Saturday, 17 December 2011 11:15

ቢሊየነሯ ቻይናዊት

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(1 Vote)

ትላልቅ ህልሞች

በራሳቸው ጥረት ሚሊዬነር የሚሆኑ ሰዎች የመጀመሪያ ምስጢራቸው ትላልቅ ህልሞችን ማለም ነው ይላል - ብርያን ትሬሲ የተባለ የስኬት ባለሙያ፡ የዛሬዋ ባለታሪካችንም ገና በታዳጊነቷ ትላልቅ ህልሞችን የሰነቀች ቻይናዊት እንስት ነበረች፡፡ ዝሃይ ሜይኪውይንግ የራስዋን ቢዝነስ የመፍጠር ህልም በውስጧ የተጠነሰሰው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው - የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ ቀጣይ የዕድገት እንቅስቃሴ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ዝሃይ ያደገችው በቻይና እጅግ የበለፀጉ ግዛቶች ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ በሆነውና በደቡባዊ ቻይና በሚገኘው ጉዋንግዶንግ ግዛት ውስጥ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ላለመውሰድ የወሰነችው ዝሃይ፤ ይልቁንም ከእናቷ ላይ ትንሽ ገንዘብ ተበድራ ጨርቃ ጨርቅ እየገዛች መሸጥ ጀመረች - ቢዝነስ ልሞክር በሚል፡፡ መጀመሪያ ላይ ታዲያ አልተሳካላትም፡፡ ኪሳራ በኪሳራ ሆነች፡፡ ሆኖም ቢዝነስ ዕጣ ፈንታዬ አይደለም በሚል ተስፋ መቁረጥ ሥራውን እርግፍ አድርጋ አልተቀመጠችም፡፡ ከኪሳራዋ ተምራ ቢዝነሱን ቀጠለች፡፡ የመጀመሪያውን ቢዝነሷን እያስተዳደረች ሳለ በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድሎችንም ማስተዋል ጀመረች፡፡ እሷ ያደገችበት የጉዋንግዶንግ ግዛት በቤት እቃዎች ማምረቻ ማዕከልነቱ ይታወቅ ነበር፡፡  በዚህ ግዛት የሚፈበረኩ ምርቶች ዘመናዊ ናቸው ተብለው ይታሰብ የነበረ ሲሆን  በሰሜኑ ክፍል ብዙ ፈላጊ ደንበኞችም ነበሩት፡፡ ሚስ ዝሃይ የቤት እቃዎች ምርት ቢዝነስውስጥለመግባት የወሰነችውም ለዚህ ነበር፡፡ ዘላ ግን አልነበረም የገባችበት፡፡ መጀመሪያ ራሷን ከስራው ጋር በቅጡ ለማስተዋወቅ በማሰብ  ከደቡቡ የአገሪቱ  ክፍል ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ምርት አቅራቢዎችን እንዲያገኙ ስታግዝ ቆየች፡፡ በስራው ልምድ እያገኘች ስትመጣ ራሷ በቀጥታ በንግዱ ውስጥ መሳተፍ ጀመረች፡፡

ዕድሜዋ 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲደርስ ቤጂንግ ውስጥ የራሷን ፋብሪካ አቋቋመች፡፡  ወጪዎችን ለመቀነስና የጥራት ችግር እንዳይፈጠር በማሰብም በአንድ ምርት ላይ አተኩራ ለመስራት ወሰነች - ትራሶችን ብቻ፡፡ ቢዝነሷ ስኬት እየተቀዳጀ መጣ፡፡ ኩባንያዋ ከፍተኛ ገቢ እያገኘ መሆኑም ይወራ ጀመር፡፡

አስደንጋጭ ገጠመኝ

እያንዳንዷን የምታገኛትን ሳንቲም ሁሉ በንግድ ስራዋ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የምትወደው ዝሃይ፤ የመኖሪያ አፓርትመንት ኪራይ በመክፈል ሌላ ወጪ ማውጣት ተገቢ መስሎ ስላልታያት ኑሮዋን እዚያው ፋብሪካው ውስጥ ማድረጓን ታስታውሳለች፡፡ ፋብሪካ ውስጥ ትውላለች፤ ቢሮዋ ውስጥ ታድራለች፡፡ በርካቶቹ ሰራተኞቿም በፈቃዳቸው እዚያው ነበር የሚኖሩት፡፡

አንድ ሌሊት ግን አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ ዘራፊዎች ቢሮዋን ሰብረው በመግባት የገንዘብ ካዝናውን እንድትከፍላቸው ጠየቋት፡፡ ሚስ ዝሃይ ግን ለመክፈት ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ምክንያቷንም ስትገልፅ፤ “ካዝናውን ከከፈትኩላቸው በኋላ እንደሚገድሉኝ ስላመንኩ ነው” ብላለች፡፡ ከዚያስ? ዘራፊዎቹ ትተዋት አልሄዱም፡፡ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ፈፀሙባት፡፡ “ፊቴ እና ጉሮሮዬ ላይ ሳይቀር ተወግቻለሁ” ይሄ ብቻ ግን አልነበረም - ጥቃቱ፡፡ ብዙዎቹ ጥርሶቿም ወላልቀዋል - በድብደባው፡፡ በመጨረሻ የእርዳታ ጩኸቷን የሰሙ ጥቂት ሠራተኞች ደርሰውላት ነው ነፍሷ የተረፈው፡ በባለሦስት ጐማ ቢስክሊሌት ሆስፒታል ወስደዋት ህክምና በማግኘቷ፡፡

እንደገና መጀመር

የማታ ማታ ዝሃይ ከአስደንጋጩ የስቃይ ገጠመኟ በማገገም ትዳር መሰረተች፡፡ ከባለቤቷ ጋር በመሆንም በትውልድ ቀዬዋ ጉዋንግዶንግ ግዛት ውስጥ የቤት እቃዎች ንግድ ጀመረች - በ1990ዎቹ ዓመታት ማለት ነው፡፡

በወቅቱ ብዙ ሰዎች በምትከተለው የቢዝነስ ሞዴል ላይ ጥርጣሬ እንደነበራቸው የምታስታውሰው ዝሃይ፤ “በእርግጥ በጣም ውጤታማ ነበር” ስትል በእርግጠኝነት ትናገራለች፡፡ ዝሃይ የተገበረችው ዕቅድ በወቅቱ የቤት ኪራይ እርካሽ በነበረበት የከተማ ዳርቻዎች ሰፋፊ መደብሮችን መክፈት ነበር፡፡ ሰፊ ቦታዎችን መያዝ ማለት ደግሞ  ብዙ ዓይነት ምርቶችን ለሽያጭ ማቅረብ ማለት ነው፡፡

በጊዜው በኢንዱስትሪው ውስጥ ያልተለመደ ነገር ለመፍጠርም ጥራለች - የትርፍ ጣሪያዋን በ30 በመቶ ዝቅ አድርጋ የምርቶችን ዋጋ በመቀነስ፡፡

የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በተመለከተ የነበረው አመለካከት መለወጡም ለቢዝነሱ ስኬት የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እስከ 1990ዎቹ ዓመታት ድረስ በቻይናውያን መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች በእጅ የተሠሩ ነበሩ፡፡ ብልፅግና ይበልጥ እየተስፋፋ ሲመጣ ግን በማደግ ላይ የሚገኘው የመካከለኛ ገቢ የህብረተሰብ ክፍል በባለሙያዎች የተመረቱ ምርጥ የቤት ዕቃዎችን የመጠቀም ፍላጐቱ እያደገ መጣ፡፡

ዝሃይ ሜይኪውይንግ፤ የቢዝነስ ዕቅዷ ስኬታማነት መረጋገጡንና ጠንካራ ገበያ  እንደፈጠረላትም ትናገራለች፡፡ ይሄም ብቻ ግን አይደለም፤ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ውስጥ በግዛቱ እጅግ ትልቁ የቤት እቃዎች መሸጫ መደብር ሊሆን በቅቷል፡፡

የቢዝነስ ዘርፎችን ማስፋት

ቢዝነሱ ትርፋማ እየሆነ ሲመጣ ኩባንያው ወደ ሌሎች በርካታ እንቅስቃሴዎች ራሱን ማስፋት ጀመረ - አንዱ የሪል እስቴት ገበያ ነው፡፡

የቤት እቃዎች የሚገዙ ብዙ ደንበኞች በሪል እስቴት ላይም ገንዘባቸውን እንደሚያፈሱ ማስተዋላቸውን የምትናገረው ዝሃይ፤ ይሄ ደግሞ ሪል እስቴት መዋዕለ ንዋይን ለማፍሰስ ጥሩ ዘርፍ መሆኑን እንድትገምት አድርጓታል፡፡

በርካታ የኢኮኖሚ ተንታኞች የቻይና የሪል እስቴት ገበያ ኪሳራ ላይ እንደሚወድቅ ቢያስጠነቅቁም ዝሃይ ግን ይሄን አትቀበልም፡፡ በፍፁም! ባይ ናት- ዝሃይ፡፡

ነገሩ በጊዜ ምርጫህ ላይ የተሞረከዘ ነው ብላለች፡፡ የእሷ ኩባንያ በሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰው ዋጋው በጣም ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ነበር - የዛሬ 10 ዓመት ገደማ፡፡ ሆኖም ኪሳራ ላይ አልወደቀም፡፡ አሁንም ቢሆን ኩባንያዋ ወደ ፊት ሊገጥሙት የሚችሉ ችግሮችን ተቋቁሞ ለማሸነፍ ዝግጁ እንደሆነ ዝሃይ ታምናለች፡፡

እቺ ታላላቅ ህልሞችን ሰንቃ የቢዝነሱን ውጣ ውረድ በጽናት ያሳለፈችው ቻይናዊት እንስት፤ ዛሬ 20ሺ ሠራተኞች የሚያስተዳድር ግዙፍ ኩባንያዋ ፕሬዚዳንት በመሆን እየመራች ትገኛለች፡፡ ፋይናንስ፣ ብረታብረት፣ የችርቻሮ ንግድና ሪል እስቴትን የሚያካትተው “Heung kong Group” የተባለ ኩባንያዋ ዓመታዊ ሽያጭ 2.9 ቢ.ዶላር ገደማ እንደሚደርስ የሚገመት ሲሆን እሷና ባለቤቷ የቻይናውያን ባለፀጐች ስም ዝርዝር በሚያወጣ መጽሔት ውስጥ ስማቸው በየጊዜው እንደሚወጣ ይታወቃል፡፡

እቺ ስኬታማ ቻይናዊት በቻይናውያን ባለፀጐች ዘንድ በንፅፅር ሲታይ እንደ አዲስ ክስተት በሚቆጠረው የችሮታ (በጐ አድራጐት) ተግባር ላይም በቀዳሚነት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

በ2010 እ.ኤ.አ የዓለማችን ሁለት ግንባር ቀደም ባለፀጐች - ቢል ጌትስና ዋረን በፌ በቻይና ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የጉብኝታቸው ዓላማም በቻይና የሚገኙ የቢዝነስ ሰዎች በችሮታ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት ነበር፡፡

ለአብዛኞቹ ቻይናውያን ባለሃብቶች የምዕራቡ ዓለም ችሮታ የመስጠት ልማድ እንግዳ ቢሆንም ለቢሊዬነሯ ዝሃይ ግን ሁለት አስርት ዓመታት ያስቆጠረ ተግባር ነው፡፡ ዝሃይ የችሮታ ተግባር ላይ የመሳተፍ ፍላጐት ያደረባት ገና የመጀመሪያ ሃብቷን ስታገኝ እንደነበር ታስታውሳለች - በ1990ዎቹ ማለት ነው፡፡ አሁንም ታዲያ የችሮታ ተግባር በንግድ ውስጥ ለመሰማራት ዋና ማነቃቂያ ሆኗታል፡፡ ችሮታ ለመስጠት ነግዶ ማትረፍ የግድ ነውና!! “ቢዝነሴን ስጀምር ከድህነት ማምለጥ ነበር የምፈልገው፡፡ ሆኖም እውነተኛ እሴታችን ያለው ለህብረተሰቡ ማበርከት ባለብን አስተዋፅኦ ውስጥ እንደሆነ እየተገነዘብኩ መጣሁ” ብላለች - ቢሊየነሯ ቻይናዊት፡፡

ለዚህ ሁሉ ስኬት ያበቃት ግን ገና በለጋ ዕድሜዋ የሰነቀችው ትልቅ ህልሟ ነው - የራሷን ቢዝነስ በመፍጠር መበልፀግ!!

 

 

Read 3962 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 11:25