Print this page
Saturday, 28 June 2014 11:04

ከዓለም በድህነት 2ኛ ናችሁ ሲባል “አይደለንም” የሚል ጠፋ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

ኦክስፎርድ ክፋቱ ነው እንጂ ገመናችንን ለእኛ ብቻ  መንገር ይችል ነበር
አንዱ ደሞ ተነስቶ በ“አፍ እላፊ” ከዓለም ቀዳሚ ናችሁ  እንዳይለን!
እንኳንም ለመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ተጨመረ (“እዬዬ ሲዳላ ነው” አሉ!)

እኔ የምለው…ማነው ለዓለም የኒዮሊበራል መንግስታት ሁሉ ቶሎ ግንፍል የሚል ደመ- ቁጡ መንግስት እንዳለን የነገራቸው? የነገራቸው ቢኖርማ ነው በየጊዜው ነገር የሚፈልጉን፡፡ ቆይ ከመቼ ወዲህ ነው የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ድሃ አገራትን እያጠና የTop 10 ደረጃ ማውጣት የጀመረው? (አንድ የመንግስት ተወካይ “የማንም እብድ እየተነሳ…” ያሉት እኮ ወደው አይደለም!) ለነገሩ ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላትም እኮ Famine የሚለውን ቃል ለማብራራት ምሳሌ የሚያደርገው እኛን ነበር! (ይሄ ታዲያ አጋጣሚ ነው ትላላችሁ?!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… እኔም ራሴ የጥናቱን ሪፖርት እንደሰማሁ…እንደመንግስት ተወካዩ ግንፍል ብዬ ኦክስፎርድን ያላወረድኩበት የስድብ ናዳ የለም (በሆዴ ነው ታዲያ!) በኋላ ሲበርድልኝ ግን ራሴን ታዘብኩት፡፡ የመንግስት ተወካዩ ግን እስካሁንም የሚበርድላቸው አይመስለኝም፡፡ (መንግስትና ግለሰብ አንድ አይደሉማ!) እናላችሁ ---- በኋላማ የንዴቴ ሰበቡ ገባኝ፡፡ ለካስ የተናደድኩት ድሃ አይደለንም ብዬ አልነበረም፡፡ (ድሃ አይደለንም ካልኩማ ከራሴ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኢህአዴግም ጋር መጣላቴ ነው!) ድሃማ ብንሆን ነው ኢህአዴግ “ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው” ብሎ ትግል ያስጀመረን፡፡ ቱግ ያስባለኝም የኦክስፎርድ ሪፖርት ሳይሆን  የሀበሻ “ወኔዬ” ነው፡፡ (ይሄ ማብራሪያ ራሴን እንጂ ቅድም የጠቀስኳቸውን የመንግስት ተወካይ አይመለከትም!)
ይኸውላችሁ-----ዝነኛው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ማፍራቱን ሰምቻለሁ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ልጅ የምትማረውም እዚያ ነው አሉ፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው---የተለየ ጠላትነት ከእኛ ጋር የለውም፡፡ እናም----- እቺ “በዕድገታችን ዓይናቸው ቀልቶ ነው” ምናምን የምትል አባባል ቦታ ያላት አትመስለኝም፡፡ ምናልባት መረጃዎችን ሲያሰባስብ የሳተው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ (“ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት---” ይባል የለ!) እሱም ቢሆን ታዲያ የእኛ ጥፋት እንጂ የዩኒቨርሲቲው አልመሰለኝም፡፡ (የተሟላ መረጃ ማቅረብ አለብና!) የፈለገ ቢሆን ግን አንዴ ሪፖርቱ ለዓለም ከናኘ በኋላ የኢትዮጵያን መንግስት ወክሎ የሚናገር ባለስልጣን፣ እንደ እኔ እንደተራ ተርታው ዜጋ በስሜት ቱግ ብሎ “የማንም እብድ እየተነሳ አጠናሁ…የሚለውን አንቀበልም” ማለት ተገቢ አይመስለኝም (እኔ ከእሳቸው ባላውቅም!) እንዴ…ያለ ስድብና ዘለፋ እኮ ኮሙኒኬት መደራረግ ይቻላል! (ኢትዮጵያ ውስጥ የዲፕሎማሲ ትምህርት ቀረ እንዴ?) ኦክስፎርድ ጥፋት አለበት ከተባለ ምን መሰላችሁ? በድህነት ከዓለም ሁለተኛ መውጣታችንን በአደባባይ ከማወጅ ይልቅ ለራሳችን በግል ሊነግረን ይችል ነበር፡፡ (ገመናችንን ለዓለም ከሚነዛው ማለቴ ነው!) እኛም ግን ፀባያችንን አሳምረን በመጠጋት ቀድመን ይሄንኑ ማማከር እንችል ነበር፡፡ ለወደፊቱ ትምህርት ነው!
አሁን አሁን ምን እንደምፈራ ታውቃላችሁ? አንዱ ዓለምአቀፍ ዩኒቨርሲቲ ድንገት ሳያስጠነቅቀን ተነስቶ “በአፍ እላፊ” ከዓለም አንደኛ ወጥታችኋል እንዳይለን ነው!(ገነባነው ያልነው መልካም ገጽታ ሁሉ አፈር ድሜ በላ ማለት አይደል!) እናላችሁ…ለዓለም አቀፍ መንግስታትና ተቋማት የሚሰጥ ምላሽና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የምንሰጠውን ምላሽ ማምታታት አይገባንም፡፡ አንደበቶቻችን ተለይተው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ተቃዋሚዎችን እስከ ዶቃ ማሰሪያቸው መንገር ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፡፡ (ኧረ ነውር ነው!) ቢያንስ ግን የራሳችን ገመና ነው (በውጭ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ፈረንጆቹ ጋ እስኪደርስ ማለቴ ነው!)
የሆነስ ሆነና --- የኦክስፎርድ ሪፖርት ውሸት መሆኑን የምናስተባብልበት ተጨባጭ መረጃ ተገኘ ወይስ አሁንም ዘለፋ ላይ ነን? (ከባለሁለቱ አሃዝ ዕድገት ውጪ ማለቴ ነው!) እኔ የምለው ግን ----ከድህነት ማጥ  ለመውጣትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ አልሞ የሚታትር መንግስት፣ ከዓለም ሁለተኛ ድሃ አገር ነው የያዝከው ቢባል ይቆጭ ይሆናል እንጂ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዴት ለዘለፋ ይነሳል? (“ዘራፍ!” የማለት ባህላችን እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው!)
በነገራችሁ ላይ በእዚሁ ጋዜጣ፣ የኦክስፎርዱን ሪፖርት አስመልክቶ ሁለቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሰጡት አስተያየት ተመችቶኛል፡፡ (የኦክስፎርድ ምሩቃን ናቸው እንዴ?) የድህነት ደረጃውን ስለተቀበሉት አይደለም፡፡ እውነት እውነት የሚሸት ነገር ስለተናገሩ ነው፡፡ በእንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ እውነት እውነቷን  የሚናገሩ የመንግስት ባለሥልጣናት ብናገኝ እኮ…ከድህነት የምንወጣበትን ጊዜ በእጅጉ እናፈጥነው ነበር፡፡ (ከእውነቱ በሸሸን ቁጥር ጉዟችን የኋሊት ይሆናል!)
ይኼውላችሁ…በሀሰት “የወርቅ ሜዳሊያ” ተሸላሚ ነበርኩ ማለት…እንኳንስ ለአገር ለግለሰብም እንደማይበጅ ሰሞኑን ታዝበናል፡፡ ውርደት እንጂ ክብርና ዝናን እንደማያስገኝም ተገንዝበናል። (አሁንም ግን ያልተገነዘቡ  አይጠፉም!) ትዝ ይላችኋል… የአዲስ አበባን አስፋልቶች የሚያፀዱ መኪኖች የመጡ ሰሞን አንድ የመስተዳደሩ ሃላፊ በኢቴቪ የተናገሩትን? እነዚህን መኪኖች በማስመጣት ከደቡብ አፍሪካ በቀር የሚቀድመን የለም ሲሉ “ቀደው” ነበር፡፡ (በኢንተርኔት ዘመን መዋሸት ከባድ እኮ ነው!) እናላችሁ -----እውነቱን ስንበረብር እነ ናሚቢያና ታንዛንያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከዓመታት በፊት የፅዳት መኪኖቹን ጥቅም ላይ እንዳዋሉ መረጃ አገኘን፡፡ (ስመረቅ “ጐልድ ሜዳሊስት” ነበርኩ እያሉ መተርተር  እኮ ይሄው ነው!)
በነገራችሁ ላይ ----- ብዋሽም ለአገሬ ብዬ ነው የሚባል ነገር አይሰራም፡፡ ውሸት ውሸት ነው!  አገርም ብትሆን እኮ የእውነት ሥሩልኝ፣ የእውነት አልሙኝ፣ የእውነት አሸልሙኝ----አለች እንጂ ዋሽታችሁ አበልፅጉኝ፣ ተተርትራችሁ “ጐልድ ሜዳሊስት” አድርጉኝ አላለችም፡፡ ደግሞስ ወላድ በድባብ ትሂድ እንጂ ምን አጥታ? በዓለም መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ደጋግመው ያጠለቁላት ወርቅ አትሌቶችን ያፈራች አገር እኮ ናት፡፡ ስለዚህ የፌክ ዝናና ስኬት ፈጽሞ አትሻም፡፡
ጦቢያ ከእንግዲህ ወዲያ የኢቴቪንም ሆነ የካድሬዎችን የ“ፌክ ገጽ ግንባታ” በጄ አትልም፡፡ በተለይ ኢቴቪ የማናውቃትን ኢትዮጵያ እየፈጠረ የሚፎግረንን ነገር ካልተወን “ጐልድ ሜዳሊስት” ነበርኩ ሲለን ከከረመው ግለሰብ ለይተን አናየውም፡፡ እንደውም እኮ የሱ ጉዳት ቀላል ነው፡፡ ኢቴቪ የሌለች አገር በምናቡ እየፈጠረ ለህዝቡ ሲያስኮመኩም ብዙ ሚሊዮኖችን እያሳሳተ በመሆኑ ጉዳቱ መጠነ-ሰፊ ነው፡፡ እናም ከዚህ በኋላ ለምንሰማው ወሬ ሁሉ ማስረጃ ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ (ፌክ ጨዋታ አብቅቷል!)
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ ሃርቫርድ ያንከራተቱን ግለሰብም “ኢንጂነር ነኝ” ያሉ ጊዜ የሚያፋጥጣቸው ቢያገኙ ኖሮ እኮ ቢያንስ “ዶክተር ነኝ” የሚለውን ውሸት እንቀንሰው ነበር። በነገራችሁ ላይ….የመንግስት መ/ቤት ሃላፊዎች የሚያቀርቡትን የሩብ ዓመትም ሆነ የሙሉ ዓመት ሪፖርት የሚያዳምጠው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ በቅጡ ፈትሾና መርምሮ ሪፖርቱ እውነት ይሁን “ፌክ” በግልጽ ሊነግረን ይገባል፡፡ (አባላቱን መርጠን ፓርላማ ያስገባናቸው ከፌክ ሪፖርት እንዲያድኑን እኮ ነው!)
ይኼውላችሁ…የመንግስት ባለስልጣን (ዳይሬክተር ይሁን ሚኒስትር) ፓርላማ ውስጥ ያቀረበው ሪፖርት ሁሉ እውነት ነው ብሎ መደምደም እጅግ አዳጋች ነው፡፡ (እውነት መሆኑ ቢረጋገጥማ ለፓርላማ ባልቀረበ ነበር) ለምሳሌ አሁን ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ የሚገኙት የገቢዎችና ጉምሩክ የሙስና ተጠርጣሪ ባለስልጣናት በመሬት ላይ ምን እየሰሩ፣ ለፓርላማ ምን ያቀርቡ ነበር? (አትጠራጠሩ! ብዙ ፌክ ሪፖርቶች ስንሰማ ከርመናል!) ሁሉም ባለስልጣን ቁጭ በሉ ወይም “ፌክ ሪፖርት” አቅራቢ ነው ብሎ ወደ ጥርጣሬ መግባት ግን ስህተት ነው። ስንት ጤነኛና  ታማኝ ባለስልጣን አለ እኮ - ለማህተቡ የሚሰራ!
በመንግስት ደረጃም እኮ በሰብል እህል ራሳችንን ችለናል በተባልን ማግስት 14ሚ. ህዝብ የእህል እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሰምተናል፤ አይተናል፡፡ ያልሆነውን ሆንን ተብለን ነበር ማለት ነው፡፡ አንዴ ደሞ በቆሎ በቀጣዩ ዓመት ኤክስፖርት እናደርጋለን የሚል ተስፋ ተሰጥቶን ስንጠብቅ የእርዳታ እህል ከለጋሾች ለምነናል፡፡ ከልመናው በላይ የጎዳን ግን እንዲህ ያለው አሳሳች መረጃ ነው፡፡ (ከ“ጐልድ ሜዳሊስቱ” በምን ይለያል?)
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ ምን መሰላችሁ? ድክመታችንንና ጉዶሏችንን የተናገሩብንን ሁሉ በጠላትነት  ፈርጀን እንዴት ልንዘልቀው ነው? እውነት ኢህአዴግ እንደሚለው… ይሄ ሁሉ  መንግስትና ዓለምአቀፍ ተቋማት እኛ በማደጋችን አይናቸው የሚቀላ ከሆነ እኮ ጉዳችን ፈላ፣ ቶሎ ብለን ወዳጅ ማድረግ ነው ያለብን፡፡ ቆይ ግን እኒህ ሁሉ ግን እንዴት ጠላቶቻችንን ሆኑ? (አገር አቀፍና ዓለምአቀፍ ጠላቶች በማፍራት የሚወዳደረን ጠፋ እኮ!) ይኼውላችሁ… እነሱ ሳይሰሙ እኛ በግድ ጠላቶች ያደረግናቸው ወገኖች እኮ በየጊዜው እየጨመሩ ነው፡፡ እስካሁን ለምሳሌ ከማስታውሳቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን- “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፣ “አምነስቲ ኢንተርናሽናል” እና “ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ)” ዋናዎቹ ሲሆኑ በቅርቡ ከአገር የተባረረው አርቲክል 19ም ሌላው ጠላታችን ነው፡፡ በመጨረሻ በጠላትነት ልንፈርጀው የተዘጋጀነው የዓለማችን ስመጥር ዩኒቨርስቲም አለ - ኦክስፎርድ! (ስመ-ጥር ቢሆንም እኮ ኒዮሊበራልነቱን አይለቅም!) እኔ የምለው-----ለቀጣዩ ትውልድ ጠላቶቻችንንም እናስረክባለን ማለት ነው? (ለካስ ብድር ብቻ ሳይሆን ጠላትም ይወረሳል!)
በእርግጥ አንዳንዴ ራሴን በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጫማ ውስጥ ከትቼ ነገሩን ስመለከተው ብግን የሚያደርግ ነገር አለው፡፡ “በትራፊክ አደጋ ከዓለም አንደኛ”፣ “ጋዜጠኞች በማሰር ከዓለም ሁለተኛ”፣ “በድህነት ከዓለም ሁለተኛ”፣ “ሰብዓዊ እርዳታ በመቀበል ከዓለም ሁለተኛ”…ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን መብገንና በቁጣ ቱግ ብሎ የሰው ሰው መዛለፍ ከሰለጠነ ልማታዊ መንግስት አይጠበቅም፡፡ (የአገርን መልካም ገጽታ ጥላሸት መቀባት እኮ ነው!) የሚያዋጣን ምን መሰላችሁ? እውነት እውነቱን ተቀብሎ ለማስተካከል መትጋት፡፡ እውነትና ሃሰት ተቀላቅሎበታል የምንለውን በመረጃ አስደግፈን ማስረዳት፣ ማግባባት፣ ማሳመን፡፡ (ተሳድበን ያሳመንነው ወገን እኮ የለም!) ፈጽሞ የማንቀበለው ካለ ደግሞ (ግን አለ እንዴ?) ሆድ ይፍጀው ብለን ወደ ስራችን መግባት!
ባለፈው ሳምንት ለአዲስ አድማስ አስተያየት የሰጡት የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ሙሼ ሰሙ፤ “ድህነቱን እየኖርኩት ስለሆነ የኦክስፎርድ ማስረጃና የአይኤምኤፍ ማስተባበያ አያስፈልገኝም”…ብለዋል (እውነታቸውን እኮ ነው!)፡፡ ለነገሩ ኢህአዴግ መራሹም መንግስት እኮ ድህነታችንን አልካደውም፡፡ ለምን በጆሮዬ አልተነገረኝም ብሎ ነው የተቆጣው (ሌላ የሚያስቆጣ የለማ!)  
ኡጋንዳ በቅርቡ ያወጣቸውን የፀረ-ግብረሰዶማዊነት ህግ ተከትሎ አሜሪካ ለጣለችው የጉዞና የእርዳታ ማዕቀብ፣የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የሰጠውን ምላሽ ሰምታችኋል? “አሜሪካ የወሰደችው አቋም አሳዛኝ ነው፤ አሁንም ግን ተባብረን መስራት የምንችልባቸው ሌሎች ዘርፎች አሉ” እኛ ማዕቀብ ቢጣልብን ምን ልንል እንደምንችል አስቡት፡፡ (መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ብለን እንሸኘዋለን!)
ከድህነት ወጥተን ወደ መንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ደግሞ እንግባ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ ባለፈው ቅዳሜ ባስነበበው መጣጥፉ፤ የመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ እንደሚጨመር ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል። ሳይውል ሳያድር ማለት ይቻላል መንግስትም የተባለውን የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ አረጋገጠ፡፡ ጭማሪው በእንዲህ ያህል ፐርሰንት ባይባልም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ችግሩ ግን ይላሉ የመንግስት ሠራተኞች፤ ከጭማሪው በፊት የሸቀጦች ዋጋ መናር ጀምሯል፡፡ በበርበሬ፣ በዘይትና በምስር ላይ እንደታየው፡፡ የግል ት/ቤቶችም ከ300ብር -500 ብር ጭማሪ አድርገዋል፡፡ መንግስት ግን እንደ ሁልጊዜው በእኔ ጣሉት እያለ ነው፡፡ የሸቀጦች የዋጋ ንረትን በዋጋ ቁጥጥር ሰጥ ለጥ አደርገዋለሁ ባይ ነው - ልማታዊው የኢህአዴግ መንግስት፡፡ ከአገሪቱ ማህፀን የበቀሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ የሸቀጥ እጥረትና ዋጋ መናር የሚከሰተው አቅርቦትና ፍላጐት ሳይጣጣሙ ሲቀሩ ነው በማለት ቁጥጥር መፍትሔ አይሆንም ይላሉ፡፡ የማንን እንመን? በመሰረታዊ የኢኮኖሚክስ ንድፈ ሃሳብ (Economics 101) እንኳን መግባባትና መስማማት አልቻልንም እኮ! (የቻይና የኢኮኖሚክስ ቲዮሪ ምን ቢሆን ነው ባካችሁ?) አረረም መረረም ግን የመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ መጨመሩ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ በዋጋ ንረት፣ በብር ዋጋ መቀነስ፣ በኢንፍሌሽን፣ ወዘተ… ከዓመት ዓመት ሲደቆስ የከረመው የመንግስት ሠራተኛ፤ እስቲ ትንሽ እንኳን ይተንፍስ (ጭማሪው የሚያስተነፍስ ከሆነ ማለቴ ነው!) አንዳንድ ወገኖች ግን የደሞዝ ጭማሪውን ኢህአዴግ ለብልሃቱ ያመጣው ነው ባይ ናቸው፡፡ የ2007 ምርጫ አክሰሰሪስ ነው ይላሉ - የደሞዙን ጭማሪ፡፡ ይሄ ደግሞ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር ሌጋሲ አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚል ስጋት አላቸው - እነዚሁ ወገኖች፡፡ ለምን ቢሉ? ጠ/ሚኒስትሩ በምርጫ ወቅት ለመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ መጨመርን አይደግፉም፡፡ ፖለቲካውን ያበላሸዋል የሚል ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡
የመንግስት ሠራተኛው ይሄኔ ጭማሪው በፐርሰንት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ በእጅጉ ጓጉቷል፡፡ ምርጫ ምናምን ትዝ ሊለው አይችልም (“እዬዬ ሲዳላ ነው” አሉ!)  እኔ በበኩሌ --- የደሞዝ ጭማሪው ከ11 ወር በኋላ በሚደረግ ምርጫ ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ ይፈጥራል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ደግሞስ ጭማሪው የቱን ያህል ቢሆን ነው ለገዢው ፓርቲ የሚጠቅም ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሆነው? በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ቀጣዩ ምርጫ እንደሚጠጥርበት መገመት አያቅትም፡፡ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና እጥረት በመንግስታዊ ተዓምር (አስማታዊ ክህሎት) ይፈታሉ ብለን ብንገምት እንኳን የመብራት መቆራረጥና መጥፋት እንዲሁም የኢንተርኔት እና የኔትዎርክ መቋረጥና መጓተት በቀላሉ የሚቀረፉ አይመስሉም፡፡ የታክሲ እጥረትና ወረፋም በአዲሱ የባቡር ትራንስፖርት መፈታቱ ገና እንደተስፋ የሚታይ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲታይ ኢህአዴግ ከ11 ወር በፊት ባደረገው የደሞዝ ጭማሪ ብቻ ትልቁን ምርጫ በድል እወጣዋለሁ ብሎ እንደማያስብ መገመት አዳጋች አይደለም (በተሳሳተ ስሌት ራሱን ካልሸወደ በቀር!)
በእርግጥ በአንዳንድ ክልሎች ምርጫ ላይ ያነጣጠረ የተሳሳተ ስሌት ገና ከአሁኑ የተጀመረ ይመስላል፡፡ ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ፤ በጋምቤላ ክልል 45ሚ.ብር የወጣበት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ብልሽት እንደገጠመው ይጠቁምና ይሄም ነዋሪዎችን ለከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደዳረጋቸው ይገልፃል፡፡ የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ምላሽ ነው፡፡ የተበላሹ የውሃ ፓምፖችን ለመጠገን 2ሚ.ብር ወጪ መደረጉን የጠቆሙት ሃላፊው፤ ነዋሪዎች በ2007 ምርጫ የተሟላ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ያገኛሉ ሲሉ አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል፡፡ ይታያችሁ ከ11 ወር በኋላ ማለት ነው። እስከዚያስ? ነዋሪው በውሃ ጥም ይለቅ? ማን ነበር “ያልበሰሉ ፖለቲከኞች ቀጣዩን ምርጫ አስበው ሲንቀሳቀሱ፤ የበሰሉ ፖለቲከኞች ቀጣዩን ትውልድ አስበው ይንቀሳቀሳሉ” ያለው? (እቺ “ሩቅ አልማ ሩቅ ለማደር የተጋች አገር” ፈርዶባት?!)   

Read 5703 times