Print this page
Saturday, 21 June 2014 14:21

የአሜሪካ ትላልቅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ስለትምህርት ደረጃቸው ምን ብለው ዋሹ?

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ቀለም የዘለቃቸው ዋሾዎች ከፖለቲከኞችም ይብሳሉ ተባለ!

           ባለፈው ሳምንት የአብዛኞቹ ሚዲያዎቻችን ሰበር ዜና የሆኑት ግለሰብ ለዚህ “ልዩ ጽሑፍ” መሰናዳት ሰበብ እንደሆኑኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡(እውነቱን መናገር ይሻላል ብዬ እኮ ነው!) ምስጋናውን ለማን ማቅረብ እንዳለብኝ ግን እርግጠኛ ስላልሆንኩ ለጊዜው “የምስጋና ማዕቀብ” ማድረጉን መርጬአለሁ፡፡ እናም በቀጥታ ወደ ርዕሰ ጉዳያችን እንግባ፡፡ ዛሬ አምዱ ለዋሾዎች ተለቋል (ድሮስ የማን ነበር አትሉኝም?)
ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ምን ሰማሁ መሰላችሁ? እኚህ የትምህርት መረጃቸውን አስመልክቶ ዋሽተዋል የተባሉት ግለሰብ እንግዲህ አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ ይታወቃሉ አሉ ?! እናላችሁ ---- በሳቸው የማነቃቂያ ንግግር ተነሳስተው ለውጥ ያመጡ አንዳንድ ግለሰቦች በጣም ተናደዱ ተባለ፡፡ ለምን መሰላችሁ? የውሸት አነቃቅቶናል ብለው እኮ ነው። እኔ የምለው ---- “ፌክ ማነቃቂያ” አለ እንዴ? (“የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” አሉ!) እንግዲህ በውሸት ማነቃቂያ ተነቃቅተን ነበር ያሉትን ሰዎች ወደቀድሞው “እንቅልፋቸው” መመለስ ከባድ ይመስለኛል፡፡ (የቀድሞ እንቅልፋቸውን ከፈለጉ ማለቴ ነው!)
እኔማ ምስኪኑ ከባባድ ውሸቶችን የሚዳፈሩት ፖለቲከኞች ብቻ ይመስሉኝ ነበር፡፡ ለካስ የቀለም ቀንድ የሚባሉትም ሳይቀሩ ድብን አድርገው ይዋሻሉና! (ተምሮ ውሸት አይደብርም?) ሰሞኑን ታዲያ በዋሾነት ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን ሳነብላችሁ ነበር (“የቸገረው እርጉዝ ያገባል” አሉ!) እናላችሁ…ባለ ከባድ ሚዛን ዋሾዎች ሲገጥሟችሁ ነገርየውን የሞራል ጉዳይ ብቻ አድርጋችሁ አትመልከቱት፡፡ ጉዳዩ ህክምና የሚሻ በሽታ ወይም አደገኛ ሱስ  ነው ይላሉ - አጥኚዎቹ፡፡
መቼም ዋሾነትን በተመለከተ የሰለጠኑት አገራት ተመክሮ ምን እንደሚመስል መቃኘት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለውድድርና ለንፅፅር ብቻ ሳይሆን ግንዛቤን ለማስፋትም ያግዛል፡፡ እናላችሁ---- ከኢንተርኔት ያገኘኋቸው በርካታ አስገራሚ መረጃዎች እንኳን ለእኔ ለናንተም የሚተርፍ ነው። (ለካ የሰለጠኑትም  ይዋሻሉ!) አሁን በቀጥታ የሰለጠኑ አገራትን የዋሾነት ተመክሮ ወደመቃኘቱ እንግባ፡፡ (የፅሁፉ ዓላማ መረጃ ማቀበል  እንደሆነ ይታወቅልኝ!) ከታላቋ እንግሊዝ እንጀምር። (እንግሊዝ የታሪኩ መቼት እንጂ ባለቤት አይደለችም!)
  እንግሊዛዊው የዝነኞች ሼፍ ሮበርት አይርቪንግ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ከገዛ ራሱ የምግብ ዝግጅት የቴሌቪዥን ሾው የተባረረው በሌላ ሳይሆን በዋሾነቱ ነበር፡፡ ይሄ ዓለምአቀፍ ሼፍ ምን ቢዋሽ ጥሩ ነው? “የልኡል ቻርልስና የልዕልት ዲያናን የሰርግ ኬክ የሰራሁት እኔ ነኝ” ብሎ ማውራት ማስወራት ጀመረ፡፡ (ያለዕዳው ዘማች አሉ!) የማታ ማታ ታዲያ የልኡሉንና የልእልቷን ኬክ የሰራው ሌላ ሼፍ መሆኑ በመረጋገጡ አይርቪንግ ቅሌት ተከናነበ፡፡ ኬኩ በተሰራበት ት/ቤት ተገኝቶ ከመመልከት ባሻገር ለኬኩ ማስጊያጫ የሚሆኑ ፍራፍሬዎችን ያቀረበ ቢሆንም ፈፅሞ ኬኩን በመስራት አልተሳተፈም ነበር፡፡ ተዋረድ ሲለው ግን እኔ ነኝ የሰራሁት እያለ “ሲሰጥ” ከረመ (ሳይቸግር ጤፍ ብድር አሉ!)
አሁን ደግሞ ወደ አማሪካ መጥተናል፡፡ ማሪል ጆንስ በማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ኮሌጅ ውስጥ ለ28 ዓመታት በዲንነት ያገለገለች ስትሆን መጀመርያ ስትቀጠር የባችለር ድግሪና ማስተርስ አለኝ ብላ ማመልከቻዋ ላይ ጽፋ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ጆንስ  የኮሌጅ ድግሪ የሚባል ነገር ፈጽሞ እንደሌላት ይፋ ሆነ፡፡ (“አበስ ገበርኩ” ማለት ይሄኔ ነው!) ዋሾነቷ ያተረፈላት ነገር ታዲያ በውርደት ከስራ መባረርን ብቻ ነው፡፡ (ሰው 28 ዓመት ሙሉ ይዋሻል?)
ጆንስ በ2007 ዓ.ም ሥራዋን ስትለቅ በዩኒቨርስቲው ድረገጽ ላይ ባሰፈረችው ጽሑፍ፤ የትምህርት ማስረጃዎቿን በተመለከተ ለተቋሙ የተሳሳተ መረጃ ማቅረቧን ጠቁማ፣  ያኔ ለሥራ ስታመለክትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት የትምህርት ማስረጃዎቿን የማስተካከል ወኔ እንዳልነበራት ተናግራለች (የምን ወኔ ነው የምታወራው?!) አሁን ማሪል ጆንስ፤ በበርክሌይ ኮሌጅ ኦፍ ሚዩዚክ የተማሪዎች ቅበላ አማካሪ ሆና እየሰራች ትገኛለች፡፡ (ውሸት አያስከስስም እንዴ?)
የIBM ሶፍትዌርን የሚሰራው “ሎተስ ዴቨሎፕመንት” ፕሬዚዳንት ጄፍሬይ ፓፖስ ስለትምህርቱና የውትድርና ታሪኩ የተናገረው ሁሉ ቅጥፈት መሆኑ የታወቀው ዘግይቶ ነው፡፡ ፓፖስ ፓይለት ነበርኩ ቢልም የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሆኖ የተገኘ ሲሆን የባህር ሃይል መቶ አለቃነቱንም በሻምበልነት ሽሮ ነው ሥራ የተቀጠረው፡፡ ይሄ ብቻ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ፒኤችዲውን ከፔፕርዲን ዩኒቨርሲቲ መቀበሉንም ለቀጣሪዎቹ ዋሽቶ ነበር፡፡ እውነቱ ሲወጣ ግን ፒኤችዲውን ያገኘው ዕውቅና ከሌለው የተልዕኮ ት/ቤት እንደሆነ ተጋለጠ።  ጄፍሬይ ፓፖስ ይሄን ሁሉ ቢዋሽም ከስራው አልተባበረም ነበር፡፡ ሆኖም ብዙም አልቆየ፡፡ የፆታ መድልዎ ፈጽሟል በሚል በቀረበበት ቅሬታ ሥራውን ለቀቀ። አሁን የMaptu Corp. and weblayers inc. ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡
በአንድ ወቅት የ”ሳሎሞን ስሚዝ ባርኔይ” ተቀጣሪ የነበረው ጃክ ግሩብማን፤ የዎልስትሪት ከፍተኛ ተከፋይ አናሊስት ነበር፡፡ በዓመት 20 ሚ. ዶላር የሚከፈለው (በወር ከ1.5 ሚ.ብር በላይ ማለት ነው) ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ ግን፣መጨረሻ ላይ የተማረበትን ዩኒቨርሲቲ በተመለከተ መዋሸቱ ታወቀበት፡፡  እሱ እንዳለው፤ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ኮሌጅ አልነበረም የተመረቀው፡፡ ከቦስተን ዩኒቨርሲቲ እንጂ፡፡ (እንደ እኛ አገር ዋናው መመረቁ ነው ተብሎ አልታለፈም!)
ግሩብማን ውሸቱ መጋለጡን ተከትሎ ለቢዝነስ ዊክ በሰጠው ቃለምልልስ፤ የዋሸው የሥራ ደህንነት ስጋት ተሰምቶት ሳይሆን እንደማይቀር ተናግሯል። (የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ግን የግብረገብነት ችግር ነው ባይ ናቸው!)
አሁን ግሩብማን፤ ለቴሌኮምና ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጥ Magee Group የተባለ ኩባንያ አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ (አሁንስ እንመነው?)  የቀድሞ የያሁ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ስኮት ቶምፕሰን፤ መጀመሪያ የተቀጠረው በአነስተኛ የስራ መደብ ስለነበር፣ የትምህርት ማስረጃዎቹን በተመለከተ ነገሬ ብሎ የመረመረው አልነበረም። እሱም ታዲያ ተመቸኝ ብሎ በደንብ ዋሸ፡፡ ከስቶንሂል ኮሌጅ በአካውንቲንግና በኮምፒዩተር ሳይንስ ሁለት ዲግሪዎች ተቀብያለሁ በማለት፡፡
የቀድሞው “paypal” ፕሬዚዳንት ቶምፕሰን፤ በጃንዋሪ 2012 ዓ.ም የያሁ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆኖ ሲሾም ነው ከዓመታት በፊት በገዛ እጁ የቀበረው ፈንጂ የፈነዳው፡፡ የያሁ ባለድርሻ የሆነው ዳንኤል ኤስ. ሎብ መረጃ ከየት እንዳገኘ ባይታወቅም የቶምፕሰንን የትምህርት ታሪክ ይፈትሽ ገባ። በመጨረሻም አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ ቶምፕሰን በአካውንቲንግ እንጂ በኮምፒዩተር ሳይንስ ድግሪ እንደሌለው አረጋገጠ። የቶምፕሰንን ዋሾነት በመንቀፍ አስተያየቱን የሰጠው ዳንኤል ኤስ ሎብ፤ “አሁን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የያሁ ኢንቨስተሮች እምነት የሚጥሉበት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሚያስፈልጋቸው ሰዓት ነው” ሲል የተናገረ ቢሆንም ለጊዜውም ቢሆን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይሄ ነው የሚባል እርምጃ አልተወሰደበትም፡፡  
የያሁ ሥራ አስፈፃሚ በዋሾነቱ የተነሳ ከስራው ባይባረርም፣ ከኃላፊነቱ ባይነሳም፣ የደሞዙ መጠን ባይቀነስም… ከሃፍረትና ከመሸማቀቅ እንደማይድን ቀጣሪዎቹ ነግረውት ነበር፡፡ (የዋሾነት ደሞዙ ሃፍረትና መሸማቀቅ ነው እንደማለት!) በነገራችሁ ላይ የእነዚህ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር ጉዳይ አንድ ሰሞን የአሜሪካ ጋዜጦች ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ (አንዱ ድግሪ የእውነት፣ ሌላኛው ድግሪ የውሸት እየሆነ አስቸገራቸዋ!)
ኬኔዝ ሎንቻር፤ “ቨሪታስ” የተባለውን ትልቁን የሶፍትዌር ኩባንያ የተቀላቀለው በ1997 ዓ.ም ነበር። ከአራት ዓመት በኋላ የውጭ ባለድርሻ አካላትን ውጤታማ በሆነ መንገድ በመምራት “CFo Magazine’s Excellence Award” አሸነፈ። በቀጣዩ ዓመት ግን ትከሻው ላይ የተደረበለትን የስኬት ፀጋ ተገፈፈ። ለምን ቢሉ? ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝቻለሁ ያለው MBA የውሸት መሆኑ በመረጋገጡ ነው። ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ ያለውም የአካውንቲንግ ድግሪ ቅጥፈት ነው ተባለ፡፡ እሱ ድግሪውን ያገኘው ከአይዳሆ ዩኒቨርስቲ ነበር። ይሄንን ተከትሎም የኩባንያው የስቶክ ዋጋ በ20 በመቶ አሽቆለቆለ፡፡ ከዚያም ሎንቻር በኩባንያው የተዘጋጀለትን መግለጫ ሰጥቶ  ሥራውን እንዲለቅ ተጠየቀ፡፡
“በዚህ የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃዬ አዝናለሁ። አሁን ባለው ሁኔታ ሥራዬን መልቀቄ ለእኔም ሆነ ለኩባንያው ጥቅም ይበጃል ብዬ አምናለሁ” ሲል ሚ/ር ኬኔዝ ሎንቻር የስንብት መግለጫውን ሰጥቷል።
በ1994 ዓ.ም “ሬዲዮ ሻክ”ን የተቀላቀለው ዴቪድ ኤድመንድሰን፤ የኩባንያውን የዕድገት መሰላል በከፍተኛ ፍጥነት ተወጣጥቶ፣ በ2005 ዓ.ም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ አዲሱን ሹመት ባገኘ በዓመቱ ግን “ፎርዝ ዎርዝ ስታር ቴሌግራም” የተሰኘው ጋዜጣ አንድ ውሸት አጋለጠ፡፡ ኤድመንድሰን ሥራውን ሲቀጠር እንደገለፀው፤ (እንደዋሸው ቢባል ይሻላል!) ከ “ኸርትላንድ ባፕቲስት ባይብል ኮሌጅ” በሥነ መለኮትና በሥነልቦና ድግሪውን አለማግኘቱን አረጋግጫለሁ አለ - ጋዜጣው፡፡  የሬዲዮ ሻክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከስራው እንዲባረር ባይፈልጉም ኤድመንድሰን ግን ሥራውን ለመልቀቅ ቅንጣት አላቅማማም፡፡ (ሃፍረቱ እንዴ ያሰራው?) “የትምህርቴን ጉዳይ በተመለከተ የተዛባ መረጃ  አቅርቤአለሁ፤ ለዚህ መዛባት ተጠያቂው እኔ ብቻ ነኝ። አሁን የሥነመለኮት ዲፕሎማ ማቅረብ እንደማልችል አውቃለሁ” ብሏል - ከመልቀቁ በፊት በሰጠው መግለጫ፡፡
የዓይን ጤና መጠበቅያ ምርቶችን የሚያቀርበው “Bausch and Lomb” የተሰኘው ኩባንያ የቀድሞ  ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሮናልድ ዛሬላም የዋሾነት ሰለባ ከመሆን አልዳኑም፡፡ እሳቸው ደግሞ ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ኤምቢኤዬን ተቀብያለሁ በማለት ነው የዋሹት፡፡ በእርግጥ ትምህርቱን ጀምረውት ነበር፤ ሆኖም ዳር ሳያደርሱት ማቋረጣቸውን ዩኒቨርስቲው ጠቁሟል፡፡ እናም ለዚህ ዋሾነታቸው የ1 ሚሊዮን ዶላር ቦነሳቸውን አጥተዋል፡፡ ሥራቸውን ግን አላጡም፡፡ “ለኩባንያው በጣም አስፈላጊ ናቸው” ተብለው በሃላፊነታቸው ሊቀጥሉ ችለዋል፡፡ የማታ የማታ ግን (በ2008 ዓ.ም) ኩባንያው እጅግ በርካታ የታዘዙ ምርቶቹ ተመላሽ ሲሆኑና በፍ/ቤት ክስ ሲጨናነቅ ዛሬላም ጥለውት ውልቅ አሉ፡፡
የኖርዌይ ተወላጇ ሊቭ ሎበርግ፤ በፍ/ቤት ተከስሳ ጥፋተኝነቷ ከመረጋገጡ በፊት፣ ለበርካታ ዓመታት በጤና እንክብካቤ ዘርፍና በሌሎች የመንግስት ተቋማት በከፍተኛ የአስተዳደር ቦታዎች ላይ ተመድባ ስታገለግል ቆይታለች፡፡ (በአገሯ ኖርዌይ ማለት ነው!) በኖርዌይ የፕሮግረስ ፓርቲ ውስጥም በፖለቲከኛነት ተሳትፋለች፡፡ (ውሸት ለፖለቲከኛ ብርቁ አይደለም!)
በ2010 ዓ.ም ነው አንድ ጋዜጠኛ እውነቱን ያፍረጠረጠባት፡፡ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ፣ ከኩዊን ሜሪ ኮሌጅና ከኖርጅስ ሃንድልሾይስኮሌ አግኝቻለሁ ያለቻቸው ድግሪዎች በሙሉ የውሸት እንደሆኑ ጋዜጠኛው አጋልጧል፡፡ ሌላው ቀርቶ በመንግስት የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣት (Certified) ነርስ እንደሆነች ስትናገር የከረመችው ሁሉ ቅጥፈት መሆኑ ተነገረ፡፡ ሎበርግ፤ እንኳንስ ኮሌጅ ልትገባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንኳን አላጠናቀቀችም ነው የተባለው፡፡ የነርስ ትምህርቷም የአንድ ዓመት የተግባር ትምህርት ብቻ እንደሆነ  ታውቋል፡፡ የዚህችን እንስት ጉዳይ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው በፍ/ቤት መከሰሷ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም ፍ/ቤቱ ጥፋተኛነቷን አረጋግጦ፣ የ14 ወር እስርና የገንዘብ ቅጣት በይኖባታል፡፡ (በኖርዌይ ውሸት ያስከስሳል ማለት ነው?!) እንግዲህ የተለያዩ የውሸት ገፆችና መልኮችን ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ የአገራችን የሥነልቦና ባለሙያዎች ዋሾነትን በተመለከተ የሚሰጡት ትንተና ምን እንደሆነ ባላውቅም የውጭዎቹ ግን አደገኛ በሽታ ስለሆነ የህክምና ባለሙያ እርዳታ ያስፈልገዋል ይላሉ። ዋሾዎቹ ወደ ወህኒ ቤት ከመወሰዳቸው በፊትም ሆስፒታል መግባት እንዳለባቸው ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ? እንዲህ ከሆነ እኮ ሆስፒታሎቻችን በሙሉ በፖለቲከኞች ሊጨናነቅ ነው፡፡ እነ ዓለም ባንክ የፋይናንስና የባለሙያ እገዛ ካላደረጉልን ነገሩን በራሳችን አቅም ብቻ  እንደማንወጣው እርግጠኛ ነኝ። (ወይስ ፀበል እንሞክር ይሆን?)

Read 2960 times
Administrator

Latest from Administrator