Print this page
Saturday, 14 June 2014 11:48

ዕባብ ያፍዝ-ያደንግዝ ያደረገባት ወፍ ክንፍ እንዳላት ትረሳለች (የአፈ-ታሪክ ወግ)

Written by 
Rate this item
(6 votes)

         “ሉሲ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” የሚለው መፅሀፍ ላይ የሚከተለው ታሪክ ይገኛል፡፡
በድሮ ዘመን በጣም ደስተኛ የሆነ ሰው ከሚወዳት ሚስቱና ከአራት ወንዶች ልጆቹ ጋር ይኖር ነበር። የአንጋፋው ልጅ ስም ጥልቅ ዓይን ይባላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቆቁ ተባለ፡፡ ሶስተኛው ልጅ ጡንቸኛው የሚል ስም ተሰጠው፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጅ ህፃን ስለነበር ስም አልተሰጠውም፡፡
አንድ ቀን በማለዳ እናታቸውና ልጆቹ ከመኝታቸው ሲነሱ አባታቸውን ከቤት አጡት፡፡ በሚቀጥለው ምሽትም ሳይመለስ ቀረ፡፡ በማግስቱም የአባታቸው ዱካ ጠፋ፡፡ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር ብዙ ተወያዩ፡፡ ወዴት እንደሄደ ማንም የሚያውቅ የለም፡፡
እናታቸው ራሷን በሁለት እጆቿ ደግፋ ለቅሶና ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡ ጥልቅ ዓይን “ምናልባት አጎታችንን ሊጠይቅ ሄዶ ይሆናል፡፡” አለ፡፡ “ድግስ ተጠርቶ ወደ ጎረቤት ሄዶ ይሆናል” ሲል ቆቁ የራሱን ግምት ሰጠ፡፡ “ምናልባትም ወደ ተራራ ወጥቶ ነፋስ እየተቀበለ ይሆናል” በማለት ጡንቸኛው የበኩሉን ግምት ተናገረ፡፡
ይሁንና አባታቸው እንደጠፋ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ አልፎ አልፎ ልጆቹ ወደ ጫካና ወደ ተራራ ሄደው ከፍ ባለ ድምፅ አባታቸውን ይጣራሉ፡፡ መልስ ሳያገኙ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በሁኔታቸው እየተሰላቹ ስለሄዱ መፈለጉን አቆሙ፡፡
ሕፃን ወንድማቸው ግን እንደነሱ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ አንድ ቀን ጧት እናቱ አቅፋው ሳለ፣ ህፃኑ ልጅ “አባቴ የት አለ? አባቴን እፈልጋለሁ፡፡” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገረ፡፡ ታላቅ ወንድሙ ጥልቅ ዐይን “እውነት ነው፡፡ አባባ የት አለ?” በማለት ሕፃኑን እየተመለከተ እርሱም ጠየቀ፡፡ “አሁኑኑ ተነስተን አጥብቀን ብንፈልገው ይሻላል” ሲል ጡንቸኛው አምርሮ ተናገረ፡፡
መፈለግ ቀጠሉ“ቆይ-ቆይ ከሩቅ ቦታ የለቅሶ ድምጽ ይሰማኛል፡፡ በዚህ በኩል… ጪኸት እየሰማሁ ነው! ተከተሉኝ!” በማለት ቆቁ አስገነዘበ፡፡ እንደ ጩኸቱ ቅርበትና ርቀት ቆቁ በተሰማው አቅጣጫ ተያይዘው ተጓዙ፡፡ በመጨረሻም ወደ አንድ ወንዝ ተቃረቡ፡፡ አባታቸው በወንዙ ዳርቻ በጦሩ ከወጋው አነር ጋር ተፋጦ አዩት፡፡ አነሩ የአባታቸውን እግር አቁስሎታል፡፡ “አባባን ማዳን ይገባናል!” በማለት ጡንቸኛው ጮኸ፡፡ በቅጽበት በጠንካራ ጡንቾቹ አነሩን አነቀው፡፡ የታነቀው አነር አየር አጥቶ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡
“እጅግ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ደረሳችሁልኝ! ዘነጣጥሎ ይበላኝ ነበር፡፡ በጦር ብወጋውም አስቀድሞ አቁስሎኝ ስለነበር ደከመኝ፡፡ እህል ውሃም ስላልቀመስኩ ድካሜ ተባባሰብኝ፡፡ አመጣጤ የሚታደን ነገር ለማግኘትና ለእናንተ ለማምጣት ነበር” እያለ አባታቸው አስረዳ፡፡ ሁሉም ሰው “ጀግኖች ናቸው፡፡” በማለት አደነቃቸው፡፡
ወንድማማቾቹ ይህንኑ የሕዝብ አድናቆት ሰሙ፡፡ በመካከላቸው ታላቅና ኃይለኛ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ አባታቸውን በማዳን ማን ዋነኛውን ተግባር (ሥራ) እንደሰራ ለማወቅ ይነታረኩ ጀመር፡፡ ጥልቅ ዐይን “እኔ ዱካውን (ኮቴውን) ባላየው ኖሮ አባታችን የሄደበትን አናውቀውም ነበር” አለ፡፡ ቆቁ በበኩሉ “ዱካው አንድ ቦታ ስንደርስ ጠፍቷል፡፡ እኔ የለቅሶውን ጩኸት ሰምቼ ባልመራችሁ ኖሮ አባታችንን ማግኘት አንችልም ነበር” ሲል ተከራከረ፡፡
“ሁለታችሁም ተሳስታችኋል፡፡ አባታችንን ብናገኘው ምን ዋጋ አለው፡፡ እኔ አነሩን ባልገልለት ኖሮ አባታችን እኮ በአነሩ ይበላ ነበር፡፡ ዋናው ክብር ለእኔ ይገባኛል!” እያለ ጡንቸኛው ደነፋ፡፡ ወደ አባታቸው ሄዱ፡፡ እርሱን በማዳን ረገድ ክብር የሚሰጠው ማን እንደሆነ እንዲነግራቸውም ጠየቁት፡፡
አባታቸውም “ሰማችሁ ልጆቼ እኔን በመታደጋችሁ ባለውለታዬ ናችሁ፡፡ ከሦስታችሁም እኔን አድኖ ለቤት ለማብቃት ትልቁን ክብር የሚያገኝ የለም፡፡ አንዳችሁም ትልቁን ክብር የሚያሰጥ ውለታ አልሰራችሁም፡፡ ለትልቁ ክብር የሚበቃ ሥራ የሰራው ይህ ህፃን ወንድማችሁ ነው፡፡  ክብር ለሕፃኑ ትንሽ ወንድማችሁ ይገባዋል፡፡ ጀግናችሁ ነው” በማለት አባታቸው ነገራቸው፡፡ ትንሹን ሕፃንም ታቀፈው፡፡
*         *        *
ትክክለኛው ክብርና ምሥጋና ለሚገባው ተገቢውን ክብር እንስጥ፡፡ የሌሎችን ዋጋ ለመውሰድ ጥቅማቸውንም ለመንጠቅ አንሞክር፡፡
በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስን አንመኝ! ዛሬ ሁለ-መናችንን ጠንቅቀን ለማየት ጥልቅ-ዐይን ያስፈልገናል፡፡ የምናየውንና የሚገጥመንን ሁሉ ያላግባብ እንዳንመዝንና የተሳሳተ ምላሽ እንዳንሰጥ ቆቅነት ያስፈልገናል፡፡ ይሄ ሁሉ ኖሮን ግን አቅም ማዳበር ካልቻልን ከንቱ ነው! በመጨረሻም እንደህፃን የዋህ የሆነ ልቡና ያሻናል - የምንፈልገውን ሁሉ በንፅህና ለመጠየቅ! ተስፋ የማይቆርጥ የህፃን መንፈስ ሁልጊዜም ያስፈልገናል፡፡ መሸለም ያለበትና ዘላቂው ተሸላሚ ይሄ ተስፋ የማይቆርጥ የነገ ተስፋ ነው!
ቻይናዎች ሁለት የፊደል ባህሪያትን አገጣጥመው ነው ድቀትን (Crisis)፣ የችግር ጊዜን፤ የሚተረጉሙት። ሁለቱ ባህሪያት ጣጣ (Risk) እና አጋጣሚ (Opportunity) ናቸው፡፡ አንድን ጉዳይ፣ (የችግር ጊዜ) ለማሸነፍ የሚያመጣውን ጣጣ ልንችል፣ ያሉንን አጋጣሚዎች ልንጠቀም ዝግጁ መሆን አለብን እንደማለት ነው፡፡ የሀገራችንን አያሌ ችግሮች እንዲህ ቆርጠን እንፍታቸው ካ›ልንና ዝግጁነት ካላሳየን፣ የውሃ ላይ ኩበት ነው የምንሆነው፡፡ ጣጣውን ችሎ አጋጣሚን ለመጠቀም መነጋገር,፣ መመካከር ፣ አዕምሮን ከአዕምሮ ማወዳደርና መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም ያለፈቻቸው አምስት ዘመናት አሉ፡፡ አንደኛው “ዓለም እኔን የምትሰማኝን ያህል ናት” ያልንበት ነው፡፡ ሁለተኛው “ዓለም እኔ ነች ብዬ የማስባት ናት” የምንልበት ነው፡፡ ሶስተኛው ዓለም እልቆ መሣፍርት የሌላት ማሽን ናት፡፡ እንዴት እንደምትሠራ እደርስባታለሁ” የምንልበት የሳይንስ ዘመን ነው፡፡ አራተኛው “ዓለም እኔ በፈጠርኳቸው ልዩ ልዩ ምናልባቶች የተሞላች ስትሆን ይምህ የእኔ አመለካከት ያመጣው ነው” የተባለበት ነው፡፡ በመጨረሻም፤ “የእኔ ዓለም ማናቸውም ቀመር (formulation) የማይወስነው መዋቅር ያላት ናት፡፡ እኔ ዓለምን የማያት ከሷ ጋር እንዳለኝ ጅምላ ልምድ ነው። እናም በራሴ ምልክት ስሪቶች (Symbolic constructs) ራሱን ነፃ በማውጣት መንፈስ እየተጫወትኩ፣ እየተንቀሳቀስኩ ነው” የምንልበት ዘመን ነው፡፡ የዓለምን ታሪክ ወደራሳችን ተርጉመን ፋይዳ ሰጥተን ካስተዋልነው፤ ለውጥ የማምጣትና የማሸነፍ ዕድል አለን፡፡
ቴድ ሲልቬይ የተባለ ፀሀፊ ይሄን ይላል “... ለደጋ ፍየሎች መረማመጃ የድንጋይ ደረጃ እንሰራለን። ለእንስሶች ማረፊያ ቤት እንሰራለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእባብም የሚያስደስተውን የአየር ማረጋጊያ (Air conditioning) እናደርጋለን! ለሰው ልጅ ግን ተገቢውን መጠለያ፣ ለህፃናትም በቂ መኖሪያ ሥፍራ፣ አንሰጥም” ይላል፡፡ ለዜጎቻችን ቢያንስ መሰረታዊውን የቤት ችግር ማስወገድ - በተለይ ይሄ ሁሉ የቤት ሙስና ባለበት አገር - እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አናንቀላፋ፡፡ በግሪክኛ Hypnos - እንቅልፍ ማለት ነው፡፡ Hypnos የሚለው ቃል ሥረ ቃሉ hypnosis ነው፡፡ ይህኛው ግን በመንቃትና በመተኛት መካከል ያለ ሰመመናዊ ስሜት ነው፤ ይለናል ሚካኤል ፓወል፡፡
ሁኔታዎች አጥፊያችን ሆነው ስናገኛቸው በቆቅ ዐይን ማየት እንጂ ሰመመን ውስጥ (Hypnosis) ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ መንቃት፣ ጆሮአችንን ማንቃት፣ አቅማችንን ማወቅና መስፈንጠር፤ እመርታ ማሳየት አለብን፡፡ አለበለዚያ እንደ አፈ-ታሪኩ፤ “ዕባብ ያፍዝ ያደንግዝ ያደረገባት ወፍ፤ ክንፍ እንዳላት ትረሳለች” መባል አይቀርልንም፡፡  



Read 6855 times
Administrator

Latest from Administrator