Saturday, 05 July 2014 00:00

“ስንት ሰዓት ነው?” ቢሉ ከተሜው፤ “የዘመኑ ሰዓትና የዘመኑ ሰው ውሸታም ነው፡፡ ዝም ብለው ጥላዎትን አይተው ይሂዱ!” አለ ባላገር፡፡

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ደራሲ ከበደ ሚካኤል ከፃፏቸው አጫጭር ትርክቶች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድፈረሰኛ ተራራ እየወጣ ሳለ፤ አንድ፣ አንድ እግሩ ቆራጣ የሆነ ሰው ያንን መንዲስ የሚያክልና ጫፉ ሩቅ የሆነ ተራራ፤ እየተንፏቀቀ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ያገኘዋል፡፡ ያም እግሩ የተቆረጠ ሰው፡-
“ጌታዬ እባክህ የተወሰነ መንገድ ድረስ አፈናጠኝና ውሰደኝ?” ሲል ይለምነዋል፡፡ ፈረሰኛውም ልቡ በጣም ይራራና፤
“እሺ ወዳጄ ፈረሱ የቻለው ርቀት ያህል አብረን እንሄዳለን፡፡ ና ውጣ” ብሎ፤ ወርዶ፣ አቅፎ ያፈናጥጠዋል፡፡
ትንሽ መንገድ አብረው ከተጓዙ በኋላ፤ እግረ ቆራጣው ሰውዬ፤
“ጌታዬ፤ ብዙ ምቾት አልተሰማኝም፡፡ አካል-ጉዳተኛ በመሆኔ አንደኛው እግሬን እጅግ ህመም ተሰማኝ!” አለው፡፡
ፈረሰኛው፤
“ታዲያ እንዴት ብናደርግ ይመችሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
አካል-ጉዳተኛውም፤
“ትንሽ መንገዱ እኔ ልሂድ፣ አንተ እግርህ ጤነኛ ስለሆነ ተከተለኝ” አለው፡፡
ፈረሰኛው በሁኔታው አዝኖ ልቡ ራራና፤
“መልካም፤ እኔ ልውረድ አንተ ሂድ፡፡ ሲደክመኝ ትጠብቀኝና ደሞ አብረን እንጓዛለን” አለውና ወረደ፡፡
የተወሰነ ርቀት፤ አካል-ጉዳተኛው በፈረስ፣ ባለፈረሱ በእግሩ ተጓዙ፡፡
ፈረሰኛው “ደክሞኛል ጠብቀኝ” አለው፡፡
እንደገና ተፈናጠጡና መንገድ ቀጠሉ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ፣ ፈረሰኛው ወረደለትና አካል ጉዳተኛው በፈረስ ቀጠለ፡፡ አሁን ግን ያ አካል-ጉዳተኛ ፈረሱን ኮልኩሎ ለዐይን ተሰወረ፡፡ ፈረሰኛው ቢሮጥ፣ ቢሮጥ ሊደርስበት አልቻለም፡፡
ባለፈረሱ ጮክ ብሎ፣ “እባክህ ሌላ ምንም አልፈልግም፣ የምነግርህን ብቻ አንዴ አዳምጠኝ?” አለው፡፡
ፈረስ ነጣቂው ባለቤቱ የማይደረስበት አስተማማኝ ቦታ ሲደርስ፤
“እሺ ምን ልትል ነው የፈለከው? እሰማሃለሁ ተናገር!” አለው በዕብሪት፡፡
ባለፈረሱም፤
“ወንድሜ ሆይ! አደራህን ይሄን እኔን ያደረከኝን ነገር ለማንም ሰው እንዳትነግር፡፡ ወደፊት በዓለም ደግ የሚያደርግ ሰው ይጠፋል!” አለው፡፡
*         *          *
ደግነት የብዙ ህይወታችን መሰረት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ቀናነት ካልተጨመረበት ዲሞክራሲም፣ ፍትሃዊነትም፣ ልማትም፣ አስተማማኝነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ደግ ያደረጉን ለመካስ ዝግጁ መሆን እንጂ ለክፉ ማጋለጥ አይገባም፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል፡፡ መምህራን የልጆችን ተስፋ አለምላሚ ናቸው፡፡ ወታደሮች የሀገር ህልውና ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ገበሬዎች የኢኮኖሚ ገንቢዎች ናቸው፡፡ የጥበብ ሰዎች የዘመን ዜማዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋዳሾች ናቸው፡፡  
“ሀብት ሲበዛ ዲሞክራሲ ይረጋገጣል ያለው ማነው?” ብሏል አንድ አዋቂ፤ ምን ያህል ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንደሚተሳሰሩ ሲያጠይቅ! ያለው ይናገራል፣ የሌለው ያፈጣል ወይም ሁሉን “እሺ” ይላል፤ የሚባል ነገር አለና አስተውለን ብናስብ ታላቅ ነገር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ፤ እየተሳሰቡ መጓዝን የመሰለ ነገር የለም፡፡ መከራችን፤ የሀገራችን የችግር ቁልል ተራራ አካል ነውና ለብቻ አይገፋም፡፡
ከረዥም ጊዜው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል አንፃር ስንመለከት ወጣቶች ልዩ ባህሪ እንዳላቸው እናስተውላለን - ታሪክን ዋቤ ቆጥረን፡፡ ባህሪያቸው፤ ቁርጠኝነትና ራስ - ወዳድ አለመሆን፣ ፍትሐዊነት፣ ጭቦኛ አለመሆን፣ የሴቶችን እኩልነት ማመን እና ትሁትነት የሚያካትቱ ልዩ ምልክቶቹ ነበሩ፤ ለማለት ያስደፍራል፡፡ እኒህ ምልክቶቹ ዛሬ ወዴት አሉ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው! እንጠያየቅ፡፡ ወጣቱን ያላቀፈ ጉዞ፣ ጉዞ አይደለምና!
አንጋረ ፈላስፋ፤
“ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ-ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይለናል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ የልማት፣ የኢኮኖሚ ድርና ማግ ናቸው እንደማለትም ነው፡፡ ባህልን ማክበር፣ አዋቂን ማድመጥ፣ ለዕውቀት መሪ ቦታ መስጠት፣ ጎረኝነትን ማስወገድና የጋራ መድረክ፣ የጋራ ሸንጎ መሻት፣ ዋና ጉዳይ መሆናቸውን መቼም አንዘንጋ፡፡
“የአያቴ ብስክሌት መንዳት አሪፍ መሆን እኔን ከመውደቅ አያድነኝም” ይላል ገጣሚ ሰለሞን ደሬሣ (ልጅነት)፡፡ በትላንት አበው ታሪክ መመካት ብቻውን ወደፊት አያራምደንም ሲል ነው፡፡ አንድም ነገን ዛሬ እንፍጠረው እንደማለት ነው፡፡ የሁሉም እኩል የሆነች አገር አጠንክሮ ለመጨበጥ እንዘጋጅ ሲልም ነው፡፡ እርስ በርስ የማንፈራራባት፣ የማንጠራጠርባት፣ ነጋችንን ጨለማ አድርገን የማናይባት አገር ነው መገንባት ያለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ አለመተማመን ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው፡፡ “ስንት ሰዓት ነው?” ቢሉ ከተሜው፤ “የዘመኑ ሰዓትና የዘመኑ ሰው ውሸታም ነው፡፡ ዝም ብለው ጥላዎትን አይተው ይሂዱ!” አለ ባላገር፤ የሚለው ቁም ነገር ነገን እንድናስተውል ልብ በሉ የሚለን ነው!

Read 5057 times