Saturday, 28 June 2014 10:48

ለመብላት የጠፋ ቅቤ ስሞት በአፍንጫዬ ይፈስሳል፤ አለ ዶሮ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

(በቁም ያልረዳ ዘመድ ሲሞቱ አርባ ይደግሳል)

ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት ሰዎች አንድ ጫካ እያቋረጡ ሳሉ፣ አንዲት የወፍ ጫጩት ከዛፍ ላይ ጎጆዋ ወድቃ መሬት ላይ ያገኙዋታል፡፡
አንደኛው - “ቤቴ ወስጄ እንደ ዶሮ ጫጩት አሳድጋታለሁ” አለ፡፡
ሁለተኛው - “ለጥናትና ምርምር ትጠቅማለች፡፡ ወደ ላቦራቶሪ ወስደን ለባለሙያ እንስጣት” አለ፡፡
ሶስተኛው - “የለም ጎበዝ፤ ወደገበያ ወስደን እንሽጣት” አለ፡፡
በዚህ ክርክር ብዙ ከተሟገቱ በኋላ በዚያው አካባቢ የሚኖር አንድ ፈላስፋ አዋቂ ስላለ ወደሱ ዘንድ ሄደው ዳኝነት ሊጠይቁ ተስማሙ፡፡ ወፊቱን ይዘው አዋቂው ቤት ሄዱ፡፡
“ምን ልርዳችሁ ምን ላግዛችሁ?” አለና ጠየቃቸው፡፡ ተወካያቸው እንዲህ ሲል አስረዳ፡-
“ከዛፍ ጎጆዋ የወደቀች ወፍ አግኝተናል፡፡ አንዱ ቤቴ ወስጄ ላሳድጋት አለ፡፡ አንዳችን ለቤተ-ምርምር እንስጣት አልን፡፡ አንዳችን ገበያ ተወስዳ ትሸጥ አልን፡፡ ማንኛችን ነን ትክክል?”
ፈላስፋውም ጥቂት ካሰበ በኋላ፤
“ወዳጆቼ ሆይ! ለዶሮ ጫጩት የሚሆነው ኑሮ ለወፍ ጫጩትም ይሆናል ብሎ ያሰበ ተሳስቷል፡፡ ሁሉም የየራሱ ኑሮ ነው ያለው፡፡ አሳድጎስ ምን ሊያደርጋት ነው? ዓላማ ቢስ ይሆናል! ቤተ-ምርምር እንውሰዳት ያለውም ተሳስቷል፡፡” ለወፊቱ የሚጠቅማት ነገር የለምና፡፡ ወደገበያ ወስደን እንሽጣት ያለውም ከዚች ጫጩት ሽያጭ ማንኛችሁ ምን ያህል ልትጠቀሙ ነው? የማያዋጣ ጥቅም ከመፈለግ አለማድረጉ ይመረጣል” አላቸው፡፡
“እንግዲያስ ምን አድርጉ ትለናለህ?” አሉና ጠየቁት፡፡
ፈላስፋውም፤
“ከሁሉም የሚሻለው ወፊቱን ወደ ጎጆዋ መመለስ ነው፡፡ ኑሮዋን መልሱላት፡፡ ሰላሟን ስጧት፡፡ የተፈናቀለን ሰው እንደምታቋቁሙ ሁሉ ለወፊቱም እንደዚያ አስቡላት” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
*   *   *
ያለዓላማ ጉዞ ከንቱ ነው፡፡ ያለቅርስና ያለበቂ መሰረታዊ ጥቅም ነፃ-ገበያን መመኘት የጫጩት አትራፊነት ምኞት ነው፡፡ ያለብስለት ጥናትና ምርምር፣ ያለብቁ ባለሙያ ዕድገት ዘበት ነው፡፡ ኑሮው ካልተመለሰለት፣ ደሀ ጎጆው ካልተመለሰ፣ ልማቱ ከደረቀ፣ እሳቱ ካልሞቀ ተስፋው ይሞትበታል፡፡ ኑሮው መለወጥ አለበት፡፡ መታገዝ አለበት፡፡ ገቢና ወጪው መመጣጠን መቻል አለበት፡፡ ውሎ አድሮ ገቢው ይጨምር ዘንድ መንገዱ ሊጠረግለት ይገባል፡፡
ዛሬ እንደፋሽን የተያዘው ህገ-ወጥ ብልፅግና ነው፡፡ ሀገራዊ ስሜት ያለጥርጥር እየቀጨጨ ነው፡፡ ደምብና ሥርዓትን መጣስ እንደፋሽን ተይዟል፡፡ ድህነትን መቀነስ እንደአፍ አመል ሆኖ ይነገራል እንጂ በበሰለ መልኩ ህዝብ ውስጥ አልሰረፀም፡፡ ግማሽ ጎፈሬ፣ ግማሽ ልጩ የሆነ ካፒታሊዝም ከፋይዳው ማነስ ግራ ማጋባቱ ይብሳል፡፡ የምሁሮቻችን የድህነትን አሽክላ ለማስወገድ ዝግጁ አለመሆን፣ ከስራ አጥነት መዘዝ ጋር ተዳምሮ፣ ከአረንቋው እንዳንወጣ እያደረገን ነው፡፡ አዙሪቱ እጅግ ጥምዝምዝና ተደጋጋሚ ነው፡፡ “ከእለት እንጀራና ከትክክለኛ ምርጫ የትኛው ይሻላል?” ዓይነት አጣብቂኝ የድህነት የቤት ጣጣ ነው፡፡ ሀብት እኩል ባልተከፋፈለበት አገር ምርጫ 100% ተሳካ ሲባል አይገርምም ይላሉ ለበጠኛ አበው - ባለሙያዎች እንዲህ ግራ-ገብ ነገር ሲበዛባቸው፡፡ ከሁሉም ይሰውረን ማለት ትልቅ ፀሎት ነው፡፡
የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ኢ-አድሎአዊነትና ቀናነትን ይጠይቃል፡፡ የብዙሃን ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት አስፈላጊነት አጠያያቂ ያለመሆኑን ያህል፤ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል መሆናቸውን፣ በታሪክ የብቻውን ካሳ የሚያገኝ አንድም ፓርቲ መኖር እንደማይገባ፣ እርስ በእርስ መወዳደራቸው የዕድገት ማሺን መሆኑ እጅግ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ያለጭቦ መሳተፋቸውና መወከላቸው፣ የሲቪል ቡድኖችም ሊሳተፉበት ማስፈለጉ ገሀድ ጉዳይ ነው፡፡ በማግለል እንጂ በማሳተፍ የምናወጣው ነገር እንደሌለ ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡
ኑሮ ዛሬ ነው፡፡ ነገ ምኞት ነው፡፡ ህይወት በእጅ ባለበት ሰዓት የሚኖር እንጂ በምኞት የሚታቀድ አይደለም፡፡ ዛሬ መኖር መቻል አለበት፡፡ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በቀላሉ መገብየት አለባቸው፡፡ ቀን በቀን እየናረ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት ሳንገታ ዕድገትን ብናልም ምኞት ብቻ ነው፡፡ ለመብላት የጠፋ ቅቤ ስሞት በአፍንጫዬ ይፈስሳል፤ አለ ዶሮ የሚበላው ለዚህ ነው፡፡  

Read 5216 times