Print this page
Tuesday, 08 July 2014 07:51

ኢህአዴግ በርና መስኮት ያልተገጠመላቸው ኮንደሚኒየሞች ለመመረቅ ምን አስቸኮለው?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

ተቃዋሚዎች ቀጣዩን ምርጫ እናሸንፋለን ሲሉ “ፕራንክ” እያደረጉን  ይመስለኛል
ቤተመንግስት ሄጄ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ ነኝ” ለማለት አስቤአለሁ
የብርሃንና ሰላም የዋጋ ጭማሪና የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ተገጣጠሙ!


አርቲስት ሸዊት መኖሪያ ቤት የውጭ በር  ላይ አንድ ምስኪን ልጅ ተቀምጧል፡፡ ብዙም ሳይቆይ አርቲስቷ ኤክስክሉሲቭ ቶዮታዋን እያሽከረከረች ከግቢዋ ትወጣለች፡፡ ልጁ ፀጉሩን እያከከ ወደ መኪናዋ ይቀርብና  “አንድ ጊዜ ፈልጌሽ ነበር” በማለት ወርዳ እንድታነጋግረው ይጠይቃታል፡፡ ትሁት ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከመኪናዋ ዱብ ብላ ታናግረዋለች- “በሰላም ነው?” የሚል ጥያቄ በማስቀደም፡፡ “ከምን እንደምጀምርልሽ አላውቅም…” ይላል ልጁ እየተቅለሰለሰ፡፡ “እስከዛሬም የቆየሁት ለስምሽና ለዝናሽ አስቤ ነው…” ትንሽ ልቧን ካንጠለጠላት በኋላ ወንድሟ እንደሆነ ያረዳታል፡፡ ጠላታችሁ ክው ይበልና ክው ብላ ደነገጠች - ሸዊት፡፡ ልጁ እንዴት ወንድሟ እንደሆነ ማስረዳቱን  ይቀጥላል፡፡ አባቷ ዲላ በኮንስትራክሽን ስራ ላይ ሳሉ እዚያው ከሚሰሩ ሴት ጋር ተዋውቀው እሱ እንደተወለደ ይነግራታል፡፡
ድንጋጤዋ የጨመረው አርቲስቷ፤ “የእኔ አባት ግን… እርግጠኛ ነህ” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ አባቷ “ልጄ አይደለህም” ብለው መካዳቸውን እንዲሁም ከእሷ የሚፈልገው እንድታስተምረው ብቻ እንደሆነ እያለቀሰ ሲነግራት ሸዊት የበለጠ ትጨነቃለች፡፡ “ለማስተማሩ ችግር የለም… አስተምርሃለሁ --- እኔን የጨነቀኝ እሱ አይደለም” ትላለች- የአባቷን “ዲቃላ” መውለድ ማመን ያዳገታት አርቲስቷ፡፡ ሁኔታዋን ያየ ሁሉ በእጅጉ አዝኖላት “ምነው ቅዥት ባደረገላት” ሲል መመኘቱ  አይቀርም፡፡
በእርግጥም የተነገራት ነገር ሁሉ እውነት አልነበረም - ፕራንክ ነው (በቴሌቪዥን የሚቀርብ “አፕሪል ዘ ፉል“ ብትሉት ያስኬዳል!)  ሸዊትን ፕራንክ ያደረጓት የኢቴቪ 3 “ጨዋታ” ፕሮግራም አዘጋጆች ናቸው፡፡ በነገራችሁ ላይ ፕራንክ በቀጥታ ከፈረንጆቹ የተቀዳ (የተኮረጀ) ፕሮግራም ነው (መንግስትም እኮ ይኮርጃል!) እንዲያም ሆኖ ግን የሀበሻ ፕራንክና የፈረንጆቹ አራምባና ቆቦ ነው፤ ልዩነቱ የእኛ ፕራንክ በአብዛኛው የሚያዝናና ሳይሆን ቆሌ የሚገፍ መሆኑ ነው - በአርቲስት ሸዊት ላይ እንደተደረገው፡፡ አንዱ ደግሞ በምረቃው እለት ከዩኒቨርሲቲ የተላኩ ነኝ በሚል ሰው ፕራንክ ተደርጓል፡፡ ለምረቃ የሚያበቃ በቂ ነጥብ ስለሌለህ ጋውንህን ለመውሰድ ነው የመጣሁት በማለት ነው ሰውየው የተመራቂውን ቆሌ የሚገፈው፡፡ ራሳችሁን በተመራቂው ቦታ አድርጋችሁ በዚያ የደስታ ቀን የሚፈጠርባችሁን ስሜት አስቡት፡፡ በዚያ ላይ “እኔ እነደዚህ ዓይነት ቀልድ አልፈልግም” ብላችሁ የመናገር እድል እንኳን የላችሁም፡፡ አንዱ የጨዋታ ፕሮግራም አዘጋጅ አንዳንድ አርቲስቶች ፕራንክ በመደረጋቸው ቅር እየተሰኙ እንደሆነ ገልፆ ነገር ግን ፕራንክ መደረጉ ለራሳቸው እንደሚጠቅማቸው ሲናገር ሰምቼ ግርም አለኝ፡፡ (የድንጋጤን ጥቅሞች የምታውቁ ንገሩኝ!) ግን እነሱ ብቻ አይደሉም ፕራንክ የሚያደርጉን፡፡ ከመንግስት ጀምሮ እኛን ፕራንክ የማያደርግ  የለም። (“ሀበሻን መሸወድ ይቻላል” የሚል አዋጅ ፀድቋል እንዴ?) ለነገሩ ባይፀድቅም ችግር የለም፡፡ ፕራንክ መደረጋችን ትክክል አይደለም ብለን ተሟግተን አናውቅም እኮ!
በነገራችሁ ላይ አሁን ዱባይ ገቡ የተባሉትና “ባለ ጎልድ ሜዳሊስት ነኝ” ሲሉን የከረሙት ግለሰብ “ፕራንክ ነው ያደረግኋችሁ” ቢሉን እኮ በቀላሉ ይገላገሉ ነበር፡፡ ፕራንክ ነው ከተባለ ይፈቀዳላ! (ከመጭበርበር መሸወድ ይሻላል እኮ!?)
እኔ የምላችሁ… እነያ በሃቀኛ ታጋይነታቸውና ተራማጅነታቸው ዓለም የሚያውቃቸው የቀድሞው የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ የምድሪቱን ሰው ሁሉ “ፕራንክ” ሲያደርጉ አይደለም እንዴ የኖሩት? እሳቸው ለካ የናጠጡ የድራግ ከበርቴ ነበሩ፡፡ (“አፒራንስ ኤንድ ሪያሊቲ” ይሏችኋል ይሄ ነው!) መምሰልና መሆን ለየቅል ናቸው፡፡ አያችሁልኝ… ከፈጠራ ፕራንክ ይልቅ የእውነተኛው ዓለም ፕራንክ በእጅጉ የላቀና የመጠቀ ነው!
እናላችሁ… ተራማጅ ነን ባዮች፣ ከእኛ በላይ ለአገር ተቆርቋሪ ላሳር የሚሉ፣ ዲሞክራት ነን ባዮች … ሁሉም ፕራንክ ሲያደርጉን ነው የከረሙት - ሲሸውዱን። ለነገሩ እኛን (ሰፊውን ህዝብ ማለቴ ነው!) ፕራንክ የማያደርግ  ማን አለ? ሌላው ቀርቶ ከ40 ዓመት በፊት ንጉሱ “የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን…” እያሉ ህዝቡን ፕራንክ ሲያደርጉት ኖረዋል (መንግስት ሆኖ የማይሸውድ የለም እኮ!) ደርግማ ዕድሜ ዘመኑን ሁሉ ፕራንክ አድርጎናል፡፡ ኢህአዴግም ያው ነው - ፕራንክ ማድረግ ነፍሱ ነው። በነገራችሁ ላይ መንግስት ህዝቡን ፕራንክ እያደረገ ይሁን አይሁን ለማወቅ ቀላል ነው፡፡ ይሄውላችሁ … ፕራንክ የሚያደርግ መንግስት ሁልጊዜም “ህዝብ ህዝብ” ማለት ይወዳል፡፡ ቢፈልጥ ቢቆርጥ …ቢገድል ቢያስር…ቢዘርፍ ቢወርስ… ሁሌም ሰበቡ “የህዝብ ጥቅም ለማስከበር” የሚል ነው፡፡ ለህዝብ ጥቅም እያለ ህዝብ ይደፈጥጣል፡፡ በተለይ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች በህዝብ ስም መሸወድ ተክነውበታል፡፡ እናም ወደድንም ጠላንም ፕራንክ ስንደረግ ነው የኖርነው እያልኳችሁ ነው፡፡
ዝም ብዬ ሳስበው እኛ ሃበሾች ለፕራንክ ሳንመች አንቀርም፡፡ (እንዴ ሁሉም እየተነሳ እኮ ነው የሚሸውደን!) ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን ስንቴ ነው ፕራንክ ያደረገን? አንዴ “የስርጭት እንጂ የኃይል አቅርቦት ችግር የለብንም፤” “የመብራት መቆራረጡ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነ ደርሼበታለሁ” “ህዝቡ የመብራት ሃይል ኪራይ ሰብሳቢዎችን በመታገል ያግዘኝ” ወዘተ--- እያለ ሲሸውደን እኮ ነው የኖረው፡፡ ከምሬ ነው የምላችሁ --- መብራት ኃይል እኮ በጣም ግርምምም….የሚል መ/ቤት ነው፡፡ እኔ የምለው--- ኢህአዴግ ከስልጣኑ ለይቶ የማያያቸውን ሦስት የመንግስት ተቋማት ታውቃችኋላችሁ? - ቴሌ፣ መብራት ሃይልና ባንክ ናቸው፡፡ በእነዚህ የመጣ በዓይኑ መጣ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በገቢ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮምን የሚወዳደረው ያለ አይመስለኝም፡፡ (ከእነ ስሙ እኮ “የምትታለብ ላም” ወይም “የገንዘብ ማተምያ ማሽን” ነው  የሚባለው!)
ኢትዮ ቴሌኮም እንዴት ፕራንክ እንደሚያደርገን ለማወቅ ከፈለጋችሁ፣ በየቀኑ የሚልክልንን ቴክስት ሜሴጅ መመልከት በቂ ነው፡፡ እኛ ኔትዎርክና ኢንተርኔት ተቸግረናል፤ እሱ ሌላ ቴክኖሎጂ ላስተዋውቃችሁ እያለ መከራ ያበላናል (ፕራንክ መሆኑ እኮ ነው!)
እኛን ፕራንክ በማድረግ ሪከርድ የያዘው ግን  ኢቴቪ ነው!! (ከእሱ በስተቀር “ማርና ወተት የሚፈስባት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች” ያለን የለም!) ወደፊት እኮ አይደለም ዛሬ፣ አሁን አለች እያለ ነው ፕራንክ የሚያደርገን፡፡ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) በእነ ቢቢሲ ሞዴል ኮርፖሬሽን ሆኖ ሊቋቋም ነው ሲባል ሰምተናል፡፡ (የቻይናው ሲሲቲቪ እንዳይሰማ!) እኔ የምለው ግን…ከመቼ ወዲህ ነው ልማታዊ ሚዲያ የኒዮሊበራል ሚዲያን ሞዴል የሚያደርገው? (ኢቴቪ ውስጥ ኒዮሊበራሎች ሰርገው ገብተው እንዳይሆን?) ነገርዬው ፕራንክ መሆኑ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡
ሃቁን ልንገራችሁ አይደል---እዚህች አገር ላይ እኛን ፕራንክ ለማድረግ የማይደፍር ባለሥልጣን በሉት ተቋም እግራችሁ እስኪቀጥን ብትኳትኑ አታገኙም፡፡ አንድ የመንግስት ባለሥልጣን “የኮብልስቶን ሥራ ከኢንጂነሪንግ ሙያ እኩል ነው” ብለው ፕራንክ እንዳደረጉን አይረሳኝም። የእውነትና የዕውቀት መፍለቂያ የሚባሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችንም እንኳ ፕራንክ ያደርጉናል! (ጭንቅላታችንን ወስደው ባዶ ድግሪ ይሰጡናል!) ይታያችሁ… በድግሪና በማስትሬት ያስመረቁት ተማሪ፣ በእንግሊዝኛ አንድ ዓ.ነገር መፃፍ አይችልም ከተባለና በተመረቀ ማግስት ከኮብልስቶን ውጭ ሃሳብ የማይመጣለት ከሆነ ምን ልንል ነው - ተሸውደናል ከማለት ውጭ፡፡
ፕራንክ አድራጊዎች የመንግስት ተቋማት ብቻ ከመሰሏችሁ በጣም ተሸውዳችኋል፡፡ በግሉም ዘርፍ ሞልተዋል! (ከባለ ጎልድ ሜዳሊስቱ የማይተናነሱ!) አንዳንድ የአረብ አገራት ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስንቱ ፕራንክ አድርገዋል መሰላችሁ! (በሹፍርና ትቀጠራለህ ተብሎ ሄዶ የፍየል እረኛ የሆነውን ቤቱ ይቁጠረው!) በየቴሌቶኑ፣ በየድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ለስቴዲየም ግንባታ፣ ለሆስፒታል፣ ለግድብ፣ ለት/ቤት፣ ለስደት ተመላሾች ማቋቋምያ… በሚሊዮን ብሮች ለመስጠት ቃል ከገቡ በኋላ፣ የውሃ ሽታ ሆነው የሚቀሩ ባለሀብቶችም ፕራንክ እያደረጉን እኮ ነው (እያጭበረበሩን ነው ከማለት እየሸወዱን ነው አይሻልም?) በሚሊዮን የሚገመት አባላት አሉን፣ አባላቶቻችን መቶ ሺ ደርሰዋል፣ ወዘተ--- እያሉ ፕራንክ የሚያደርጉን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም በሽ ናቸው፡፡
በ97ቱ ምርጫ “መንፈስ ነው” እስከመባል የደረሰው ቅንጅትም እኮ በደንብ ፕራንክ አድርጐናል። (ፓርቲው ሳይሆን መሪዎቹ!) ቅንጅት የፈጠሩት ፓርቲዎች፤ የሥልጣን ዋዜማ ላይ ይሻኮታሉ ብሎ ማን ጠረጠረ? በዳግም ምርጫ
(በታክቲክና ብልሃት ማነስ!) ያሸነፉባቸውን የምርጫ ቦታዎች ለኢህአዴግ አስረክበው ሙልጫቸውን እንደሚወጡ ማን ገመተ? ፓርላማ አንገባም ብለው ወህኒ ቤት ለመግባት መወሰናቸውን ማን አሰበው? “ቅንጅት መንፈስ ነው…” እያሉ ቀላል ፕራንክ አደረጉን!! በእርግጥ ህዝቡም የዋዛ አይደለም፤ እሱም በተራው ተቃዋሚዎቹን ለ10 ዓመት ፕራንክ አድርጓቸዋል (ያልተቀየማቸው መስሎ ድምፁን ነፍጓቸዋል!)
በምርጫ 97 ኢህአዴግም እኮ እንደ ህዝቡ ፕራንክ ተደርጓል፡፡ መቼም መላ የአዲስ አበባ ህዝብ አይመርጠኝም ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም። ለነገሩ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት ምን እንደሚመስል ያወቀው  በምርጫ 97 ነው። (ህዝቡ ቀላል ፕራንክ አደረገው!)
ምርጫ በመጣ ቁጥር ከአውራው ፓርቲ ይልቅ የበለጠ የሚያስገርሙኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አንድም ቀን ከህዝብ ጋር የረባ ስብሰባ ያላደረገው ፓርቲ ሁሉ በምርጫው ኢህአዴግን በዝረራ አሸንፎ ሥልጣን እንደሚይዝ በአደባባይ ይደሰኩራል፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ የ“ቤቶች” ድራማው እከ እንደሚለው፤ ለሽ ብሎ የከረመው ፓርቲ ሁላ በምርጫ ዋዜማ ብድግ ይልና “ኢህአዴግን ከስልጣን ለማውረድ አንድ ወር በቂ ነው” ብሎ ሲፎልል ትሰሙታላችሁ፡፡ ይሄን ያመነ ፕራንክ ተደርጓል ማለት ነው፡፡
አትታዘቡኝና---አንዳንዴ “ኢህአዴግ ነፍሴም” የሚያደርጋቸውና የሚናገራቸው ነገሮች ፕራንክ ይመስሉኛል፡፡ (የግሌ ትዝብት እኮ ነው!) ለምሳሌ የሆነ ጊዜ ላይ .. አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ለማሰለፍ 30 ወይም 40 ዓመት በስልጣን ላይ የመቆየት (ይሄማ “መክረም ነው!”) ፍላጐት እንዳለው በይፋ መናገሩን አስታውሳለሁ፡፡ (ፕራንክ በሆነ አላላችሁም?!) ይኸውላችሁ ይሄ ዓይነቱ ንግግር ፕራንክ የማይሆነው ለዚምባብዌው መሪ ለሙጋቤ ብቻ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? እሳቸው ቢያንስ “ዚምባብዌ  የእኔ ናት!” ብለው ቁርጡን ተናግረዋላ፡፡ እኔ የምለው … ፓርቲዎች ከ20 ዓመት በኋላ  ጡረታ እንዲወጡ የሚያዝ አዋጅ እየተረቀቀ መሆኑን ሰምታችኋል? (ፕራንክ ላደርጋችሁ ፈልጌ ነው! )
በነገራችሁ ላይ…መንግስት የቱንም ያህል ፕራንክ ማድረግ ቢያስደስተው በመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ላይ ፕራንክ ያደርገናል ብዬ አላስብም፡፡ እንደውም ጭማሪውን ተከትሎ ነጋዴዎች በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳያደርጉ አስጠንቅቋል ተብሏል፡፡ ሆኖም ከ70 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተምያ ቤት ይሄን ማስጠንቀቂያ የሰማ አይመስለኝም፡፡
እናም ከሐምሌ 1 ጀምሮ በጋዜጣ ማተምያ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንደሚያደርግ ለጋዜጣ አሳታሚዎች በደብዳቤ አስታውቋል፡፡ (የደሞዝ ጭማሪና የዋጋ ጭማሪው ተገጣጥሞበት መሆን አለበት!) እንጂማ የደሞዝ ጭማሪው ተግባራዊ ይሆናል በተባለበት ሐምሌ 1 ብርሃንና ሰላም የጋዜጣ ማተምያ ዋጋ ለመጨመር አያስብም ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ግን የዋጋ ጭማሪው ፕራንክ ነው ብሎ ቢሸውደን ይሻለዋል (የመንግስት መመሪያ መተላለፍማ አደጋ አለው!)
ባለፈው እሁድ ማታ ቤቴ ቁጭ ብዬ የኢቴቪን ዜና ስኮመኩም፣ በሰሚት 21ሺ ገደማ የሚጠጉ  ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ የምረቃና የቁልፍ እርክክብ ሥነ-ሥርዓት መደረጉን ሰማሁና ደስ አለኝ። ሲያልቅ አያምር እንዲሉ ግን በዘገባው መቋጫ ላይ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ያነጋገራቸው ቤት ተረካቢዎች፤ ቤቱን መረከባቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው፤ መስኮትና በሮቹም በፍጥነት ይገጠማሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ በጥርጣሬ ተሞልተው ተናገሩ።
ድንግጥ አልኩ፡፡ (በር  ሳይገጠም ነው እንዴ ቁልፍ የተረከቡት?) ቆይ ግን ኢህአዴግ የት ለመሄድ ቸኩሎ ነው ያለ በርና መስኮት ቤቶቹን  ያስመረቀው? እኔ የምለው .. በርና መስኮት ሳይኖር ቤት ይባላል እንዴ? ወይስ ኢህአዴግ የቤት ባለቤቶቹን ፕራንክ ማድረግ ፈልጎ ነው? ለማንኛውም ቤት የሚባለው ምን ምን ሲያሟላ እንደሆነ ብናውቅ አይከፋም፡፡ ያለዚያ እኮ ነገ ደግሞ ጣራ ሳይመታ ቤት ነው ተብሎ ሊመረቅ ይችላል፡፡
ዓላማው የቤት ባለቤቶችን ፕራንክ ለማድረግ ከሆነ ግን በርና መስኮት ሳይገጠምለት ብቻ ሳይሆን ገና መሰረቱ ሳይወጣም ይቻላል፡፡ በነገራችሁ ላይ የኢቴቪ 3 ፕራንክ ፕሮግራም በጣም ኢንስፓየር ስላደረገኝ ቤተመንግስት ሄጄ “የጠ/ሚኒስትሩ ልጅ ነኝ፤ አገናኙን” ለማለት አስቤያለሁ፡፡ ድንገት በሆነ ተዓምር ከቀናኝ ግን ነገርየው ፕራንክ ነው አልላቸውም (የጠ/ሚኒስትር ልጅ መሆን ደስ ይላል እኮ!)

Read 3839 times