Saturday, 14 June 2014 11:59

የሳይንስ ምርምር ውጤቶች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

የማንነት ባህርይ (ፐርሰናሊቲ) ከዘር ይወረሳል?

      አዎ! ከፍተኛው የማንነት ልዩነቶች በአብዛኛው ከዘር የሚወረሱ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ልጅ በመልክ ብቻ ሳይሆን በዝንባሌ፣ በፍላጎት፣ በባህርይ፣ በስሜት አገላለጽ፣ በማኅበራዊ ተሳትፎ … አጠቃላይ ሰብዕናቸው ከወላጆቻቸው ጋር ሲመሳሰል ፣ “ቁርጥ የእናቱ ልጅ፣ ቁርጥ የአባቱ ልጅ” የሚባለው ያለምክንያት አይደለም-የማንነት ባህርይ ከዘር ሐረግ ስለሚወረስ ነው፡፡
ለዚህ እውነት ጥሩ ማሳያ የሚሆኑን ከአንድ እናትና አባት የተፀነሱ (ወንድ ወይም ሴት) ፆታ ያላቸው ተመሳሳይ (አይደንቲካል) ነገር ግን ተነጣጥለውና ተራርቀው፣ በተለያዩ ቤተሰቦች ውስጥ ባደጉ መንትዮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ መንትዮች ላይ የታየው የባህርይ ውርስ፣ የአመራር (ሊደርሺፕ) ብቃት፣ ባህላዊነት (ትራዲሽናሊዝም)፣ ለሥልጣን ተገዢነት (ኦቢዲያንስ ኦቶሪቲ) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ባህላዊ እሴቶችንና ሕግ አክባሪነት ከዘር መውረስ ያልተለመደ ስለሆነ ወደፊት በጥናት የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ሌሎች ከወላጅ አባትና እናት የሚወሰዱ ባዮሎጂያዊ መሠረት ያላቸው ውርሶች፣ ሰሬቶኒን፣ ዶፓሚንና ኖራአድሬናሊንን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ ያሉ የነርቭ አስተላላፊዎች ስለሚገናኙ ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ ሌሎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ከዘር የሚወረሱ ባህርያት በኑሮ ደስተኛ መሆን፣ የመለያየት ስሜት መመሳሰል፣ ለድብርት እጅ ያለመስጠት፣ አንድ ነገር ኪሳራ (ሪስክ) ይኖረዋል ብሎ ያለመጨነቅ… ናቸው፡፡
ይህ ማለት ግን እነዚህ ከዘር የሚወረሱ ባህርያት በምንም ዓይነት መንገድ አይለወጡም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በተፈጥሮው ፈሪ የሆነ ሰው ድፍረትን ሊማር ይችላል፤ ኪሳራ የማይፈራ ሰው ብልጥ ሊሆን፣ ድብርት ሲሰማን ሰውነታችን ምን እንደሚል ማወቅ ሕይወታችንን በምቾት እንድንመራ ሊረዳን ይችላል፡፡ ነገር ግን ራሳችንን ልንሆን ወደማንችልበት ሌላ ሰው በፍፁም መቀየር አንችልም፡፡
29.6 ካራት አልማዝ  
ካራት እጅግ በጣም የከበሩ ማዕድናት መለኪያ ነው፡፡ ወርቅ ምን ያህል ንፁህ እንደሆነ የሚለካው በካራት ነው፡፡ ይህ ወርቅ 24 ካራት ነው ሲባል፣ ሌላ ምንም ዓይነት ድብልቅ ማዕድን የሌለው መቶ ፐርሰንት ንፁህ ወርቅ ነው ማለት ነው፡፡
አንድ ካራት 200 ኪ.ግ ይመዝናል፡፡ በቅርቡ ከደቡብ አፍሪካ ኩሊናን የማዕድን ጉድጓድ የተገኘው ሰማያዊ አልማዝ ክብደት እጅግ የሚገርምና የሚደንቅ ነው፡፡ የዚህ ልዩና አስገራሚ ሰማያዊ አልማዝ ክብደት 29.6 ካራት ነው፡፡
የባንክ ካርድ ማንበቢያ መሳሪያ
የባንክ ካርድ ማንበቢያ መሳሪያ አሰራር፣ ከቴፕሬከርደር ጭንቅላት አሰራር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ከማግኔት የተሰራውና በፕላስተር የተሸፈነው ካርድ በማንበቢያው መሳሪያ ውስጥ ሲያልፍ፣ ካርዱ የያዘው መረጃ ወደ አንባቢው መሳሪያ ይተላለፋል፡፡ መሳሪያው የአንድን ሰው ምስጢራዊ ቁጥር (ፒንኮድ) የሚያነብ ከሆነ፣ በካርዱ ላይ በተሸፈኑት ቺፕሶች ላይ የኤሌክትሪክ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
በዚህ ጊዜ እንደማግኔታዊ የቴፕ ክር፣ የደንበኛው የፒን ኮድ በመሳሪያው ላይ ይታተማል፡፡ መሳሪያው ላይ የታተመው ምስጢራዊ ኮድ ትክክለኛ ከሆነ፣ ካርዱ፣ የተጠየቀው ክፍያ እንዲፈፀም ያዛል፡፡
የሙዚቃ ችሎታ ወይም የዳንስ ጥበብ በዘር ይወረሳል?
አንዳንድ ሁኔታ ለእንዲህ ዓይነት ችሎታ መፈጠር ሚና የሚጫወቱ ጂኖች ብቻና የጂኖች ውህደት ይኖራል እንጂ “የሙዚቃ ጂን” ወይም “የዳንስ ጥበብ ጂን” የሚባል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የሙዚቃ ወይም የዳንስ ጥበብ ባህርይ (ጂን) በቤተሰብ ሊወረስ ይችላል፡፡ ከቤተሰብ የሚወረሰው የሙዚቃ ወይም የዳንስ ጥበብ 50 ፐርሰንት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ያለውን ችሎታ ግማሹን ብቻ ነው ከወላጆቹ የዘር ሐረግ (ጄኔቲክ) የሚያገኘው፡፡ ግማሹ ችሎታ የራሱ ነው፡፡
ለዚህ ሐሳብ ማጠናከሪያ፣ ከውጪ የማይክል ጃክሰን ወንድሞችና እህት (ጃክሰን 5)፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ የብርቱካን ዱባለን ቤተሰቦች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ በጨቅላነታቸው ለማደጎ (ጉዲፈቻ) ተሰጥተው ሙዚቀኛ የሆኑ ሰዎች ታሪክ ሲጠና፣ ወላጆቻቸው ሙዚቀኞች እንደነበሩ የታወቀው በቅርቡ ነው፡፡
በርካታ ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩባት ዋና ከተማ
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እጅግ በርካታ ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩባት ከተማ የባንግላዴሿ ዋና ከተማ ዳካ ናት፡፡ በእያንዳንዱ ስኩዌር ሜትር (አንድ ኪ.ሜትር በአንድ ኪ.ሜትር በሆነ ቦታ) 44,500 ሰዎች ይኖራሉ፡፡
ወፎች በሌሎች ፕላኔቶች መብረር ይችላሉ?
በሌሎች ፕላኔቶች ላይ ወፎች ስለመኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ካሉም፣ ምድር ላይ ካሉት ጋር በጣም ላይመሳሰሉ ይችላሉ፡፡
ይኖራሉ ብለን ብንገምት፣ የፊዚክስ ሕግ በምድር ላይም ሆነ በሌሎች ፕላኔቶች ላይ ተመሳሳይ ስለሆነ የወፎቹ ክብደት ከመጠን ያለፈ ካልሆነና ከባቢ አየሩ በጣም ስስ ካልሆነ በስተቀር የማይበሩበት ምክንያት አይኖርም፡፡
ግራኝ ነዎት ወይስ ቀኝ?
በአንዳንድ ስፖርቶች ግራኝ ተጫዋቾች፣ በቀኝ እጅ ከሚቀናቸው ስፖርተኞች ጋር ሲነፃፀሩ፣ በብዙ ፐርሰንት ይበልጣሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በቀኝ እጅ መጫወት የሚቀናቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ ከግራኝ ተጫዋቾች ጋር ልምድድ ስለማያደርጉ ነው እንጂ ግራኞች በልጠው አይደለም ተብሎ ይታሰባል፡፡
በሌሎች ዝርያዎች ግራኝና ቀኝ የሚባል ነገር ይኖር ይሆን?
አብዛኞቹ አከርካሪና (Vertebrates) በደንብ የደረጀ አንጎል ያላቸው እንስሳት በሁለት ወገን ወይም ምዕራፍ (ቀኝና ግራ) የተከፈለ አንጎል ነው ያላቸው። የእያንዳንዱ ክፍል ተግባር፣ የተቃራኒውን ክፍል እንቅስቃሴ (ሞተር ፋንክሽን) መቆጣጠር ነው፡፡
አሁን ይህን ጋዜጣ እያነበቡ ያሉት “በቀኝ አንጎል” ወይም “በግራ አንጎል” ነው የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በአንጎል ውስጥ በርካታ ተግባራት የሚከናወኑት በአንደኛው የአንጎል ክፍል ወይም በሌላኛው ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድን ነገር በቀኝ ወይም በግራ እጅ የመሥራት ፍላጎት፣ የአንጎል ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው እጅ ቅድሚያ የመስጠት (Lateralization) ጉዳይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ለምሳሌ፣ “ለንግግር፣ የቀኝ ክፍሌን፣ ለመራመድ ደግሞ የግራ ክፍሌን ልጠቀም” ብሎ መወሰን ሳይሆን በዘፈቀደ ለአንደኛው ክፍል ቅድሚ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡
የሰው ዘር ብቻ አይደለም የዚህ ዓይነት አንጎል ክፍፍል ያለው፡፡ ስለዚህ እንስሳት ግራ ወይም ቀኝ እጃቸውን ለመጠቀም ቢመርጡ አያስገርምም። በርካታ የዓሳ፣ የወፍ፣ አዞ፣ ዔሊ፣ እንቁራሪት… የመሳሰሉ ዝርያዎች ቀኝ ዓይናቸውን የመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት፤ ቺምፓንዚዎችና ጎሬላዎች፣ ልክ እንደ እኛው ቀኝ እጃቸውን የመጠቀም ዝንባሌ እንዳላቸው አመልክቷል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ፣ ትልቅ ቀይ ቡናማ ፀጉር ያላቸው፣ ጭራ አልባና ባለ ረዥም ጠንካራ እጅ ኦራንጉተንስ (Orangutans) የተባሉ ጦጣዎች ግራኞች ናቸው፡፡ ይሁንና፣ ይህ ጥናት የተካሄደው እንስሳት ማቆያ ዙ (zoo) ውስጥ ባሉ እንስሳት ላይ ስለሆነ፣ ሳይንቲስቶች በሁለት ጎራ ተከፍለው “ይህ ግኝት ጫካም ውስጥ ባሉት እንስሳት ላይ ይሰራል፣ አይሰራም” በሚለው ጉዳይ ላይ ክርክር ይዘዋል፡፡
እንደ ሰው፣ ጦጣና ዝንጀሮ ከፍተኛ የአንጎል የዕድገት ደረጃ የሌላቸው ጡት አጥቢ እንስሳትም (non primates) በቀኝ ወይም በግራ እጅ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ሴት ውሾችና ድመቶች የቀኝ እጃቸውን መዳፍ መጠቀም ሲመርጡ፣ ወንዶቹ ግን ግራኞች ናቸው፡፡ ሆኖም  በሰው ልጅ ላይ የምናየውን አጠቃላይ ባህርይ በየትኛውም ፍጡር ላይ አናይም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይህ ሁኔታ ሰዎች ለቋንቋ ከሚያስፈልጋቸው ረቂቅ ክህሎት (Fine motor skill) የመነጨ ነው ብለው ያስባሉ፡፡
ምንጭ፡- (BBC Knowledge and Science Uncovered June 2014)

Read 4155 times