታሪክ ኢንስፓየር ሆኜ ያመነጨሁትን አዲስ ሃሳብ!! ለየትኛውም የአፍሪካ መንግስት ከረባሽ ዝሆኖችና ከተቃዋሚዎች የቱን ትመርጣለህ የሚል ጥያቄ ቢቀርብለት፣ ረባሽ ዝሆኖችን እንደሚመርጥ ሳይታለም የተፈታ ነው። (ስልጣን መነቅነቅና ማሳ መደርመስን ምን አገናኛቸው?!)
እናንተ ስለአፍሪካ መንግስታት ያላችሁን ግንዛቤ በትክክል ባላውቅም እኔ ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፡፡ የአፍሪካ መንግስታት በምዕራባውያን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ስር ባይሆኑ ኖሮ፣ እስካሁን ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ መጥፋታቸው አይቀርም ነበር፡፡ ከተቃዋሚዎች ቀጥሎ እንደ ዳይኖሰር የሚጠፋው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ምርጫ” የሚለው ቃል ነው። ይሄን ቃል ተከታትለው ከአፍሪካ ምድር የሚጠፉት “ዲሞክራሲ” እና “የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት” የሚሉ ቃላትና ሃረጎች እንደሚሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ወደ ዋና ጉዳያችን ስንመለስ … ለአፍሪካ ተቃዋሚዎች ብዬ ያመነጨሁት ሃሳብ ለአፍሪካ መንግስታትም በእጅጉ የሚበጅ መሆኑን አስረግጬ እናገራለሁ፡፡ በነገራችሁ ላይ በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ተቃዋሚዎች በገዢው ፓርቲ ላይ የሚነሱትና “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ብለው ህብረት የሚፈጥሩት በምርጫ ዋዜማ ነው፡፡ ያኔ መንግስት ጠባይ ያለውን ሰብስቦ ወህኒ ያጉራል። ትዕቢት ትዕቢት የሚለው ካለ ደግሞ ጥርሱን ሊያወልቀው ይችላል፡፡
 እኔ የምለው…ባለፈው ሳምንት የአንድነት አመራር አባልን ጥርስ ያወለቁት የደህንነት ኃይሎች ናቸው የተባለው እውነት ነው እንዴ? (ጥያቄ ነው!) ከመንግስት ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠም ብዬ እኮ ነው (መች ተሰጥቶ ያውቃል እንዳትሉኝ!) ባለፈው ምርጫ የኢህአዴግ ካድሬዎች የአንድነትን የቅስቀሳ መኪና ጐማ አተነፈሱ ተብለው መወንጀላቸውን ሰምቼ ነበር። ከራሳቸው ከአንድነቶች፡፡ ነገርዬው ተገቢ ባይሆንም ጥርስ ከማውለቅ ግን ሺህ ጊዜ ይሻላል፡፡ (ማውለቅም ማተንፈስም ቢከለከል ጥሩ ነው!)
እናላችሁ ---- የባሰባቸው የአፍሪካ መንግስታት ዓይን ከማጥፋትም ወደ ኋላ አይሉም (ምን ነካችሁ--- ነገርዬው ሥልጣን እኮ ነው!) ይሄ ደግሞ ምዕራባውያኑ  ጆሮ መድረሱ አይቀርም፡፡፡ የአፍሪካ መንግስታት እቺን እቺን ፈፅሞ አይፈልጓትም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ሪፖርትም ይከተላል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጣጣ ያድናል ባይ ነኝ አዲሱ የመፍትሄ ሃሳቤ፡፡ እናላችሁ… የአፍሪካ መንግስት በምርጫ ዋዜማ ላይ ልክ ለረባሾቹ ዝሆኖች ያሰራጩት አይነት መልእክት በተለያዩ ሚዲያዎች ያሰራጫሉ - ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፡፡ እንዲህ ሊል ይችላል፤ መልእክቱ -
“በመላው ዓለም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን የምትሉ ወገኖች ሁሉ፤ በዚህች አገር ላይ የሚገኙ ነውጠኛ ተቃዋሚዎችን በራሳችሁ ትራስፖርት ሰብስባችሁ በመውሰድ (ለሰርከስ ይሁን ለሌላ) ለምትፈልጉት ጉዳይ መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እያሳወቅን፣ ይህን የማታደርጉ ከሆነ ግን በነውጠኞቹ ተቃሚዎች ላይ ተገቢ ያልነውን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን”
ይሄ ማሳሰቢያ በተሰራጨ በአጭር ጊዜ ውስጥ እነ አምነስቲና ሂዩማን ራይትስዎች በፍጥነት ደርሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ሰብስበው ከአጥፊነትም ከመጥፋትም ይታደጓቸዋል - እንደ ረባሾቹ ዝሆኖች ማለት ነው፡፡
በዚህም የአፍሪካ ተቃዋሚዎች እንደ ዳይኖሰር ከምድረ ገፅ ከመጥፋት ይድናሉ - በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጠባቂነት፡፡ የአፍሪካ መንግስታትም በየአራትና አምስት ዓመቱ ለምእራባውያን እርዳታ ሲሉ  ሲያደርጉት ከነበረው የይስሙላ ምርጫ ይገላገላሉ። (እፎይ ብለው የሰላም እንቅልፍ ይለጥጣሉ!) በሆነ ተዓምር ተቃዋሚዎች ከስልጣን ነቅንቀው ይጥሉን ይሆን? ከሚል ራስ ምታት ይገላገላሉ፡፡ (Win/Win Situation ይሏል ይሄ ነው!)
ወዳጆቼ፤ሌላው ሁሉ መፍትሔ ተሞክሮ ስላልሰራ ይሄ ደሞ ይሞከራ!! ተቃዋሚዎችን ከመጥፋት እንታደጋቸው፡፡

Read 2533 times