Saturday, 14 June 2014 12:34

በህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃትና መገለል ..ውጤት...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

ሕጻናትን በሚመለከት ባለሙያዎች ከሚያስተላልፉዋቸው መልእክቶች መካከል በአካልና በወሲብ ጥቃት የደረሰባቸውን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ በዚህ እትም Melinda Smith, M.A., and Jeanne Segal, Ph.D.  በውጭው አቆጣጠር February 2014 ለንባብ ያበቁትን እኛም ለአንባቢዎች እነሆ ብለናል፡፡
በመጀመሪያ የህጻናት መጠቃትና መገለል ...መኖሩን ማመን መቀበል እና ሕጻናቱን ከጥቃት መከላከል እንዲሁም ተፈጽሞ ሲገኝም ለሚመለከተው ሪፖርት ማድረግን ሁሉም ሰው እንደመርህ ሊቀበለው ግድ ይላል፡፡ በህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት እንደበለዘ የሰውነት ክፍል ወይንም እንደተሰበረ አጥንት  ይቆጠራል፡፡ በአካል ላይ የሚደርስ ጥቃት በግልጽ የሚታይ ሲሆን በሞራል ላይ የሚደርሰው ጥቃት ግን እስከመቼም የማይረሳ የአእምሮ ጠባሳ ይጥላል፡፡
በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ምን እንደሆነና የሚያስከትለውን ጉዳት ማወቅ ከተቻለ ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ እና የህጻናቱን ደህንነት ለመጠበቅ መንገድ ይከፍታል፡፡ ነገር ግን የሕጻናቱን ፍላጎት በቸልተኝት ማለፍ፣ ክትትል እንዳይደረግላቸው ማድረግ፣ አደገኛ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ አለመጠንቀቅ፣ ወይንም ልጆች ጠቀሜታ እንደሌላቸው አድርጎ መገመት በሕጻናት ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች የሚመደቡ ናቸው፡፡
ሕጻናት በሚደርስባቸው ጥቃት ሳቢያ ስሜታቸው ይጎዳል
ጤናማ የሆነ የእርስ በእርስ ግንኙነት ይጎድላቸዋል
በትምህርት ቤት በመኖሪያ ቤት እንዲሁም በስራ ቦታ ተግባራትን ማከናወን ያስቸግራቸዋል፡፡
እንደአፈጻጸሙ ሁኔታና መጠን ውጤቱ ቢለያይም ሁሉም ግን ጎጂዎች ናቸው፡፡
ሕጻናት ጥቃት ሲደርስባቸው፡-
1/ እምነት ማጣትና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችግር ይገጥማቸዋል፡፡
ሕጻናቱ የጥቃት ችግር ሲደርስባቸው በመጀመሪያ አለመግባባት የሚፈጥሩት በቅርብ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ወይንም ከወላጆቻቸው ጋር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ እና በልጆቹ የወደፊት ሕይወት ላይ የበለጠ ችግር ያስከትላል ተብሎ ይታመናል፡፡
2/ ጥቅም የሌላቸው ወይም ለዘለቄታው ጉዳተኛ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡
ሕጻናቱ በተደጋጋሚ ስለደረሰባቸው ጉዳት በበጎም ይሁን በመጥፎ ጎኑ የሚነገራቸው ከሆነ ስሜታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ አዋቂዎች በልጆቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለመነጋገር ከፈለጉ ልጆቹን መልሶ ጥፋተኛ በሚያደርግ መንገድ ሳይሆን ለደረሰው ጉዳት ፈጻሚው ተጠያቂ እንደሚሆንና እነርሱም በወደፊቱ ሕይወታቸው ላይ ምንም ጠባሳ ሊጥልባቸው እንደማይገባ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች በተፈጠረው ችግር ሀፍረት እና መገለል እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
3/ የስሜት መለዋወጥ ያጋጥማቸዋል፡፡
ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች ስሜታቸውን በትክክለኛው መንገድ ማስረዳት ይቸገራሉ፡፡ ከጥቃቱ በሁዋላ እራሳቸውን ለመግለጽ በጣም ስለሚቸገሩ ባልተጠበቀ እና በተሳሳተ ወይንም እነርሱን ሊገልጽ በማይችል መንገድ ሲገልጡት ይታያሉ፡፡ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ መጨነቅ መደበር ወይንም ቁጣ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ያንን በስቃይ የተሞላ ስሜታቸውን ያስታገሱ ስለሚመስላቸውም መጠጥና እጽ ወደመውሰዱ ያዘነብላሉ፡፡

ወሲባው ጥቃት የደረሰባቸውን ሕጻናት ለመለየት አያስቸግርም፡፡
ለመራድ ወይንም ለመቀመጥ ይቸገራሉ
ወሲብን በሚመለከት በእድሜያቸው የማይመጥናቸው እውቀት እና ስሜት ያሳያሉ፡፡
ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በተለይም አንድን ሰው እንዳያገኙት ሲያስወግዱት ይስተዋላል፡፡
በሰዎች ፊት ልብሳቸውን መቀየር አይፈልጉም ወይንም ያፍራሉ፡፡
በ14 አመት እድሜያቸው በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፍ በሽታ ወይንም እርግዝና ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡
ቤታቸውን ጥለው ይወጣሉ፡፡
ልጆችን ከጉዳት ለመከላከል ወላጆች እንዲሁም ሌላው ሊፈጽማቸው የሚገቡ ነገሮች አለ፡፡ ባለትዳሮች ብዙውን ጊዜ ሊገልጹዋቸው የማይችሉዋቸው ልዩነቶች ይገጥሙዋቸዋል፡፡
ለምሳሌ፡- ከትዳር ጉዋደኛ ጋር ጭንቀት የተሞላበት ግንኙነት፡ ብዙ ስራ መስራትና ለመዝናናት ጊዜ እስከማጣት መድረስ፡ የኢኮኖሚ ውስንነት፡ ሱስ አስያዥ እጾችን መጠቀም፡
በመሳሰሉ ምክንያቶች በወላጆች መካከል ብዙውን ጊዜ አለመመቸት የማይገናኙ ወይንም የተዘበራረቁ ስሜቶች ይስተዋላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆቻቸው ምን አይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው ለመከታተል የሚያስችላቸውን ትኩረት አይሰጡም፡፡ ለማንኛውም ተከታዮቹ ነጥቦች ለልጆች ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት የሚያስችል መንደርደሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡  
የመጀመሪያው ጥሩ ምሳሌ መሆን ነው፡፡
ቤተሰቦችን ማክበር / በትህትና ማነጋገርን ለልጆች ማስለመድ በጣም ጠቀሜታ ያለው ባህርይ ነው፡፡ ልጆች ጥፋት ቢያጠፉ እንኩዋን ምን እንዳደረጉ ማስረዳት እና ያንን ነገር ሌላ ሰው እንደማይወደው በትህትና መግለጽ ጠቃሚ ነው፡፡ የቁጣ መንፈስ ልጆችንም ተቆጪ ያደርጋቸዋልና ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ወላጅ ጥፋት ፈጽሞ ከሆነም ልጆችን ይቅርታ መጠየቅ ትክክለኛው ነገር ነው፡፡  በተጨማሪም ምንጊዜም እወድሀለሁ/እወድሻለሁ ማለት በጎ ነው፡፡ በጎ ባህርይን ለልጆች መሸለም ይገባል፡፡
ወላጆች ከሌሎች ወላጆች ጋር ቅርርብ መፍጠር ወይንም ጉዋደኛ መሆን ሌላው ነጥብ ነው፡፡
ወላጅ አንድ መገንዘብ ያለበት ነገር አለ፡፡ ይኼውም... ነገሮችን ለውይይት ማቅረብ ወይንም ያለውን የቁጣ ስሜት ለሌሎች መግለጽ የታመቀውን ችግር እንደሚያቃልል ነው፡፡ ወይንም በዛ ምክንያት ወደሌላ ችግር ይቀየር የነበረውን ስሜት ያስወግዳል፡፡  ልጆች ወላጆቻቸው በደስታ ተሞልተው ሲያዩ እነርሱ ደግሞ በበለጠ ሁኔታ በጣም ይደሰታሉ፡፡ ከወላጆች ጋር ለተለያዩ እስፖርታዊ ጨዋታዎች መገባበዝ እና ይህንንም ልጆች እንዲያዩት እንዲሳተፉበትም ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እስፖርታዊ ጨዋታ ጭንቀትን ያስወግዳል፡፡  
ልጆችን ይዞ ከጎረቤት ወይንም ከጉዋደኛ ከቅርብ ዘመድ ጋር በፕሮግራም መገናኛት
ልጆች አስፈላጊ እና በቂ የሆነ የመዝናኛ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ልጆችን ማመስገንና ማበረታታትን መልመድ የወላጆች አንዱ ተግባር መሆን አለበት፡፡
ትንሽ የምትመስል አባባል ለልጆች ግን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ አለበለዚያ ልጆች ሊጎዱና ጉዳቱም እስከእድሜ ፍጻሜ ድረስ ሊቆይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ለልጆች ቅን መሆን ይገባል፡፡ ለልጆችህ በእነእርሱ እንደምትኮራ ግለጽላቸው፡፡ ፈገግታ ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊህ እንደሆነች/ነ መግለጽ... ታስፈልጊኛለሽ/ታስፈልገኛለህ... ለእኔ ትልቅ ዋጋ አለህ/ማለት ተገቢ ነው ማለት ይጠቅማል፡፡
ከትምህርት በሁዋላ በቤት ውስጥ የእረፍት ጊዜን ማመቻቸት ይጠቅማል፡፡

የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እከሌ ነው በማለት ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ልጆች በጣም ይጠቀማሉ፡፡ ወላጆችም ቀላል የማይባል ጥቅም አላቸው፡፡ ልጆች እንዲደሰቱ በውጭው አጣራር ቤቢ ሻወር የሚባለውን ፕሮግራም ለልጆች መፍጠር ይጠቅማል፡፡ በዚህም ልጆቹ ጉዋደኞቻቸውን ወይንም በአካባቢ የሚያውቁዋቸውን ልጆች ይጋብዛሉ፡፡ በዚህም ስጦታ ይለዋወጣሉ፡፡  
መድረኮች ማመቻቸት ጠቃሚ ነው፡፡ ምን አይነት ልጅ ለጥቃት ተጋላጭ ነው የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በልጆች ላይ የሚደርስ ጥቃት በዘር፣ በጎሳ፣ በባህል ወይንም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ሳይለይ በአካል እና በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ይበልጡኑ በድህነት ላይ በሚኖሩት እንደሚብስ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይበልጡኑ የሚጎዱ ልጆች ነገሮችን ለመረዳት የሚቸገሩ፣ የአእምሮ ዝግመት ያለባቸው፣ የእድገት ውስኑነት ያለባቸው፣ የተገለሉ ወይንም የማይፈለጉ ልጆች  ሲሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ ሲሉ አስቸጋሪ ነገሮች ውስጥ የሚገቡ፣ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ወይንም የአካል ጉዳተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ማጠቃለያ የሚሆነው... የተጎዱ ልጆች መኖራቸው ሲታወቅ ወዲያውኑ ለሚመለከተው ክፍል ሪፖርት ማድረግ የሚለው ነው፡፡ 

Read 2037 times