Saturday, 24 December 2011 07:49

የክለቦች በፋይናንስ መጠናከር እግር ኳሱን ያሳድጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ2012 ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚወዳደረው ቅ/ጊዮርጊስ ስፖንሰሮችን በመማረክ፣ የስታድዬም ግንባታውን በማቀላጠፍ እና የገቢ ምንጮቹን በማስፋት የያዘው የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫ ለአገሪቱ እግር ኳስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ተመለከተ፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈር ቀዳጅ የሚባለው የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሰሞኑን ከኩባንያዎች ጋር ክለቡን በከፍተኛ የፋይናንስ አቅም በሚያሳድግ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት እስከ 26 ሚሊዮን ብር ይገኝበታል፡፡

የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ከሳምንት በፊት እግር ኳስ ክለቡ ማልያ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱን ከደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር ሲያደርግ ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት በሚቆይ የውል ኮንትራት በየዓመቱ 5 ሚሊዮን ብር የሚከፈለው ይሆናል፡፡ የእግር ኳስ ክለቡ ሆራይዘን ከተባለ የጐማ ምርት አቅራቢ ኩባንያም ጋር ተጨማሪ የስፖንሰር ሺፕ ውል የፈፀመ ሲሆን ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት በልምምድ ማልያው ኩባንያውን እያስተዋወቀ በየዓመቱ 500ሺ ብር እንዲከፈለው ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የክለቡ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገልፁት ቅ/ጊዮርጊስ በፋይናንስ ራሱን ለማጠናከር በተያያዘው አቅጣጫ ከአፍሪካ 4 ትልልቅ ክለቦች ተርታ የመሰለፍ ራዕይ ይዟል፡፡   ቅ/ጊዮርጊስ ከማልያ ስፖንሰሩ ደርባ ሲምንቶ እና ከልምምድ ትጥቅ ስፖንሰር ሆራይዘን ጐማ በተጨማሪ ሌሎች ኩባንያዎችንም በዙሪያው አሰባስቧል፡፡ ክለቡ ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት በሚቆዩ የስፖንሰርሺፕ ውሎች ከሬይስ ኢንጂነሪንግ ከኒያላ ሞተርስ፣ ከአግሪሴፍትና ከኤሊኮ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እየሠራ ሲሆን ከሚድሮክ ኩባንያ በየዓመቱ የ1 ሚሊዮን ብር የስፖንሰሺፕ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በስታዲዮም ግንባታ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም ሰሞኑን ወደ ታላቅ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተሰጠው መግለጫ ለስታድዬሙ ግንባታ ሲከናወን የቆየው ቁፋሮ እንደተጠናቀቀ የተገለፀ ሲሆን የክለቡ የበላይ ጠባቂ ሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድዬሙን ለሚገነባው የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ 76 ሚሊዮን ብር ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፈሉ እና የግንባታ እቃዎች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸው ተወስቷል፡፡ በተመሳሳይ አቅጣጫ እየተጠናከረ ያለው ኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ የ2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከመጀመሩ በፊት የአምናው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ቡና ከሃበሻ ቢራ ፋብሪካ ጋር ባደረገው የማሊያ ስፖንሰርሺፕ ስምምነት 5 ሚሊዮን ብር አግኝቷል፡፡  ለሚቀጥሉት 5 ዓመት በሚቆይ የስፖንሰር ሺፕ ውል በክለቡ ማሊያ የሃበሻ ቢራ ሎጐን በመለጠፍ በዓመት 1 ሚሊዮን ብር እየታሰበለት የሀገር ውስጥና የአህጉር ውድድሮችን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ዓመት የሊጉ ሻምፒዮን ከመሆኑ በፊት በነበሩት የውድድር ዘመናት በፋይናንሻል አቅሙ ደካማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ኢትዮጵያ ቡና ከ3 ዓመት በፊት ከቡና ግብይት ተቋሙ ኢሴክስ ባለቤትነት ከተያዘ ወዲህ ያለበትን የፋይናንስ ችግር እየቀረፈ ነው፡፡ ክለቡ ከሜታ አቦ ቢራ ጋር በተመሳሳይ የማልያ ስፖንሰርሺፕ በማድረግ ባለፉት 3 ዓመታት 2.5 ሚሊዮን ብር አግኝቶ ነበር፡፡የኢትዮጵያ ቡና ከፍተኛ አመራር በክለቡ ድረ ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት ክለቡን በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ አቅምና፣ በመሠረተ ልማት በማጠናከር ወደ ፕሮፌሽናልም ደረጃ የመድረስ ራዕዩን እውን ለማድረግ  የክለቡ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ በዓመት 50 ቢሊዮን ብር በሚንቀሳቀሱበት የቡና ግብይት 30 በመቶ ድርሻ ያላቸው ቡና አብቃዮች፣ ጅምላ ሻጮች፣ ቡና ላኪዎች በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የቡና ኢንዱስትሪ የሚንቀሳቀሱ 25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከእግር ኳስ ክለቡ ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይ በሊግ ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች በፕሮፌሽናሊዝም መዋቅር በመንቀሳቀስ እድገት እንዲኖራቸው የገቢ ምንጮቻቸውን ማብዛታቸው ወሳኝ ነው፡፡ በመንግስት ተቋማት ድጋፍና በተወሰኑ ግለሰቦች አስተዋጽኦ የሚንቀሳቅሱ ክለቦች በተደራጀ ሁኔታ የስፖንሰርሺፕ ውሎችን በማከናወን መስራታቸው ተስፋፍቶ መቀጠል አለበት፡፡ክለቦች በስፖንሰርሺፕ ውሎች የገቢ ምንጫቸውን በማብዛታቸው በመምጣታቸው እና ፌዴሬሽኖች ከትላልቅ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመስራት ጥረታቸውን በማጠናከራቸው በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አንዳንድ አገራት በእግር ኳስ ዕድገታቸው አበረታች ለውጥ እንዲያገኙ እየረዳ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት በፕሮፌሽናሊዝም መዋቅር እግር ኳሳቸውን እያስተዳደሩ ባሉት በዩንጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ የሚካሄዱ ሊጐች በገቢ ምንጫቸው መጠናከር እና በፉክክር ደረጃቸው መጐልበት ተሻሽለዋል፡፡ በ5ቱ አገራት ያሉ ሊጐች  በተደራጀና ዘመናዊ አስተዳደር እየተመሩ በመሆናቸው ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን መማረክ ጀምረዋል፡፡ተባባሪ ስፖንሰሮች እና ደጋፊ ኩባንያዎችን እያሰባሰቡ ናቸው፡፡ ከሊጐቹ በብቃታቸውነጥረውበመውጣትወደአውሮፓክለቦች የመዛወር ዕድል ያላቸው  ተጨዋቾችም ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከ5 ዓመት በፊት የኬንያ ፕሪምዬር ሊግ ኩባንያ ከተመሠረተ በኋላ የሱፐር ስፖርት የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በመገኘቱ ለ5 ዓመታት በሚቆይ የስፖንሰር ሺፕ ውል የኬንያ ሊግ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አድርጓል፡፡ ሱፐር ስፖርት በኬንያ እግር ኳስ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እስከ 2016 በሚቆይ ስምምነት 12 ሚሊዮን ዩሮ ይሰጣል፡፡ በኬንያ የሚንቀሳቀሱ ትልልቅ ኩባንያዎች ለአገሪቱ ትልልቅ ክለቦች ኤፍሲ ሊዮፓርድስ፣ ጐሮማሃይ፣ ሶፋፓካና ማታሬ ዩናይትድን በማልያ ስፖንሰርሺፕ እየደገፉ ናቸው፡፡ የኬንያ ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች በፋይናንስ አቅማቸው በመደራጀታቸው የተጨዋቾችን ቅጥር ከናይጀሪያ፣ ከካሜሮን ከዲ.ሪ ኮንጐ እና ከኡጋንዳ ማከናወን ችለዋል፡፡ የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሠረተው የሚዲያ አጋርነት ውል፣ የሊጉ ጨዋታዎች በሱፐር ስፖርት ቻናል እየተሰራጩለት ነው፡፡ ክለቦች ከተለያዩ ኩባንያዎች በገቡት የማልያ ስፖንሰርሺፕ ውል በ2011 100 ሚሊዮን ብር አጋብሰዋል፡፡ ይሄው የገቢ ምንጫ መስፋት የሊጉን ውድድርና ተሳታፊ ክለቦቹን አቅም ከማጠናከሩም በላይ በታዳጊና ወጣቶች ፕሮጀክት ውድድሮች እንካሄዱና የተደራጀ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት ሆኗል፡፡  ሴካፋውድድሮችንማስተዳደር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ያላቸው ታንዛንያ በምስራቅ አፍሪካ በዘመናዊ ሁኔታ የሚካሄድ ሊግን በማደራጀት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ በስታድዬም ብዛት ያለው ተመልካች በማግኘቱ ከፍተኛ የገቢ አቅም እንዳለው የሚነገረውና በስፖንሰሩ ቮዳኮም ሊግ ተብሎ የተሰየመው የታንዛኒያ ክለቦች ውድድር ለዘንድሮ የውድድር ዘመን ከሊጉ ስፖንሰርሺፕ 607 938 ዩሮ ገቢ አድርጓል፡፡ በኡጋንዳ የክለቦች ውድድር ምንም እንኳን በቅርብ አመታት በብልሹ አስተዳደር ተናግቶ ቢቆይም ሱፐር ስፖርት በሊጉ ስፖንሰርነት ብቅ ብሎ የኡጋንዳ ሱፐር ሊግ ከተባለ በኋላ ለውጥ እያሳየ ነው፡፡ በአገሪቱ የቴሌኮም ኩባንያና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ትልልቅ ክለቦችን በስፖንስርሺፕ እየደገፉ ናቸው፡፡  5 የተለያዩ ክለቦች በኡጋንዳ ሰፊ ኢንቨስትመንትላቸው ኩባንያዎች ባለቤትነት በመያዛቸው በፋይናንስ አቅማቸው ለውጥ እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ሱፐር ስፖርት የኡጋንዳን የክለቦች ውድድር ስፖንሰር ሲያደርግ የሊጉን ኦፊሴላዊ ድረገጽ ያቋቋመ ሲሆን ዋና ዓላማው ሊጉን ከኡጋንዳዊያን ጋር በማቀራረብ የሚኖረውን ትኩረት መጨመር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከ5 ወራት በፊት በአገሪቱ በሚንቀሳቀስ የለስላሳ መጠጦች አምራች ኩባንያ ፕራይመስ ለ3 ዓመታት በሚዘልቅ የስፖንሰርሺፕ ውል በየዓመቱ በ383ሺ ዩሮ ማግኘት የበቃው ደግሞ የሩዋንዳ ክለቦች ውድድር ነው፡፡ የሩዋንዳ ትልቅ ክለቦች የመከላከያ ተቋማት የሚተዳደሩ ቢሆንም ሌሎች ክለቦች በአገሪቱ ባሉ ኩባንያዎችና የማህበረሰብ ተቋማት ሰፊ ኢንቨስትመንት እያገኙ ናቸው፡፡ በብሩንዲ የክለቦች ውድድርም በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ለውጥ በባለቤትነት የተያዙ ናቸው፡፡ የሊግ ውድድሩ አምስተል በተባለው የቢራ ጠማቂ ኩባንያ ሊጉ  ስፖንሰር ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገራት በአፍሪካ ዋንጫ እና በአህጉራዊ ደረጃ በሚደረጉ የክለብ ውድድሮች ተሳትፎ ማጣታቸውና ውጤት ማስመዝገብ የተሳናቸው በክለቦች ውድድሮች የተጠናከረና በፋይናንስ አቅም የተደራጀ አስተዳደር ሳይኖራቸው በመቆየቱ ነው፡፡ በተለይ ካለፉት 5 ዓመታት በዞኑ አንዳንድ አገራት የክለብ ውድድሮች በስፖንሰርሺፕ፣ በዘመናዊ አስተዳደርና በመንግስታት የላቀ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተጀመሩ ስራዎች ግን ተስፋ ሰጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በየአገሪቱ ያሉ የሊግ ውድድሮች በፋይናንስ አቅም መጐልበትና በዘመናዊ አስተዳደር መመራት ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ሊኖራቸው የሚቻለው ውጤታማነት ያሳድጋል ይህ ስኬት ደግሞ ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡

 

 

 

Read 3024 times Last modified on Saturday, 24 December 2011 08:05