Saturday, 12 July 2014 12:14

ወደ አባይ መፍሰስ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

(የመጨረሻው ክፍል)
ያው!... ያው!... ያው እዚያ ማዶ!...
አባይ አባ ድፍርስ ሃምሳ ሜትር ከሚሆን የገደል አፋፍ ቁልቁል እየተግመለመለ ይወርዳል፡፡ ከዳር ዳር ሞልቶ፣ አራት መቶ ሜትር በሚደርስ ስፋት እየተገማሸረ ቁልቁል ይወረወራል፡፡ ይሄን ባሻገር ያለውን ተፈጥሯዊ ትንግርት ትንፋሽን ውጠው ዝም በማለት እንጂ፣ ተናግረውም ቃል ደርድረውም አይገልጹትም!...
አባይ አባ ቁጣ አንዳች ነገር ሳያበሳጨው አልቀረም፡፡ ደሙ እንደፈላ ግስላ ከአፋፍ ተወርውሮ ገደል ስር ራሱን ይፈጠፍጣል፡፡ እሪ እያለ ቁልቁል ተወርውሮ ከአለት ወለል ላይ ይጋጫል፡፡ አረፋ እየደፈቀ በነጎድጓዳማው ድምጹ ታጅቦ ጢሱን ሽቅብ ያትጎለጉላል፡፡ የቀስተዳመና መቀነት ችሎ ሸብ የማያደርገው ሽንጠ ሰፊው አባይ፣ ይሄው ከፊት ለፊታችን ይውረገረጋል፡፡
ግርምት አፍዝዞን ከቆምንበት አፋፍ፣ ግብናችንን ወደፊት መራመድ ጀመርን፡፡ ቁልቁል እየተገማሸረ የሚወርደው ፏፏቴ የሚረጫቸው ብናኝ የውሃ ፍንጣሪዎች፣ ሸለቆውን አልፈው መጥተው ፊታችን ላይ ጤዛ መስራት ጀምረዋል፡፡ ዙሪያ ገባው የጤዛ ኩታ በደረቡ ቁጥቋጦዎች ተሸፍኗል፡፡ የአባይ እንባ ያረሰረሰው ዳገት፣ በጤዛ ወርዝቷል፡፡ ዙሪያው ተፈጥሮ ፈትላ የሸመነችውን ያማረ አረንጓዴ  ሸማ ተከናንቦ ይታያል፡፡
አይኖቼን ቁልቁል ወደ ገደሉ ወረወርኳቸው፡፡ አባይ ከአፋፉ ተወርውሮ የሚያርፍበት ጭስ የተሞላ ገደል፣ የሲኦልን ምድጃ መስሎ ይታየኛል፡፡ ማደሪያ የለው ተብሎ የሚታማው መንገደኛው አባይ፣ ይዞት የሚዞረውን አገር ሙሉ ግንድ እዚህ ምድጃ ላይ ማግዶ በማይታይ እሳት እራሱን የሚያንተከትክ ይመስላል፡፡ አባይ ራሱን እያንተከተከ፣ ጢሱን ሽቅብ እያትጎለጎለ፣ በአሸባሪ ድምጽ እሪታውን ያስነካዋል። እኔ ከፊት ለፊቴ የሚሆነውን ሁሉ ፈዝዤ እያየሁ ቃል ሳልተነፍስ አፋፉ ላይ ቆሜያለሁ፡፡
“ዊ ጎ ቱ አባይ?” የሚለው የብላቴናው አስጎብኛችን ድምጽ ከተመስጦዬ አባነነኝ፡፡
“ዚስ ኢዝ ዳጥ!... ተእግራችሁ ቆንጠጥ እያረጋችሁ ነው መጓዝ!... ቬሪ ቬሪ ዳጥ!...” ብላቴናው ከአፋፉ ቁልቁል የምታስወርደዋንና ወደ ፏፏቴው የምታደርሰዋን ጠባብ መንገድ እየጠቆመ መናገር ጀመረ፡፡ እያስጠነቀቀን ነው፡፡ እርግጥም እንደኔ በአባይ ትዕይንት ለፈዘዘ እንግዳ፣ መንገዷ አስቸጋሪ ናት፡፡ በፏፏቴው ብኛኝ ውሃ ስለረሰረሰች ታዳልጣለች፡፡ እሷ አዳለጠችህ ማለት፣ አበቃልህ ነው፡፡ ቁልቁል ተንሸራተህ ገደሉ ስር ያለው የአባይ ምድጃ ውስጥ ከመማገድ ውጭ ምርጫ የለህም!... ይሄን ክፉ ሃሳብ እያሰላሰልኩ በፍርሃትና በስጋት ስሜት ተውጬ የቆምኩበትን የረሰረሰ መሬት አየሁት፡፡
“ኧረ ተጠንቀቁ ጋሼ!... ዘ ዳጥ ኢዝ አደገኛ!... ዘፎሊንግ ጎ… ዴዝ!...” የጉዞ ባልደረቦቼ ፎቶግራፍ ለመነሳት ሲሽቀዳደሙ ያየው ብላቴናው አስጎብኛችን በስጋት ድምጽ መልሶ ተናገረ፡፡  ብዙም ትኩረት እንዳልሰጡት ሲገባው፣ ወደ እንግሊዛዊው የጉዞ ባልደረባችን ሚስተር ክላርክ ጠጋ አለና መናገር ጀመረ፡፡
“ዩ ኖው ሚስተር?... ቢፎር ቢፎር ታይም ዚስ ዳጥ ፎልዳውን ኤ ፈረንጅ ቱሪስት ላይክ ዩ ዳይድ!...” አለ ብላቴናው ወደፏፏቴው አሻግሮ እያየ ትክዝ ብሎ፡፡ ሚስተር ክላርክ ብላቴናው የተናገረውን ነገር ሲያደምጥ በድንጋጤና በግራ መጋባት ፈዞ ቆመ፡፡
“ዋት ዱ ዩ ሴይ?...” ሚስተር ክላርክ ብላቴናውን እያየ በስጋት ሲጠይቅ፣ ሁላችንም መልሱን ለመስማት ጓጉተን ልጁ ላይ አፈጠጥን፡፡
ብላቴናው ከረጅም አመታት በፊት ተከሰተ ስለተባለና ታላቅ ወንድሙ ስለነገረው አደጋ መተረክ ጀመረ፡፡ እንደነገረን ከሆነ፣ የሆነ ጊዜ ላይ ከውጭ አገራት የመጡ ቱሪስቶች ፏፏቴውን ለመጎብኘት በቡድን ሆነው ወደዚህ ስፍራ ጎራ ብለው ነበር አሉ፡፡
ቱሪስቶቹ በአባይ ትንግርት ተገርመውና ተደንቀው ሲጎበኙ ቆዩ፡፡ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ማስታዎሻ የሚሆናቸውን ፎቶግራፍ እየተሳሳቁና እየተቃቀፉ በመነሳት ላይ ሳሉ ታዲያ፣ ያልታሰበ ነገር ይከሰታል፡፡ ከቱሪስቶቹ አንዷ በተፈጥሯዊው ውበት ሲበዛ ተደስታና አቅሏን ስታ ኖሮ፣ ከወዲያ ወዲህ እያለች ፎቶ ስትነሳ፣ መሬቱ አዳለጣትና ሚዛኗን ስታ ወደቀች፡፡
የሴትዮዋ ፍጻሜ አሳዛኝ ነበር፡፡ ከወደቀችበት አፋፍ ቁልቁል ተንከባልላ ገደሉ ስር ገባች፡፡ አባይም እንደ ገለባ እያላጋ ይዟት ተጓዘ፡፡ አብረዋት የመጡ ቱሪስቶችም ሆኑ የአካባቢው ሰዎች ቱሪስቷን ለማትረፍ አቅም አልነበራቸውም፡፡ የዚያች ምስኪን ሴት አስከሬን የአባይ አዞዎች ሲሳይ ሆኖ ቀረ፡፡
አሳዛኙን የብላቴናው ትረካ እየሰማሁ በፍርሃት ስርድ ይታወቀኛል፡፡
የቆምኩበትን መሬት አጥብቄ ረግጬ ፏፏቴውን አሻግሬ አየዋለሁ፡፡ ብላቴናውን ተከትዬ ወደ ገደሉ ለመውረድ የሚያስችል ድፍረት በውስጤ አልነበረም። እዚሁ ካፋፍ ላይ ቆሜ አባይን በቅርብ ርቀት እያየሁ መደመምን መርጫለሁ፡፡ በአባይ ተፈጥሯዊ ዜማ የታጀቡ ስለ አባይ የተቋጠሩ ስንኞች በእዝነ ህሊናዬ ሲንቆረቆሩ ይሰሙኛል - የገጣሚ ውዳላት ገዳሙ ስንኞች፡፡
“… ቀለም ዳምኖ ምድር አስውቦ
ዙር መቀነት አከናንቦ
ካለት አለት ተፈጥርቆ
ያገር አፈር ጥሪት ነጥቆ
እብስ አለ ሄደ ርቆ
ዛፍ ጉማጁን አተራምሶ
ገጸ ምድሩን ልሶ ልሶ
ሰው አራቁቶ ዳባ አልብሶ
ምድረ አበሻን አስለቅሶ
ጥርግ አለ ሆድ አስብሶ
ካንዱ ገፎ ሌላ ሽሮ
ካፋፍ ገደል ተገማሽሮ
ካናት ሜዳ ተጠቅሎ
ገደሏ ስር ተሸብሎ
ባፈር ቀልቶ እየደማ
አባይ ልጁን እያስጠማ
ቁጭት አዝሎ እምባ አቅዞ
እብስ አለ ግቱን ይዞ…”
 (ውዳላት ገዳሙ፣ እናትና ልጅ)
እንዲህ ብላ ተቀንኝታለት ነበር ውዳላት ገዳሙ፣ ለዚህ ከአይኔ ስር ለሚፈሰው አባይ ከአስር አመታት በፊት፡፡ ዛሬ ከአስር አመታት በኋላ ግን፣ አባይ ልጁን እያስጠማ፣ ወገኑን ሆድ እያስባሰ ወደሰው አገር የሚፈስ ከንቱ ወንዝ ብቻ አይደለም፡፡ ምድረ ሃበሻን ሆድ አስብሶና አስለቅሶ ወደጎረቤት አገር የሚገሰግስበት ዘመን እያበቃ ይመስላል፡፡
ዛሬ ለአባይ ሌላ ስንኝ ሌላ ዜማ ነው የሚዘፈነው። ዛሬ ለአባይ ሌላ ጥበብ ነው የሚከተበው፡፡ ነገ የሚጻፈውን… ነገ የሚዘመረውን… ነገ የሚዘከረውን የአባይ አዲስ ታሪክ ለመመልከት እጓጓለሁ፡፡
እየጓጓሁ እንዲህ ከፊት ለፊቱ ቁጭ ብዬ አባይን አየዋለሁ፡፡
አባይ አሁንም ይፈሳል…

Read 1588 times