Saturday, 12 July 2014 12:04

በፈት እየተለማመዱ ልጃገረድ ያገቧል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ሰዌን ሰንትዲ ጌለእዮ ኤኬቴስ” - የወላይታ ተረት

             ኒኮስ ካዛንትዛኪስ፤ “ዞርባ ዘ ግሪክ” የሚከተለውን ይላል፤ ሟቹ ዶክተር ዮናስ አድማሱ እንደተረጐመው:-  
ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት በአንድ ዛፍ ቅርፊት ሥር ሊፈለፈል የሚዘጋጅ አንድ የቢራቢሮ ሙጭ አፍጥጬ ስመለከት፣ ቢራቢሮዋ የተሸፈነችበትን ኮፈን ሰብራ ለመውጣት ቀዳዳ ስትቦረቡር አስተዋልኩ፡፡ ትንሽ ጠበቅሁ፣ ነገር ግን ጨርሳ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ስለፈጀች ትዕግስቴን ጨረስኩ፡፡ ከዚያም ትንሽ ጐንበስ ብዬ ሙቀት እንዲሆናት በማለት ተነፈስኩባት፡፡ የምችለውን ያህል በፍጥነት እየተነፈስኩ ሙቀት ዘራሁባት፡፡ ዓይኔ እያየ እዚያው አፍንጫዬ ሥር ታምር ሲሰራ ተመለከትኩ፡፡ እንደህይወት ቅጽበት፡፡
ኮፈኑ ተገለጠና ቢራቢሮዋ ቀስ እያለች መውጣት ጀመረች፡፡ ክንፎቿ ወደኋላ ታጥፈውና ጭምድድ ብለው ስመለከት መላ ሰውነቴን የወረረኝን ድንጋጤ ምን ጊዜም አልረሳውም፡፡ ምስኪኗ ቢራቢሮ ባላት ኃይል ሁሉ ሰውነቷ በሙሉ እየተንዘፈዘፈ ክንፎቿን ለመዘርጋት ሞከረች፡፡ እንደገና ጐንበስ ብዬ በትንፋሼ ልረዳት ሞከርኩ፡፡ ሙከራዬ ከንቱ ነበር፡፡ ቢራቢሮዋ መውጣት የነበረባት በዝግታ፣ ክንፎቿም መዘርጋት የነበረባቸው በፀሐይ ሙቀት በዝግመት መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ግን አልሆነም፡፡ ይረዳታል ያልኩት የኔ ትንፋሽ ቢራቢሮዋን ጊዜዋ ከመድረሱ በፊት፣ ክንፎቿም ጭምድድ ብለው የግድ ከኮፈኗ እንድትፈለፈል አድርጓት ኖሯል፡፡ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ለጥቂት ሴኮንዶች ከታገለች በኋላ መዳፌ ላይ ሕይወቷ አለፈ፡፡
ሸማ በፈርጅ እንደሚለበስ ዕውቀትም ፈርጅ ፈርጅ አለው፡፡ ከዕውቀትና ከተመክሮም በላይ ተፈጠሮ የራሱ ሂደት፣ የራሱ የላቀ የተለቀ እንዲሁም የጠለቀ መንገድ አለው፡፡ ከልኩ በላይ ሙቀት የተሰጣት ቢራቢሮ፣ ከልኩ በላይ ትንፋሽ የበዛባት ሙጭ ከተፈጥሮ ማህፀን ትላቀቅ እንጂ፤ ህይወቷን መቀጠል አልሆነላትም - ከተፈጥሮአዊ ጉዞዋ ቀድሞውኑ ተናጥባለችና ሁሉም የየራሱ ተፈጥሮአዊ ሂደት አለው - የየራሱም አቅም አለው፡፡ ስለሆነም በራሱ ሐዲድ ላይ እንጂ አንዱ በሌላው ሐዲድ ላይ አይሄድም፡፡ ዛሬ ሁሉም መንገዶች ወደ ሮማ አያመሩም፡፡ የተለያዩት መንገዶች ወደተለያዩ ከተሞች ይሄዳሉ እንጂ!
“”ቆሎ ለዘር፣ እንዶድ ለድግር አይሆንም” ይሏልና ሁሉን በቦታው ማዋል እጅግ ተገቢ ነገር ነው፡፡ በዓለም ላይ፤ በተለይም በፖለቲካ ትግል ውስጥ፣ ጊዜ የለየ፣ ቦታ የመረጠ ብቻ ነውና እግቡ የሚደርሰው፡፡
ጥበበኛ የፖለቲካ መሪ፣ ታጋይ፣ የሥራ ኃላፊ፣ የጐበዝ አለቃ ማስተዋል ካለበት ፍሬ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት የሮበርት ግሪን አስተያየቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በማናቸውም የሥልጣን ዘመን የሚያጋጥሙ “አምስት ዓይነት አደገኛ ሰዎች አሉ - በዓለም ላይ - ከእነዚህ ተጠንቀቅ” ሲል እንዲህ ይደረድራቸዋል :-
አንደኞቹ - ትዕቢተኛና ኩራተኛ ሰዎች ናቸው - ከነዚህ ዓይነቶቹ ራቅ፡፡
ሁለተኞቹ - ተስፋ - በሚያስቆርጥ ሁኔታ አደጋ ላይ ነን ብለው የሚያስቡ ስሜታቸው ስስና በቀላሉ ተሠባሪ ናቸው - ረዥም ጊዜ ራቃቸው፡፡ ሦስተኞቹ - እነ አቶ ጥርጣሬ ናቸው፡፡ እንደ ስታሊን ያሉቱ ናቸው፡፡ ሁሉ ሰው አጥፊዬ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ዒላማቸው ያደረጉህ ከመሰለህ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ፡፡ አራተኞቹ - የረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታ ያላቸው እባቦች የሚባሉት ዓይነት ናቸው፡፡ አይቆጡም፣ በፊት ለፊት የሚያሳዩት የንዴት ባህሪ የለም - ያደባሉ፣ ያሰላሉ፤ ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡ ይበቀላሉ፡፡ ማሺንክ ናቸው፡፡ ከእንዲህ ያለው እባብ እጥፍ -ጥንቃቄ አድርግ፡፡ አንዴ ካቆሰልከው እስከመጨረሻው ተገላገለው - ከሱ ጋር ግማሽ መንገድ አትሂድ - ከእይታህ ውጪ አድርገው፡፡ አምስተኞቹ - ግልብ፣ የሚያደርጉትን አስበው የማያደርጉ፣ አብዛኛውን ጊዜ ዕውቀት - ጠገብ ያልሆኑ (Unintelligent) ናቸው፡፡ ከምታስበው በላይ የማይታለሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው ከመጉዳቱ ወይም ከመበቀሉ ይልቅ የሚከፋው ጊዜህን፣ ጉልበትህን፣ ሀብትህን ከማባከኑም አልፎ ተርፎ ንጽህናህን ያጐድፍብሃል፡፡ በግልጽ አጥንተህ በግልጽ ፈትሸው፡፡
በሀገራችን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ችግሮች ለመላቀቅ በርካታ ጊዜ ጥያቄዎች ቢነሱም ባንዱ ችግር ላይ ሌላ እየጨመረ መፍትሔ እየራቀ መሄዱ ገሃድ ነው፡፡
ዕውቁ የሀገራችን ገጣሚና ፀሐፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በምኒልክ አንደበት “ችግሬን አላገኛችሁልኝም፡፡ ህመሜን አላወቃችሁልኝም፡፡ መድሃኒት አልኳችሁ እንጂ ለመከራዬ …አውጫጪኝ ምን ያደርግልኛል?”
እንዲሉ፤ ለችግራችን መድሃኒት ዛሬም በጋራ መፈለግ አለብን፡፡ የቃናችን፣ የልሣናችን፤ የቋንቋችን ህብር በአንድ ካልተቃኘ አገራችንን ከገባችበት አረንቋ ማውጣት ይከብደናል፡፡
“አንዱ ባለቀረርቶ፣ ሌላው ባለቄሬርሳ፣ ሦስተኛውም ያው ባለሽለላ ናችሁ፡፡ የሁላችሁም ውጤት በጠቅላላው ሲደመር፣ አንድ ባዶ ፉከራ ብቻ ነው ጩኸታችሁ፡፡ በኔ በምኒልክ ላይ ተቀያየራችሁብኝ እንጂ እናንተ ከቶም አልተቀየራችሁም፡፡ አንድ ናችሁ፡፡ ዛቻ፡፡ ማስፈራሪያ ብቻ…” ይላል፤ ያው ፀሐፌ- ተውኔት፡፡
ጩኸታችንን ቀንሰን ፍሬ የሚያፈራ ሥራ እንሥራ! በየጊዜው “በወደቀው ግንድ ላይ ምሳር ከማብዛት” የተለየ ነገር አገኘን ስንል፤ መልሰን ለጋውን ትውልድም ያላንዳች በሳል ጉዞ የምንረመርም ከሆነ፤ ሁለት ትውልድ ባንድ ጊዜ እናጣለን፡፡ ትውልድን ለማለምለም ገና ብርቱ ጥረት ይጠበቅብናል፡፡ ካለፈው እየተማርን መጪውን ካላሳመርን ውሃ - ወቀጣ ነው የሚሆነው፡፡ ከሁሉም ወገን “በፈት እየተለማመዱ ልጃገረድ ያገቧል”ን በቀና ትርጉሙ አይተን፣ “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል” ካላልን ከልማታችን ጥፋታችን እንደሚበረክት ልብ እንበል!!

Read 4407 times