Saturday, 05 July 2014 00:00

“በመሬት ቅርምት” ሚሊዮኖችን መመገብ ይቻላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተለያዩ ሀገራት እንደሚከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አይነት የተለያየ የኢንቨስትመንት አሠራሮችን ይከተላሉ፡፡ በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በየሀገሮቻቸው ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ለውጪ ባለሀብቶች የተፈቀዱና የተከለከሉትን በግልጽ ለይተው ያስቀምጣሉ፡፡
በእኛ ሀገር ለምሳሌ የፋይናንስ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኢነርጂ ሴክተሮች ለውጪ ኢንቨስትመንት ዝግ ሲሆኑ የእርሻው ሴክተር ግን ክፍት ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ለውጪም ሆነ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት አዘጋጅታለች፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች ታዳጊ ሀገራትም በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር ሰፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጪ ባለሀብቶች ይሰጣሉ፡፡ የአካባቢና የቀደምት ነዋሪ ማህበረሰቦች መብት ጥበቃ ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች፣ ሀገራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጪ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት የሚሰጡበትን አሠራር “የመሬት ቅርምት” (Land - grabbing) ይሉታል፡፡
የመብት ተሟጋቾቹ የወቅቱ “የትግል አጀንዳ” ይህን “የመሬት ቅርምት” አጥብቀው መቃወም ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ለተቃውሟቸው የሚያቀርቡት ዋነኛ መከራከሪያ፣ የቀደምት ነዋሪ ማህበረሰቦችን ጥንታዊ የአኗኗር ዘይቤ ያዛባል፣ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉና ለባሰ ችጋር እንዲጋለጡ ያደርጋል፣ የአካባቢ ጥበቃንም ያባብሳል፣ ባጠቃላይ የሀገሪቱን ነዋሪዎች ወደ ባሰ ድህነት ይከታል የሚል ነው፡፡
ሰሞኑን በአሜሪካ የቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት የተደረገ ጥናት ግን የመብትና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ተቃውሞ ፉርሽ የሚያደርግ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ሳይንቲስት ፓውሎ ዲኦዶሪኮና በኢጣሊያ የሚላኖ ፖሊ ቴክኒክ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ማሪያ ክርስቲና ሩሊ የተደረገው ጥናት፣ በ “መሬት ቅርምት” ከለማ እርሻ በሚገኝ ምርት ቢያንስ ሶስት መቶ ሚሊዮን ሰዎችን አጥግቦ መመገብ እንደሚቻል ይፋ አድርጓል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በታዳጊ ሀገራት የተደረጉ ከ200 ሄክታር በላይ የእርሻ የውጭ ኢንሽትመንት ስምምነቶችን እንዳጠኑ ተናግረዋል። ለውጪ ኢንቨስትመንት ከተሰጡ የእርሻ መሬቶች በተገኘ ምርት በኢንዶኔዢያ፣ በማሌዢያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒና በሱዳን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን በሚገባ መመገብ እንደተቻለ መረጋገጡን አክለው ገልፀዋል - ተመራማሪዎቹ፡፡

Read 1679 times