Saturday, 28 June 2014 10:53

የሃመር “ወጠሌ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

          በአኗኗር ዘይቤያቸው የቱሪስት ቀልብ ማረፊያ ከሆኑ የሃገራችን ብሄር ብሄረሰቦች መካከል ሃመሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በቆላማው አካባቢ የሚኖሩት ሃመሮች አርብቶ አደሮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ፍየልና የቀንድ ከብቶች የኑሮአቸው መሰረቶች ናቸው፡፡ የምግብ ውጤቶቻቸውም ከእነዚሁ እንስሳት የሚገኙ ናቸው፡፡
“ወጠሌ” ደግሞ ዋነኛው የሃመሮች የክብር ግብዣ፣ የማህበራዊ ህይወት መወያያ መድረኮች ማድመቂያ ምግብ ነው፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለሚዲያ ባለሙያዎች ባዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም መሰረት ወደ ሃመሮች መንደር በዘለቅንበት አጋጣሚም ተወዳጁ ወጠሌ በተመረጡ ባለሙያ ተሰናድቶ ቀርቦልን አጣጥመነዋል።
ይህ የሃመሮች ተወዳጅ ምግብ አዘገጃጀት እንዲህ ነው፡፡ በደንብ ስጋ የያዘ ወጠጤ ፍየል (በሬም ሊሆን ይችላል) ይመረጥና ይታረዳል፡፡ ስጋው በአግባቡ ይበለታል፡፡ ወጠሌን የማዘጋጀት ሙያው አላቸው ተብለው የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች (ሼፎች ማለት ይቻላል) ይመረጡና የወጠሌ ቦታ ይመርጣሉ። እሳት የሚቀበልና በደንብ እየተንቀለቀለ መንደድ የሚችል እንጨት ይመረጣል፡፡ እንጨቱ በተመረጠው ቦታ በረጅሙ ይጋደምና እሳት በሚገባ እንዲቀጣጠል ይደረጋል፡፡ በአግባቡ በየብልቱ የተበለተው ስጋ ቀጠን ባሉ እንጨቶች ላይ ጠልጠል ተደርጎ ይሰካል፡፡ አንድ የእግር ታፋ አንድ ቀጭን እንጨት ላይ እንዲሰካ ይደረጋል፡፡ ሌሎች የስጋ ብልቶችም በተመሳሳይ መልኩ በተዘጋጁት በርከት ያሉ እንጨቶች ላይ ይሰካሉ። መሃል ላይ ተጋድሞ በሚንቀለቀል እሳት ከሚነደው እንጨት በአማካይ እስከ 40 ሣ.ሜትር በሚደርስ መሬት ላይ ስጋው የተሰካባቸው እንጨቶች መሬት ላይ እየተሰኩ ተገቢውን ርቀት ጠብቀው ይደረደራሉ፡፡
ስጋዎቹ መብሰል ያለባቸው በእሳቱ በመለብለብ አልያም በጭስ ሳይሆን በሙቀት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል እሳቱና ጭሱ እንዳይነካቸው ባለሙያዎቹ የንፋሱን አቅጣጫ እየተመለከቱ ተገቢውን ማስተካከያ ያደርጋሉ፡፡
ስለ ብሄረሰቡ የምግብ አይነቶች ማብራሪያ የሰጡን ባለሙያ እንደነገሩን፤  በእሳት ሙቀት ብቻ እንዲበስል የሚፈለገውን ወጠሌን አዘጋጅቶ ለመብልነት ለማብቃት ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓታት ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለኛ የተዘጋጀውን በሙቀት የተጠበሰ ስጋ (ወጠሌ) ቀምሰን እንዳረጋገጥነውም እጅግ ጣፋጭ ነው፡፡ ስጋ በአይኔ አይዙር ያለ እንኳ ቢሆን በቢላዋ ሲቆረጥ በሚታየው የስጋው ማራኪ አበሳሰል ምራቁን መዋጡ አይቀርም፡፡
በብሄረሰቡ በአብዛኛው ይህ መሰሉ ምግብ የሚዘጋጀው የክብር እንግዶች ሲመጡና እና የሃገር ሽማግሌዎች ወይም የብሄረሰቡ መሪዎች ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልእክት ወይም ህዝባዊ ስብሰባዎች ሲኖር ነው፡፡
የአበላል ስነ-ስርአቱም ስጋው በሚጠበስበት (በሚወጠልበት) ዙሪያ ቅጠል ተነጥፎ ቅጠሉ ላይ በመቀመጥ ነው፡፡ ቅጠሉ ላይ የተቀመጠ ማንኛውም ሰው የወጠሌ ተቋዳሽ ይሆናል፡፡ መብላት የሚጀመረው በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት ሲሆን ቀዳሚ ተመጋቢዎች ወይም ቀማሾችም ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ከሁሉም በእድሜ አንጋፋ የሆኑት ደግሞ በሃመር ቋንቋ “ጎል” በተለምዶ “ፍሪምባ” የሚባለውን የስጋ አይነት ይመገባሉ፡፡ ከአንጋፋው በስተቀር ማንም ፍሪምባ መብላት አይፈቀድለትም፡፡ ሽማግሌው ጥርሱ እንኳ መብላት ባይችል ፍሪምባው ተሰጥቶት በሌላ ሰው አጋዥነት እንዲመገብ ይደረጋል፡፡ ይህም ለሽማግሌዎች የሚሰጠውን ክብር ላለማጓደል የሚደረግ ነው፡፡
ስጋው እየተበላ በስነ-ስርአቱ ላይ የሃገር ሽማግሌዎች ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሚባሉ ታላላቅ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ፡፡ የተላለፉ ህዝባዊ ውሳኔዎች ካሉም በዚህ ስርአት ላይ ብቻ ይነገራሉ፡፡ የስነ-ስርአቱ ማሳረጊያም የሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት ይሆናል፡፡
በብሄረሰቡ የተለያዩ የመጠጥ አይነቶችም ይዘወተራሉ፡፡ አብዛኞቹ ከማሽላ፣ ከበቆሎ፣ ከማር የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ ፋርሲ የሚባለው መጠጥ ከበቆሎና ከማሽላ የሚዘጋጅ ሲሆን በሌላው የሃገራችን አካባቢ ጠላ በመባል የሚታወቀው የመጠጥ አይነት ጋር ይመሳሰላል፡፡ “አላ” የሚባለው የመጠጥ አይነት ደግሞ ከበቆሎና ከማር የሚዘጋጅ ሲሆን የጠጅ አይነት ነው፡፡ ሽማግሌዎች ብቻ የሚጠጡትና ለምርቃት ስነ-ስርአት የሚጠቀሙበት ደግሞ የቡና ገለባ ተፈልቶ የሚዘጋጀው “ቡኒ” የሚባል መጠጥ ነው፡፡
በሃመር ብሄረሰብ ከወጠሌ ሌላ ሌሎች የምግብ አይነቶች ያሉ ሲሆን አንደኛው “ዝጎ” የሚባለው ከበቆሎ፣ ከማሽላና ከማር የሚዘጋጅ ምግብ ነው። ይህ ምግብ በብሄረሰቡ “የውሽማ ምግብ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ለውሽማ የሚቀርብ የፍቅር ምግብ ነው፤ የውሽማውን ጥንካሬ ለመጠበቅም ይጠቅማል፡፡ “ሙና” የተሰኘ ከበቆሎ፣ ከስንዴና ከማሽላ እየተድቦለቦለ የሚዘጋጅ በወተት የሚበላ ምግብም በሃመሮች ዘንድ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡  

Read 1947 times