የውድድር ዘመኑ ሲጀመር በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተመረጡ ጨዋታዎች ለማስተላለፍ መታቀዱ በይፋ ቢነገርም ባልታወቀ ምክንያት ይህን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉም ግጥሚያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ሊኖራቸው የሚችለውን ትኩረት አደብዝዞታል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ የ3 ሳምንት ጨዋታዎች 17 ግጥሚያዎች ተደርገው 30 ጎሎች ከመረብ ያረፉ ሲሆን ሊጉ ባንድ ጨዋታ በአማካይ 1.76 ጎል የሚመዘገብበት ሆኗል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ቡና 3 ጨዋታዎች አድርጎ በሁለቱ አቻ ወጥቶ እና በአንዱ ተሸንፎ በ2 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት ከሳምንት በፊት በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ግጥሚያው ከሜዳው ውጭ በድሬዳዋ ከነማ አድርጎ 1ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ያለምንም ነጥብ 13ኛ ላይ ነው፡፡
በሌላ በኩል በነገው በትልቁ የኢትዮጵያ ክለቦች ደርቢ የሚጋጠሙት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር የቅድመ ማጣርያ ግጥሚያዎቻቸውን በኮሞሮስ ደሴት እና በጋቦን ከሜዳቸው ውጪ በጥር ወር መጨረሻ ላይ ይጀምራሉ፡፡ በ16ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነቱ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ቡና በቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያውን ከሜዳው ውጭ ከኮሞሮሱ ክለብ ኮየን ኖርድ ጋር ይጀምራል፡፡ በ9ኛው የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮፕያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ግጥሚያው የሚገናኘው ከጋቦኑ ክለብ ኤኤስ ማንጋስፖርት ጋር ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በአዲስ አበባ ስታድዬም በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ያደርጋሉ፡፡
በቅድመ ማጣርያው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚወዳደረው ኢትዮጵያ ቡና የኮሞሮሱን ክለብ ኮይን ኖርድ ጥሎ ካለፈ በቀጣይ ምእራፍ ከግብፁ ክለብ አልሃሊ ጋር ይገናኛል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፑ የሚወዳደረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የጋቦኑን ክለብ ማንጋስፖርትን ጥሎ ማለፍ ከቻለ በቀጣይ ምእራፍ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር ይፋጠጣል፡፡በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ የተሳትፎ ታሪክ ካላቸው የኢትዮጵያ ክለቦች ቅ/ጊዮርጊስ፣ መብራት ሀይልና ሀዋሳ ከነማ ፤ ደደቢት እና ኢትዮፕያ ቡና ተጠቃሽ ሲሆኑ ከምድብ ማጣርያ በፊት ያሉትን የ2 ዙር የማጣርያ ምእራፎችን ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ዘንድሮ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚወክለው ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ በአራት አህጉራዊ የክለብ ውድድሮች የመሳተፍ እድል አግኝቷል፡፡ ክለቡ በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ከ11 ዓመት በፊት እስከ ሁለተኛ ዙር መድረሱ የመጀመርያው ስኬት ከመሆኑም በላይ ለአገሪቱ ክለቦች ትልቁ የውጤት ደረጃ ነው፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት በኢንተርናሽናል ውድድር በመሳተፍ ግንባር ቀደም ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው ከ37 አመታት በፊት ነበር፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የነበረው ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያው የተደለደለው ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር እንደነበር ሲታወስ ጥሎ ማለፍ እንዳዳገተው ይታወሳል፡፡፡