Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 December 2011 11:38

ማን.ሲቲ ከአርሰናል ለዋንጫ ፉክክሩ ትርጉም ይኖረዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ማን. ሲቲ ነገ በሜዳው ኢትሃድ ስታድዬም አርሰናልን የሚገጥመው  አሸንፎ መሪነቱን ለመጠበቅ ሲሆን አርሰናል ከዋንጫ ተፎካካሪነት ለመግባት በሚያስችለው ውጤት ላይ እንደሚያነጣጥር ተገለፀ፡፡ ከሻምፒዮንስ ሊግ ከተባረረ በኋላ በፕሪሚዬር ሊግ ያልተሸነፈበት ብቃቱ ባለፈው ሰኞ በቼልሲ የተደፈረበት ማን. ሲቲ  በያዘው አቋም የበላይነት እንደሚያገኝ ግምት አግኝቷል፡፡ አርሰናል ደግሞ  ባለፉት 2 ወራት በጥሩ ብቃት በማገገም ላይ ከመሆኑ አንፃር በ8 ተከታታይ ጨዋታዎች ባለመሸነፉ በነገው ጨዋታ ለሻምፒዮነነት ያለውን የመፎካከር እድል ለማስፋት ከባድ ተቀናቃኝ ይሆናል ተብሏል፡፡

ባለፈው ሰኞ ቼልሲ 2ለ1 በሆነ ውጤት ማን ሲቲን ማሸነፉ በሻምፒዮናነት ፉክክሩ ሌሎች ክለቦች ያላቸውን ተስፋ አለምልሞታል፡፡ ከ15 ሳምንታት ጨዋታዎች በኋላ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጀመርያ ስፍራዎች ያሉ አራት ክለቦች ከመሪው በ9 ነጥብ ርቀት መገኘታቸው ለትንቅንቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

ማንችስተር ሲቲ ሊጉን የሚመራው ተከታዩን ማን ዩናይትድ በ2 ነጥብ በመብለጥ ሲሆን ነገ በኢትሃድ ስታድዬም ሽንፈት ከገጠመው አንደኛነቱን ሊነጠቅ ይችላል፡፡ ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ 6 የሊግ ጨዋታዎች 5ቱን ያሸነፈው ማን ዩናይትድ፤ ከሻምፒዮንስ ሊግ ከተባረረ በኋላ በሊጉ ዎልቨር ሃምፕተንን 4ለ1 በመርታት አገግሟል፡፡ ማን.ዩናይትድ  ነገ ከኪውፒአር ሬንጀርስ ጋር ሲጫወት ሙሉ ነጥብ ከያዘ የሊጉን መሪነት የመረከብ ሰፊ እድል ይዟል፡፡በፕሪሚዬር ሊጉ እስከ 15ኛ ሳምንት በተደረጉት 149 ጨዋታዎች 441 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን ሊጉ ባንድ ጨዋታ በአማካይ 2.96 ጎሎች የሚቆጠሩበት ሆኗል፡፡ ማንችስተር ሲቲ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በ12 ድል አድርጎ በ2 አቻ ወጥቶ እና በ1 ተሸንፎ በ38 ነጥብና በ34 የግብ ክፍያ 1ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን፤ አርሰናል በ15 ጨዋታዎች በ9 ድል አድርጎ በ2 አቻ ወጥቶ እና በ4 ተሸንፎ በ29 ነጥብና በ8 የግብ ክፍያ 5ኛ ደረጃ ላይ  ነው፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ቫንፒርሲ በ15 ጎሎች ሲመራ የሲቲው አጉዌሮ ከኒውካስትሉ ዴምባ ባ እና ከማን ዩናይትዱ ሩኒ ጋር በእኩል 11 ግቦች ይከተላሉ፡፡ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው ያለፉት 6 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች እኩል 3 ጊዜ ሲሸናነፉ ሲቲ ከ2 አመት በፊት በሜዳው በአርሰናል 4ለ2 ከተሸነፈበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ጨዋታ ግብ አላስቆጠረም፡፡ አርሰናል ከማን ሲቲ ጋር በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ 5 ጨዋታዎች በአራቱ ግብ አላስቆጠረም፡፡ ሲቲም  ከአርሰናል ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ 5 የሊግ ጨዋታዎች በአራቱ ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻለም ፡፡ስለሆነም በነገው ጨዋታ ለሁለቱ ክለቦች ግብ ያድናሉ በሚል ተስፋ የተጣለባቸውና በሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት የተያያዙት ሰርጂዮ አጉዌሮና ሮቢን ቫን ፒርሲ ይህን የግብ ድርቅ በማብቃት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው እየተገለፀ ነው፡፡ሮቢን ቫን ፒርሲ በ2011 ባደረጋቸው 32 የፕርሚዬር ሊግ ጨዋታዎች 33 ጎሎች ለአርሰናል በማስመዝገቡ በ1995 እኤአ በተመሳሳይ የጨዋታ ብዛት 36 እንዲሁም በ2004 እኤአ ቲዬሪ ሆንሪ 34  ጎሎች ካስመዘገቡበት ታሪክ ጋር አቀራርቦታል፡፡ ቫን ፒሪሲ የፕሪሚዬር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ሲሆን ከሜዳ ውጪ ባደረጋቸው በመጨረሻዎቹ 16 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች 18 ጎሎች በማስቆጠሩ ዛሬ ግብ ያገባል ተብሎ የሚጠበቀው በዚህ ብቃቱ ነው፡፡ባለፈው የውድድር ዘመን ሁለቱን ክለቦች ባገናኙ 2 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ሶስት የቀይ ካርድ ቅጣቶች ማጋጠማቸው የነገውን ትንቅንቅ አንድ ገፅታ የሚያሳይ ሲሆን ከኢማኑዌል አደባዬርና ከኮሎ ቱሬ በኋላ በውድድር ዘመኑ መግቢያ ናስሪ እና ክሊሼ ሲቲን መቀላቀላቸው እንዲሁም ቫን ፒርሲን በተመሳሳይ ለማስኮብለል በተያዘው አቅጣጫ በመካከላቸው ያለውን እሰጥ አገባ አባብሶታል፡፡

ማን ሲቲ እና አርሰናል በፉክክር ደረጃቸው እኩል ግምት ቢኖራቸው በፋይናንስ አቅማቸውና ባላቸው የአስተዳደር ጤናማነት እጅግ የተራራቁ ናቸው፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት በሼክ መንሱር ባለቤትነት ከተያዘ በኋላ በ800 ሚሊዮን ፓውንድ ኢንቨስትመንት የተደራጀው ማን ሲቲ ዘንድሮ በፕሪሚዬር ሊግ ሪኮርድ ሆኖ የተመዘገበ 197 ሚሊዮን ፓውንድ ኪሳራ ቢያስመዘግብም በሊጉ ዋንጫውን ለመውሰድ ባለው ግምት ቀዳሚውን ግምት እንደወሰደ ነው፡፡ ሲቲ ከ3 ዓመት በፊት ለተጨዋቾች ደሞዝ በዓመት 54 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ የነበረው ሲሆን ዘንድሮ ይሄ ወጪው 174 ሚሊዮን ፓውንድ በመድረስ በእንግሊዝ የምንግዜም ከፍተኛው የደሞዝ ከፋይ ክለብ አድርጎታል፡፡ ምንም እንኳን የማን ሲቲ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ጤናማ ባይመስልም ዘንድሮ ክለቡ በገቢው ላይ 22በመቶ እድገት ተመዝግቦ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ 150 ሚሊዮን ፓውንድ ዓመታዊ ገቢ ማስገባቱ ክለቡ ከሜዳ ውጤት ጋር በሚቀጥሉት ሁለት የውድድር ዘመናት ከገባበት የኪሳራ አዙሪት ሊወጣ እንደሚችል ተስፋ አሳድሯል፡፡

በዴሌዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ ጥናት መሰረት በአውሮፓ እግር ኳስ የገቢ ሊግ ማን ሲቲ በ125 ሚሊዮን ፓውንድ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን የነገ ተጋጣሚው አርሰናል በ222 ሚሊዮን ፓውንድ ዓመታዊ ገቢው 5ኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ማንሲቲ በተጨዋቾች ዝውውር ከወጪ ቀሪ ያወጣው 440 ሚሊዮን ፓውንድ  ከ5 የእንግሊዝ ሃያላን ክለቦች ወጪም የሚልቅ ሲሆን አርሰናል በተመሳሳይ ቡድኑን ለማጠናከር በውድድር ዘመኑ ያስመዘገበው ወጪ 29 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነው፡፡በ2011 የዴሊዮቴ የአውሮፓ ክለቦች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ  በተለያዩ የገቢ ምንጮች አርሰናል ከማንሲቲ የተሻሉ አሃዞችን ገቢ አስመዝግቧል፡፡ ማን ሲቲ በውድድር ዘመኑ ከአርሰናል የተሻለ ገቢ ያገኘው ከተለያዩ የንግድና የስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴዎቹ ብቻ ነው፡፡ በቲቪ ስርጭት መብት  አርሰናል 86.5 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያገኝ ማን ሲቲ 66 ሚሊዮን ፓውንድ፤ በሜዳ ገቢ  አርሰናል 93.9 ሚሊዮን ፓውንድ  ማን ሲቲ 29.8 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም በተለያዩ የንግድ  እንቅስቃሴዎች ማን ሲቲ 57 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስገባ የአርሰናል ገቢ 44 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ሰንዴይ ታይምስ በ2011 የእንግሊዝ አሰልጣኞችን የሃብት ደረጃ ሲያወጣ የማን ሲቲው ሮበርቶ ማንቺኒ 16 ሚሊዮን ሃብትና 6 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ደሞዝ እንዳላቸው ሲያሳውቅ በሃብታቸው 19 ሚሊዮን ፓውንድ አስመዝግበው ብልጫ ያላቸው የአርሰናሉ ቬንገር በ4.8 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ደሞዝ ከማንቺኒ ያነሰ ክፍያ እንዳላቸው አመልክቷል፡፡

 

 

Read 7007 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 11:40