Saturday, 21 June 2014 14:13

“ዓለም ነገ ልታልቅ ነው ቢሉኝም፣ ዛሬ ዛፍ መትከሌን አልተውም” (ማርቲን ሉተር)

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“የሚስቅልህ ሰው ስለበዛ፣ ትክክል ነኝ ብለህ አታስብ”
(የእንግሊዞች አባባል)

ከዕለታት አንድ ቀን አንደ ቀንድ - አውጣ (Snail) ወደ አንድ ቡና ቤት ከመሸ በኋላ ይሄዳል፡፡ ከዚያም በሩን ያንኳኳል፡፡
ባለቡና ቤቱ፤ በሩን ዘጋግቶ እየጨራረሰ ነው፡፡
“ማነው?” ይላል የቡና ቤት ባለቤት፡፡
“እኔ ነኝ!” ይላል ቀንድ አውጣ፡፡
“ትንሽ መጠጣት ፈልጌ ነበር”
“መሸኮ! ከዚህ ወዲያ አላስተናግድም!”
“እረ በእግዚሃር አስተናግደኝ! ምንም ሄጄ እምዝናናበት ቦታ የለኝም፡፡ የት እንደምሄድም አላውቅም! እባክህ ተባበረኝ!”
“አያ ቀንዳውጣ! እየዘጋሁ ነው ስልህ ምንድን ነው ችግርህ? ትመለሳለህ ተመለስ አለበለዚያ ዋጋህን ታገኛለህ! ተግባባን?”
“ባለቡና ቤት፤ እኔ አንድ ነገር ሳልቀምስ ወደ መኝታዬ መሄድ አልችልም! ይገባሃል?”
“ቆይ እንግዲህ እንዲገባህ ምን ማድረግ እንደምችል አሳይሃለሁ!” እያለ የዘጋውን በር ይከፍትና ይወጣል፡፡
ቀንድ - አውጣው በሁኔታው ተደስቶና የበለጠውን ዕውነት አስረዳዋለሁ ብሎ ፍንድቅድቅ ብሏል፡፡
ሰውዬው ግን ንግግሩን ሁሉ አቋርጦ በንዴት ተወጥሮ ወደውጪ መጣና፤
“አንተ ማነኝ ብለህ ነው ይሄ ሁሉ ጉራ? ይሄ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀንዳውጣውም፤
“ጌታዬ፤ ውሃ ጠምቶኝ ነው ያስቸገርኩህ፡፡ እባክህ…” ብሎ ሳይጨርስ፣ ባለሆቴሉ ባለ በሌለ ኀይሉ በቲራ ጠረገው፡፡ ቀንድ አውጣው ሩቅ ከመሽቀንጠሩ የተነሳ፤ የት ሄዶ እንደወደቀ እንኳን ያየው የለም!!
ከአንድ ዓመት በኋላ ቀንድ አውጣው ወደዚያው ሆቴል መጣ፡፡ ዛሬም ሰዓቱ በጣም ረፍዷል፡፡ ያ ባለ ሆቴል በሩ ሲንኳኳ፤
“ማነው?” አለ፡፡
“እኔ ነኝ!”
“ማ?”
“እኔ ቀንድ አውጣ!”
“አንተ ዛሬም ልትለክፈኝ መጣህ?”
“አይ፤ ዛሬስ አንድ ጥያቄ ብቻ ኖሮኝ ነው የመጣሁት”
ባለሆቴሉ ወጣና፤
“ምንድን ነው የፈለከው?”
ቀንዳውጣውም፤
“አንዲት ጥያቄ ብቻ ናት ያለችኝ፡፡”
“እሺ ተናገር?”
“ባለፈው ዓመት አሽቀንጥረህ ከጣልከኝ ቦታ እዚህ ለመድረስ ተጉዤ ተጉዤ፤ ይሄው ዛሬ ደረስኩኝ፡፡ ለመሆኑ ለምን ነበር እንደዛ በቲራ የመታኸኝ?!”
*    *    *
በየትኛውም ሰዓት ያረፈደ ሰው፤ ቅጣቱ እንደተጠበቀ መሆኑን አንርሳ፡፡ ማንም በመሸ ሰዓት ረግጦ ሊያሽቀነጥረን እንደሚችልም እንገንዘብ፡፡
ማዝገማችን፣ መንቀርፈፋችንና መዘግየታችን በራሱ መልክና ጊዜ ወደኛው ፊቱን አዙሮ እንደቀንድ አውጣው ሊያስመታን መቻሉ አይቀሬ ነው፡፡ ለምን ሆነ? ብለን በዓመቱ መጠየቅ ቢያንስ መሳቂያ ከመሆን አያሳልፈንም፡፡ ሌሎች ውቴላቸውን ዘግተው ሳይቆልፉ በፊት ነቅቶ መምጣት ብልህነት ነው፡፡
የሀገራችን ስሞች አስገራሚ ናቸው፡፡ በወትሮ ማዕረጉ የሹም/የንብረት ባለቤት የምንለው፤ ስሙ የኃደራ ስም ይባላል፡፡ ባላገር፣ ወታደር፣ ባላባት፣ ስደተኛ፤ ባለቤት እንዲሉ፡፡ የሀገር ባለኃደራነት መሆኑ ነው፡፡
የማኅደር ስም የሚባል አለ ደግሞ፡፡ አደራችንን አንዘንጋ የሚል የማደሪያ ስም ነው፤ ቃሉ፡፡ በየጊዜው ቃል ስንገባም “ዕውን እፈጽመዋለሁ? እንበል፡፡ የመሬት፣ የቦታ ርስት ወዘተ ንብረት ባለቤትነት ዶሴ እንደማለት ነው፡፡ የሚገርመው የማህደርም፤ የባለኃደራም ሌብነት ነበር፡፡ የዱሮ ዘመን ባለቤትነት ከዛሬ ሊለይ ይችላል፡፡ እንደ እውነቱ ግን ሁሉም ከላይ እየታዘዘ ከመፈፀሙ አኳያ፤ የቋንቋ ነገር ካልሆነ በቀር  ሁሉም ስሙ “ሙስና” ነው፡፡
የተቀብዖ ስም እንዲል መጽሐፍ ሹመት ብቻውን ፍሬ አያፈራም! የተቀባንበት፣ የተሾምንበት፣ ኃላፊነት የተቀበልንበት ስም ያው የተቀብዖ ስም ነው፡፡ ታዲያ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋልን”፣ “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለሹመት”ን እንደበቀቀን እያቀነቀንን፤ እስከመቼ እንጓዛለን? ምንም ዓይነት ኮርስ ልውሰድ፣ ዋናው ቁም ነገር፣ “ሹመቱ ለአገር እንዳገለግል፣ ኃላፊነቴን እንድወጣ ነው” እንላለን? ወይስ በሹምነቱ ዘመን ያልበላ፣ እየበላ ያለና ወደፊትም የማይበላ ማን ሹም አለ? ከበይው የሚይቋደስ፣ ባለ አላባ፣ ባለ ኮሚሽንስ ማን አለ?
ሐዲድ ተሠራ ስንል ሲመነቀል፣ አገር ያደነቀው ምሁር አፈራን ስንል፤ “አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ” ሲለን፣ ውጪ አገር ወኪል አድርገን ስንልክ “አፍንጫችሁን ላሱ” ሲለን፤ ምን ዓይነት ተዓማኒነት ልናስተናገድ ነው?
“እያንዳንዱ አሣ አጥንት እንዳለሁ ሁሉ፤ እያንዳንዱ ሰው ስህተት አለው” ይላሉ አዋቂዎች፡፡ ሆኖም ይህን ብሂል መሠረት አድርገን ስንሳሳት፣ አውቀን ስንሳሳትና ለሁሉም ዋናው ሰበብ ማግኘት ነው ስንባል መክረማችን፤ አሳሳቢ ነው፡፡
“አንድ ‹ባሪያ› በምድር ላይ እየተጓዘ እስካለ ድረስ ያንተ ነፃ መሆን (ተዓምር) ፍፁም አልሆነም!” ይላሉ የፍልስፍና ሊቃውንት፡፡
ዕውነት ነው፡፡ የአስተሳሰብ ባርነት፣ የአመለካከት ባርነት፣ የጠባብነት ባርነት፣ የመላላት ባርነት፣ እኔን ከተከተልክ - ነፃ ነህ የመባል ባርነት፤ ዲሞክራሲን እንደፈለጉ በሚተረጉሙና በሚተገብሩ የፖለቲካ ባላባቶች መጠርነፍ ባርነት…ወዘተ ውስጥ መኮድኮድ እርግማን ነው፡፡ ስለሆነም እንዴት? ለምን? ብሎ መጠየቅ ታላቅ እርምጃ ነው!
“የመጨረሻው ከባድ የብረት በርም የሚከፈተው በትንሽ ቁልፍ ነው” (ቻርለስ ዲከንስ)
ቻርለስ ዲከንስ ትንሽ ነን ብለን ተስፋ አንቁረጥ፡፡ ችሎታና ዕውቀቱን ከያዝን የመጨረሻውን ከተምበሪ ልንከፍተው እንችላለን ሲል ነው፡፡ አንዱ የእኛ ፖለቲከኞች ችግር እራስን አሳንሶ ማየት የሚሆነው ለዚህ ነው!!
የሚከተለው አገርኛ ግጥም በልኩ ያስገነዝበናል፡፡
“ዓመት ነው?”
ዕድሜ ነው?
ስሜት ነው?
ተስፋ ነው መጪው ቀን?
ወይስ ኩራት እራት፣ ከውስጡ የቀረ፣ ትርጉም ይኖር ይሆን?”
ተስፈኝነት፣ አዎንታዊነት፣ ትዕግሥትና ጽናት ከሌሉ ለአገራችን ትግል አስተዋጽኦ አይዋጣልንም፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ፤
“ዓለም ነገ ልታልቅ ነው ቢሉኝም፣ ዛሬ ዛፍ መትከሌን አልተውም” ያለን ለዚህ ነው፡፡
በአንፃሩ ትላንትም፣ አሁንም፣ ያለውን ሁኔታ እደግፋለሁ፤ አንደኛ የልማት አርበኛ ነኝ፤ አንደኛ “ኮብል ስቶኒስት ነኝ!”፤ አንደኛ አገራዊ ምሁርና የሚዲያ ተቆርቋሪ፤ የፖለቲከኛ ተንታኝ ነኝ የሚል ቢበዛ፤ ቆም ብሎ “ዕውን ነውን?” ማለት ያባት ነው! “የሚስቅልህ ሰው ስለበዛ፣ ትክክል ነኝ ብለህ አታስብ!” የሚለው የእንግሊዞች አባባል፤ ፍሬ - ጉዳይ አለው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡


Read 7055 times